ቭላድሚር ፑቲን በሚሊዮን በርሜል የሚቆጠር ነዳጅ ለሰሜን ኮሪያ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ እአአ ካለፈው መጋቢት አንስቶ ለሰሜን ኮሪያ ከሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ መስጠቷን የሳተላይት ምሥል አሳይቷል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ለትርፍ ያልተቋቋመው ኦፕን ሶርስ ሴንተር የሳተላይት ምሥል በመመልከት ነው መረጃውን ያወጣው።
ነዳጁ የዋለው፣ ፒዮንግያንግ ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት እንድትጠቀምበት ለሰጠችው መሣሪያና ወታደር ክፍያ እንደሆነ የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ ዴቪድ ላሚ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ የሩሲያና ሰሜን ኮሪያ ልውውጥ የተባበሩት መንግሥታትን ማዕቀብ የጣሰ ነው።
ተመድ አገራት በውስን መጠን ካልሆነ በስተቀር ለሰሜን ኮሪያ ነዳጅ እንዳይሸጡ ማገዱ ይታወሳል።
ማዕቀቡ ሰሜን ኮሪያ ምጣኔ ሃብቷ እንዳይነቃቃና ኒውክሌር እንዳታበለጽግ በሚል ነበር የተጣለው።
ቢቢሲ የተመለከታቸው የሳተላይት ምሥሎች፣ ባለፉት ስምንት ወራት 43 ጊዜ ያህል የተለያዩ የሰሜን ኮሪያ የነዳጅ ታንከሮች በሩሲያ ወደሚገኘው ፋር ኢስት አካባቢ መድረሳቸውን ያሳያሉ።
ባሕር ላይ የተነሱ ተጨማሪ ምሥሎች ባዶ ታንኮች በአካባቢው ደርሰው ነዳጅ ሞልተው ሲመለሱ ያሳያሉ።
ሰሜን ኮሪያ በዓለም ገበያ ነዳጅ መግዛት የማይፈቀድላት ብቸኛዋ አገር ናት።
ተመድ በዓመት 500,000 በርሜል የተጣራ ፔትሮሊየም ብቻ አገሪቷ እንድታገኝ ይፈቅዳል። ይህም ከሚፈለገው በታች ነው።
ጉዳዩን በተመለከተ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
አፕን ሶርስ ሴንተር እንደመዘገበው የመጀመሪያው ነዳጅ የደረሰው እአአ መጋቢት 7/2024 ነው።
ይህም ፒዮንግያንግ ለሞስኮ መሣሪያ ከላከች ከሰባት ወራት በኋላ ነው።
ወደ ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መላካቸው ከተገለጸ በኋላ የነዳጅ ዝውውሩ ቀጥሏል። ለመጨረሻ ጊዜ ወታደሮች የተላኩት እአአ ኅዳር 7/2024 ነበር።
የኦፕን ሶርስ ሴንተር ባለሙያው ጆ ብራየን “ኪም ጆንግ ኡን፣ ቭላድሚር ፑቲን ጦርነት እንዲቀጥል መሣሪያ ሲለግስ፣ ሩሲያ ድምጿን አጥፍታ ለደቡብ ኮሪያ ነዳጅ ትሰጣለች። ነዳጁ ሰሜን ኮሪያ ማዕቀብ ከተጣለባት ወዲህ አይታ የማታውቀው መረጋጋት ይሰጣታል” ብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የሚከታተለው የተመድ ቡድን የቀድሞ አባላት የነበሩ አራት ግለሰቦች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በሞስኮና ፒዮንግያንግ መካከል እያደገ የመጣው ግንኙነት ማሳያ ነው።
ቡድኑን እአአ ከ2014 እስከ 2019 የመሩት ሂው ግሪፊትስ “ይህ ልውውጥ የፑቲንን የጦር መሣሪያ እያጠናከረ ነው። ነዳጅ በሚሳኤል ከዚያም ነዳጅ በወታደር እየተለዋወጡ ነው” ብለዋል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ ዴቪድ ላሚ “ሩሲያ በዩክሬን ውጊያ ለመቀጠል የሰሜን ኮሪያን መሣሪያና ወታደሮች ትጠቀማለች። በምላሹ ነዳጅ ትሰጣለች። በኮሪያ ቀጣና፣ በአውሮፓና በኢንዶ-ፓስፊክ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በቀጥታ ይነካል” ብለዋል።
አብዛኞቹ ሰሜን ኮሪያውያን አገር በቀል ከሰል ይጠቀማሉ።
ነዳጅ ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ሚሳኤል መተኮሻ በአገሪቱ ለማዘዋወር፣ ፋብሪካዎችን ለማንቀሳቀስ እንዲሁም ለፒዮንግያንግ ባለሃብቶች መጓጓዣ ይውላል።
