በሰከንድ ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚወነጨፉ ሚሳዔሎችን ለመታጠቅ የኃያላኑ ፉክክር

ሰሜን ኮሪያ ሞክሬዋለው ያለችውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔልን የሚያሳይ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, KCNA via EPA

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ ሞክሬዋለው ያለችውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል

እንደ መርፌ ጫፍ የሾሉ፣ 11 ሜትር ዝርመት ያላቸው፣ 15 ቶን የሚመዝኑ እና እያንዳንዳቸው "ዲኤፍ-17" የሚል ጽሑፍ የሰፈረባቸው የቻይና ሕዝብ ነጻነት ሠራዊት ሚሳኤሎች በቤይጂንግ በተካሄደ ወታደራዊ ሰልፍ ላይ በመኪና ተጭነው ሲጓዙ ታየ።

ቻይና የዶንግፌንግ የተባሉትን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎቿን ለዓለም ይፋ ያደረገችው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2019 ባካሄደችው በዚህ ብሔራዊ ሰልፍ ላይ ነበር።

አሜሪካ እነዚህ መሳሪያዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ቀድሞውንም ታውቅ የነበረ ቢሆንም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቻይና መሳሪያዎቹን ይበልጥ በማሻሻል ወደፊት እየገሰገሰች ነው።

ከድምፅ ፍጥነት ከአምስት እጥፍ በላይ በሆነ ፍጥነት የመጓዝ እና ከተወነጨፉ በኋላ አቅጣጫቸውን የማስተካከል አቅም ያላቸው እነዚህ ሚሳዔሎች፤ እጅግ በጣም ኃይለኛ የጦር መሣሪያ ናቸው። ጦርነቶችን የሚካሄዱበትን መንገድም ለመለወጥ አቅም አላቸው።

ሚሳዔሎቹን ለመታጠቅ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ውድድር እየጨመረ የመጣውም ከዚህ የተነሳ ነው።

'ካውንስል ኦን ጂኦስትራቴጂክ' በተባለው ቲንክ ታንክ የብሔራዊ ደኅንነት ተመራማሪ የሆኑት ዊልያም ፍሪር፤ "ይህ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ያልነበረ እና በመንግሥት ተዋናዮች መካከል እየታየ ያለው የጂኦፖሊቲካዊ ፉክክር አንድ አካል ብቻ ነው" ይላሉ።

የቻይና ዲኤፍ-17 ሚሳዔል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ዲኤፍ-17 ሚሳዔል

ሩሲያ፣ ቻይና እና አሜሪካ፡ ዓለም አቀፍ ፉክክር

በቤይጂንግ የተካሄደው ሥነ ሥርዓት ቻይና በሃይፐርሶኒክ ቴክኖሎጂ እያስመዘገበችው ያለው ዕድገት የሚያስከትለው ስጋት እየጨመረ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አስነስቷል።

ዛሬ ቻይና በሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች መስክ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። ሩሲያም ትከተላለች። አሜሪካ ግን እዚህ ላይ ለመድረስ እየጣረች ነው። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ገና ምንም የላትም።

ተመራማሪው ፍሪር፤ ቻይና እና ሩሲያ ቀድመው የተገኙበት ምክንያት ቀላል መሆኑን ይናገራሉ። ምክንያቱ "ከጥቂት ዓመታት በፊት በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸው ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ብዙ ምዕራባውያን ሀገራት በዚህ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹን ሁለት አስርት ዓመታት ያሳለፉት ከጂሃዲስት ሀሳብ የመነጨ የሀገር ውስጥ ሽብርተኝነትን ሲዋጉ እንዲሁም በውጭ አገር በፀረ አማጺያን ጦርነቶች ላይ ሲያተኩሩ ነው።

ሰሜን ኮሪያ የሞከረችው ሚሳዔል ሲወነጨፍ

የፎቶው ባለመብት, KCNA/EPA-EFE/REX/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ የሞከረችው ሚሳዔል

ከቻይና እና ከሩሲያ በተጨማሪ ሌሎች ሀገራትም ወደፊት እየገሰገሱ ነው። እስራኤል 'አሮው 3' የተባለ የሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል አላት።

