ስለ አዲሱ የሩሲያ ኦሬሽኒክ ሚሳዔል ምን እናውቃለን?

የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ኦሬንሺክ የተመጣጠነ የYars-M ICBM ስሪት ሊሆን ይችላል ይላሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሐሙስ እለት የዩክሬን ዲኒፕሮ ከተማ በሩሲያ የአየር ጥቃት ከተመታች በኋላ የዓይን እማኞች ያልተለመደ ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ለሦስት ሰዓታት ያህል የዘለቀ ፍንዳታዎችንም አስከትሏል።

ጥቃቱ በጣም ኃይለኛ የሚሳዔል ጥቃትን ያካተተ ሲሆን፣ የዩክሬን ባለስልጣናትም የአህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳዔል (ICBM) ባህሪ እንዳለው ተናግረዋል።

የምዕራቡ ዓለም ባለስልጣናት ይህን መሰል ጥቃት የአሜሪካ የኒውክሌየር ፕሮግራምን በተጠንቀቅ እንዲሆን ያደርጋል በሚል ጉዳዩን በፍጥነት አስተባብለዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር፣ሩሲያ “አዲስ መደበኛ መካከለኛ ርቀት” የሚወነጨፍ ኦርሽኒክ (በሩሲያኛ የሄዝል ዛፍ እንደማለት ነው) የተባለ ሚሳዔል መጠቀሟን ገለፁ።

ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን በሚገኘው ድኒፕሮ ከተማ ጥቃት ያደረሰችው “በአዲስ የመካከለኛ ርቀት ሚሳዔል” መሆኑን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።

መሳሪያው በሰኮንድ ከ2.5-3 ኪ.ሜ. (ከድምጽ 10 እጥፍ የሚበልጥ ፍጥነት) ይጓዛል ያሉት ፑቲን፣ “በአሁኑ ወቅት ይህንን መሳሪያ በጸረ ሚሳዔል ማስቆም የሚቻልበት አቅም የለም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በዲኒፕሮ ወሳኝ ወታደራዊ የኢንዱስትሪ ስፍራ መመታቱን ገልጸው፣ ሚሳዔሎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን የሚያመርት እንደነበር አስታውቀዋል።

ጥቃቱንም እንደ ሙከራ ገልጸውት፣ “የተሳካ” ሲሉ አንቆለጳጵሰው “ዒላማውን መትቷል” ብለዋል።

ከአንድ ቀን በኋላ ለመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ሲናገሩ የሚሳዔሉ ሙከራዎች “በውጊያ ውስጥ ጨምሮ” እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ፑቲን ምንም እንኳ ስለ መሳሪያው መግለጫ ቢሰጡም፣ ምን እንደሆነ ግን ጥርት ያለ መግባባት ያለ አይመስልም።

የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ሚሳዔሉ ኬድር (ሴዳር) በመባል የሚታወቅ አህጉር አቋራጭ ባሌስቲክ ሚሳዔል ነው ሲል ይገልፃል።

የሚሳዔሉ ተተኳሽ በሰዓት 13 ሺህ 600 ኪ.ሜ. (13,600 kph) ይምዘገዘጋል የሚሉት የዩክሬን ወታደራዊ ምንጮች፣ ከተተኮሰበት የሩሲያዋ አስትራከሰን ግዛት፣ ከ1 ሺህ ኪ.ሜ በላይ ከምትርቀው፣ ዒላማው ላይ ለመድረስ 15 ደቂቃ ብቻ ፈጅቶበታል።

ሚሳዔሉ እያንዳንዳቸው 6 አረሮች ያሉት ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው ስድስት አነስተኛ ተተኳሾች የተገጠመላቸው ናቸው ብለዋል።

ይህንን የዩክሬናውያንን መላምት በመውሰድ ቢቢሲ ቬሪፋይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል መርምሯል።

አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ደብዛዛ እና ጥራት የሌላቸው ናቸው። ይኹን እንጂ በምሽት ሰማይ ላይ ስድስት ብልጭታዎችን በግልፅ የሚታዩ ሲሆን፣እያንዳንዳቸው ስድስት ነጠላ ተወንጫፊዎች ይዘዋል።

በሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት የደረሰበት ስፍራ ከዲኒፕሮ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ የሚገኝ የኢንዱስትሪ መንደር ነው።

ፍጥነት ለምን አስፈላጊ ሆነ?

የፑቲን ገለጻ ትክክል ከሆነ፣ሚሳዔሉ ሃይፐርሶኒክ ለሚለው ብያኔ የቀረበ ብቻ ሳይሆን ጥቂት ነገሮችንም ማሳካት ይችላል።

ፍጥነት አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ሚሳዔል በፈጠነ ቁጥር ዒላማውን በፍጥነት ያደባያል።

ዒላማው ላይ ለማድረስ በፈጠነ ቁጥር፣ተቃራኒው የመከላከያ ኃይል ምላሽ የሚሰጥበት ፍጥነት ይቀንሳል።

ባለስቲክ ሚሳዔል ወደ ከባቢ አየር ሲተኮስ በደጋን ቅርጽ እየተምዘገዘገ ሲሆን፣ ወደ ዒላማውም ለመድረስ ተመሳሳይ ጉዞ ያደርጋል።

ነገር ግን ወደ ዒላማው መውረድ ሲጀምር ፍጥነቱን ጨምሮ ይምዘገዘጋል፤ የበለጠ በተምዘገዘገ ቁጥር ደግሞ የበለጠ እድል ይኖረዋል።

ይህም ከምድር ወደ አየር ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ፈታኝ የሆነ የሽክርክሪት እንቅስቃሴ በማድረግ በበለጠ ዒላማውን ለማደባየት ያስችለዋል።