የሃይፐርሶኒክ የጦር መሳሪያ እንደታጠቀች የምትናገረው ኢራን፤ በሰኔ ወር በተካሄደው የ12ቱ ቀናት ጦርነት ወቅት በእስራኤል ላይ የሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ገልጻለች።

በእርግጥም መሳሪያው በከፍተኛ ፍጥነት ይጓዝ የነበረ ቢሆንም እውነተኛ ሃይፐርሶኒክ ተብሎ ለመመደብ በሚያስችል ሁኔታ በበቁ መልኩ አቅጣጫውን የመቀየር እና የማስተካከል አቅም እንደሌለው ታስቧል።

ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ከአውሮፓወያኑ 2021 ጀምሮ አዋጭ እና የሚሠራ ባለቸው የራሷ መንገድ መሳሪያውን እየገነባች መሆኑን ትገልጻለች።

የኢራን የመጀመሪያው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ወታደራዊ ሰልፍ ላይ በመኪና ተጭኖ እየሄደ

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ሰኔ ላይ በተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት እስራኤል ላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል ማስወንጨፏን ገልጻለች

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይን እና ጃፓንን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል ቴክኖሎጂ ላይ ገንዘባቸውን እያፈሰሱ ነው።

የመከላከያ ኃይሏን አቅም በማጠናከር ላይ ያለች ምትመስለው አሜሪካ፤ "ዳርክ ኢግል" ስትል የጠራችውን ሃይፐርሶኒክ መሳሪያ ይፋ አድርጋለች።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፤ ዳርክ ኢግል "የሀገራችን እና የጦር ሠራዊቷን ኃይል እንዲሁም ቁርጠኝነት የሚያስገነዘብ" ነው ያለ ሲሆን፣ "የጦር ሠራዊቱ እና የባሕር ኃይሉ ሃይፐርሶኒክ የጦር መሳሪያ ግንባታ ጥረቶችን መንፈስ እና ገዳይነት የሚያመለክት" እንደሆነም ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ይህንን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየመሩ ግን ያሉት ቻይና እና ሩሲያ ናቸው። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ግን ይህ ሁኔታ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

ጎብኚዎች የቻይና ዲኤፍ-41 አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል እና ዲኤፍ-17 ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል አጠገብ ፎቶ ሲነሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጎብኚዎች የቻይና ዲኤፍ-41 አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል እና ዲኤፍ-17 ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል አጠገብ ፎቶ ሲነሱ

'ሃይፐር ፋስት' እና 'ሃይፐር ኢራቲክ'

'ሃይፐርሶኒክ' ማለት ከድምፅ ፍጥነት አምስት እጥፍ ወይም በሰዓት 6,210 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት የሚጓዝ መሳሪያ ማለት ነው። ይህ ፍጥነታቸው ከድምጽ ፍጥነት እኩል ከሚጓዙት ሱፐር ሶኒክ መሳሪያዎች በተለየ መደብ ውስጥ ይከትታቸዋል።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥሩበት አንዱ ምክንያት ይህ ፍጥነታቸው ነው።

እስካሁን ድረስ በጣም ፈጣኑ ሚሳዔል የሩሲያው 'አቫንጋርድ' ነው። 'አቫንጋርድ' በሰዓት ከ33 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚወነጨፍ የሚነገር ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ ግን የሚጠቀሰው በሰዓት 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ይጓዛል ተብሎ ነው።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል ጥቃት የሚፈጽምበትን ሂደት የሚያሳይ ምሥል

እንደ ተመራማሪው ፍሪር ገለጻ፤ የሚያደርሱትን ውድመት በተመለከተ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ከሱፐርሶኒክ ወይም ሰብሶኒክ ክሩዝ ሚሳዔሎች ብዙም የተለየ አይደለም፥

"በጣም የተለየ የሚያደርጋቸው ለመለየት፣ ለመከታተል እና ለመጥለፍ አስቸጋሪ መሆናቸው ነው" በማለት ያስረዳሉ።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች በዋነኝነት ሁለት ዓይነት ናቸው። ቻይና ይፋ እንዳደረገችው 'ዲኤፍ-17' ዓይነት ሚሳዔሎች ሮኬት ላይ የሚገጠሙ ሲሆኑ፣ አንዳንዴም ከምድር ከባቢ አየር በላይ ሊወነጨፉ ይችላሉ። ከዚያም በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ታች በመውረድ ወደ ዒላማቸው ይምዘገዘጋሉ።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች፤ የተለመዱት የባሊስቲክ ሚሳዔሎች ከሚጓዙበት ተገማች አካሄድ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ወጥ እና ተገማች ባልሆነ (ኢራቲክ) መንገድ ከተጓዙ በኋላ ወደ ዒላማቸው አቅራቢያ ሲደረሱ አቅጣጫቸውን ማስተካከል ይችላሉ።

የሚሳዔሎቹን መዋቅር የሚያሳይ ምሥል

ከዚህም በተጨማሪ በራዳር እንዳይለዩ ወደ ምድር ዝቅ ብለው የሚወነጨፉ ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳዔሎችም አሉ።

በተመሳሳይ መልኩ ሮኬቶችን በመጠቀም በፍጥነት የሚወነጨፉት እነዚህ ሚሳዔሎች፤ ሃይፐርሶኒክ ፍጥነት ላይ ከደረሱ በኋላ የተገጠመላቸው 'ስክሪምኤት ኢንጅን' የተባለ ልዩ ሥርዓት መሥራት ይጀምራል።

ይህ ሥርዓት ከአየር ላይ የሚያገኘውን ኦክስጅን በመጠቀም ዒላማቸው ጋር እስከሚደርሱ ድረስ ረጅም ርቀት እንዲጓዙ ያስችላቸዋል።

እነዚህ ሚሳዔሎች "ሁለት ጥቅም ያላቸው መሳሪያዎች" ናቸው። ይህም ማለት በሚሳዔሎቹ ላይ የሚጫነው ኒውክሌር ወይም መደበኛው ዓይነት ፈንጂ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን እነዚህ የጦር መሳሪያዎች አደገኛ የሚያስብላቸው ፍጥነታቸው ብቻ አይደለም።

በወታደራዊ አገላለጽ አንድ ሚሳዔል "ሃይፐርሶኒክ" ተብሎ ለመመደብ በሚበርበት ወቅት አቅጣጫውን የሚቀይር መሆን አለበት።

ያስወነጨፈው አካል፤ ሚሳዔሉ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዒላማው እየበረረ ባለበት ጊዜ እንኳ በድንገት እና ባልተጠበቀ መንገድ አቅጣጫውን መለወጥ የሚችል መሆን አለበት።

ሚሳዔሎቹ ከ15 ደቂቃ በታች ባለጊዜ ውስጥ ሊመቱ የሚችሉበትን ርቀት የሚሳይ ካርታ

ይህ አቅማቸው ለመጠለፍ አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል። አብዛኞቹ በመሬት ላይ የተተከሉ ራዳሮች የሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሉ በርሮ መጨረሻ ዒላማው ጋር ሳይቀርብ በፊት ይለዩታል በሚል የሚተማመኑባቸው አይደሉም።

የዩናይትድ ኪንግደም ሮያል ባሕር ኃይል የቀድሞው አዛዥ እና እና የፀረ አየር ጦርነት ባለሙያ የሆኑት ቶም ሻርፕ፤ ሃይፐርሶኒክ መሳሪያዎች ከድምፅ ፍጥነት በአምስት እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ፍጥነት የሚጓዙ ቢሆንም እነርሱን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች እንዳሉ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት "ውጤታማ" እንደሆኑም ጭምር ይከራከራሉ።

የመጀመሪያው አማራጭ የሚሳዔሎቹን ዒላማ ለመከታታል እና ለመለየት ይበልጥ አስቸጋሪ ማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ ረገድ መርከቦች ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ።

"ከንግድ ሳተላይቶች የሚገኙ በደንብ ግልጽ ያልሆኑ የሳተላይት ምሥሎች እንኳ ዒላማ ለማድረግ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ ሲባል ለገበያ የሚቀርቡት ከጥቂት ደቂቃዎች መዘግየት በኋላ መሆን አለበት" በማለት ሌላኛውን መፍትሔ ያስረዳሉ።

ዒላማን ለመወሰን በሚያስችል ደረጃ የሆኑ አሁናዊ እና ትክክለኛ የሳተላይት ምሥሎችን ማግኘት አስቸጋሪ እና ውድ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ነገር ግን ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና ሌሎች እየመጡ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ በኋላ ይህንን ሊለውጡ እንደሚችሉ ጠቁሟል።