በእርግጥ እንደዚህ አይነት ጥቃቶችን መከላከል ለወታደራዊ ኃይሎች አዲስ አይደለም፤ ይኹን አንጂ ፍጥነቱ እየጨመረ በሄደ መጠን ፈታኝ እየሆነ ይሄዳል።

ለዚህም ነው ፑቲን ይህን አዲስ አይነት ሚሳዔል በሚገልጹበት ወቅት ፍጥነት ላይ አፅንዖት የሰጡት።

በሩሲያ ከተተኮሰ ሚሳዔሎች 80% ያህሉ በዩክሬን ተጨናግፈዋል፤ይህም ያልተለመደ አሃዝ ነው። ነገር ግን እነዚህ ፈጣን የባለስቲክ ሚሳዔሎች ፍጥነቶች ያንን ቁጥር ዝቅ ለማድረግ የታሰቡ ናቸው።

ኦሬሽኒክን ከሌሎች ሚሳዔሎች ጋር በማጣመር ሐሙስ በዲኒፕሮ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የደረሰ ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኦሬሽኒክን ከሌሎች ሚሳዔሎች ጋር በማጣመር ሐሙስ በዲኒፕሮ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የደረሰ ጉዳት

አዲሱ ሚሳዔል ምን ያህል ርቀት ይወነጨፋል?

የሩሲያ ወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ኢሊያ ክረምኒክ ለክሬምሊን ወገንተኛ ለሆነ ጋዜጣ፣ ኢዝቬስቲያ እንደተናገሩት አዲሱ ሚሳዔል እስከ አሁን ድረስ የተፈረጀው በመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች ምድብ ውስጥ ሊሆን ይችላል ።

“ከ2,500 - 3,000 ኪ.ሜ እስከ 5,000 ኪ.ሜ ሊወነጨፉ ከሚችሉ አዲስ የሩሲያ መካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች ጋር የሚመደብ ነው፤ አህጉር አቋራጭ ግን አይደለም” ይላሉ።

ይህም ከሞላ ጎደል መላውን አውሮፓ የሚያካልል ቢሆንም አሜሪካ ግን አይደርስም።

ክራምኒክ አክለውም “የሚሳዔሉ ጫፎች እያንዳንዳቸው የራሳቸው መሪ ያላቸው የሚነጣጠሉ አረሮች መታጠቃቸው ግልጽ ነው” ብለዋል።

እኚህ ባለሙያ ይህ ሚሳዔል አህጉር አቋራጭ የሆነው እና ያርስ ኤም (Yars-M) በመባል የሚታወቀው መሳሪያ አነስ ያለው ስሪት ሊሆን እንደሚችል ጠቁዋል።

ሩሲያ ባለፈው ዓመት ብዙ ነጻ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አረሮች የያዘ አዲስ ሚሳዔል ማምረት እንደጀመረች ገልጻ ነበር።

ሌላው ባለሙያ ዲሚትሪ ኮርኔቭ ለጋዜጣው እንደተናገሩት፣ ኦርሽኒክ አጭር ርቀት በሚወነጨፉት ኢስካንደር (Iskander) ሚሳዔሎች ላይ ተመሥርቶ የተመረተ ሊሆን ይችላል።

ኢስካንደር ሚሳዔል አዲስ ሞተር ተገጥሞለት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በብዛት ጥቅም ላይ ውሏል።

ባለሙያው ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወራት በደቡባዊ ሩሲያ ከሚገኘው የካፑስቲን ያር የሙከራ ጣብያ ላይ ኢስካንደር ገዘፍ ባለ ሞተር ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ይህም ምናልባት ኦርሽኒክ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሐሙስ ዕለት ሩሲያ ወደ ዩክሬን ያስወነጨፈችው ሚሳዔል ከተመሳሳይ ቦታ የተተኮሰ ነው።

ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል?

የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ቭላዲላቭ ሹሪጊን ለኢዝቬስቲያ ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ኦርሽኒክ አሁን ያለውን ዘመናዊ የሚሳዔል መቃወሚያ ሁሉ ማሸነፍ የሚችል ነው።

በተጨማሪም ምንም እንኳ በዲኒፕሮ ፋብሪካ ከመሬት በታች ያሉ ግንባታዎች መውደማቸውን የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ ባይኖርም፣ መሳርያው የኒውክሌር ተወንጫፊን ሳይጠቀም በከፍተኛ ጥልቀት ውስጥ በደንብ የተጠበቁ ምሽጎችን ሊያወድም ይችላል ብሏል።

ሌላው ሩሲያዊ ተንታኝ፣ ኢጎር ኮሮቼንኮ፣ ለታስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ሚሳዔሉ ብዙ ራሳቸውን ችለው የሚምዘገዘጉ አረሮች እንዳሉት በመግለጽ “አረሮቹ ወደ ዒላማው በአንድ ጊዜ በመድረስ” እጅግ በጣም ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

የአደጋ ጊዜ ስጋት አማካሪ የሆኑት ጀስቲን ክሩምፕ ለቢቢሲ ቬሪፋይ ሚሳዔሉ የዩክሬንን አየር መከላከያን የመገዳደር አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

አክለውም “በዚህ ግጭት ውስጥ የዩክሬን ከፍተኛ ስጋት ከሆኑት መካከል አንዱ የሩሲያ አጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎች ናቸው” ብለዋል።