ሰሜን ኮሪያ ከሚያስፈልጋት ዘጠኝ ሚሊዮን በርሜል ውስጥ ከሩሲያ የተሰጣት 500,000 በርሜል ነው።
ርካሽ የነዳጅ አቅርቦት
ሰሜን ኮሪያ ማዕቀብ ከተጣለባት በኋላ ነዳጅ የምትገዛው በሕገ ወጥ መንገድ ሲሆን፣ ይህም ባሕር ላይ ማጓጓዝን ስለሚጠይቅ ጊዜና ገንዘብ እንደሚወስድ የሰሜን ኮርያ ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ሰኪውሪቲ ስትራቴጂ የጥናት ባለሙያ ዶ/ር ጎ ሚዮንግዮን ይናገራሉ።
“አሁን ኪም ጆንግ ኡን በቀጥታ ነዳጅ እያገኘ ነው። የተሻለ ጥራት ያለውና በነጻ የሚገኝ ነዳጅም ነው። ለነዳጅ አምራቿ ሩሲያ ሚሊዮን በርሜል ምንም ማለት አይደለም። ለሰሜን ኮሪያ ግን ብዙ ነው” ሲሉም ያክላሉ።

በዝምታ የሚከናወነው ልውውጥ
ኦፕን ሶርስ ሴንተር የተከታተለውና 43 ጊዜ የተደረገው የነዳጅ ጉዞ በይፋ የተደረገ አይደለም።
በሩሲያ ቮስቶክኒ ወደብ ነዳጁ ሲደርስ መከታተል በማይቻልበት መንገድ ነው።
በሰሜን ኮሪያ ምሥራቅና ምዕራብ የባሕር መዳረሻ መጓዛቸውንም የሳተላይት ምሥሎች ያሳያሉ።
የኦፕን ሶርስ ሴንተር አጥኚ ጆ ባይረን እንደሚለው “ከመጋቢት ጀምሮ በየሳምንቱ ምንም ድምጽ ሳይሰማ ይጓጓዙ ነበር” ብሏል።
ነዳጅ ጫኝ ታንከሮቹን ሲከታተል የነበረ ቡድን በእያንዳንዱ መርከብ ላይ ምን ያህል በርሜል ሊጫና እንደሚችል በማስላት የተላከውን የነዳጅ መጠን ለማወቅ ችሏል።
ከዚያም ወደ ቮስቶክኒ የሚገቡትን መርከቦች ምሥል በመመልከት ውሃ ውስጥ ምን ያህል ጠልቀው እንደገቡ በማስላት መርከቡ ላይ የተጫነውን ነዳጅ መጠን ለማወቅ ተችሏል።
ታንከሮቹ መሸከም ከሚችሉት እስከ 90% ሙሉ እንደነበሩ ታውቋል።
“መርከቦቹ ከዚያ በላይ ቢጭኑ ሊሰጥሙ ይችሉ እንደነበር ማወቅ ችለናል” ሲሉ የጥናት ባለሙያው ተናግረዋል።
ሩሲያ በሚሊዮን በርሜል የሚቆጠር ነዳጅ ለሰሜን ኮሪያ መስጠቷና ይህም እአአ በ2023 ከሰጠችው አሥር እጥፍ መሆኑ ታውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት ከወራት በፊት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ሩሲያ ከ500,000 በላይ በርሜል ነዳጅ ለሰሜን ኮሪያ ሰጥታለች ብሏል።
“ነሐሴ ላይ ደመና ስለነበር መርከቦች ማየት አልቻልንም ነበር። በዚህ ወቅት ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን በርሜል ተጉዞ ሊሆን እንደሚችል እናምናለን” ብለዋል አጥኚው።
ማዕቀብን የጣሰው ልውውጥ
ሩሲያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና ሳለ በተመድ ሰሜን ኮሪያ ላይ የተላለፈ ማዕቀብን ጥሳ ነዳጅ ሰጥታለች።
ነዳጁ ከተጓዘባቸው መርከቦች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተመድ ማዕቀብ የተጣለባቸውም ናቸው።
በሩሲያ ግዛት ውስጥ ሳሉ ሕጋዊ እርምጃ መወሰድ ነበረበት።
ሩሲያ የመጀመሪያውን የነዳጅ በርሜል ከላከች ከሦስት ሳምንታት በኋላ የተመድን የነዳጅ ዝውውር ማዕቀብ ተቆጣጣሪ ቡድን አግዳለች።
የዚህ ቡድን አባል አሽሊ ሄስ “የተወሰኑትን መርከቦችና እጃቸው ያለበትን ተቋሞች እየተከታተልን ነበር። ግን 500,000 በርሜል ሳይደርሱ በፊት እንዳናስቆም ቡድናችን ታገደ” ትላለች።
እአአ ከ2021 እስከ 2023 ቡድኑን የመራው ኤሪክ ቮአክ እንደሚለው የቡድኑ ሩሲያዊ አባላት ሥራቸውን ለማደናቀፍ ሞክረዋል።
“አሁን ቡድኑ ስለፈረሰ ሕጉን ችላ ብለው መቀጠል ይችላሉ። መርከቦቹ በሩሲያ ወደብ አርፈው ነዳጅ ጭነው እንዲሄዱ ሩሲያ ማድረጓ ምን ያህል ማዕቀቡ እንደተጣሰ ያሳያል” ብሏል።
አሁን በኦፕን ሶርስ ሴንተር ቦርድ ውስጥ የሚሠራው ኤሪክ “አምባገነን መንግሥታት ያሻቸውን ለማግኘት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ችላ ብለው ተባብረው እየሠሩ ነው።አስጊ ነው። የሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ኢራን እንዳይገኝ መፍራት አለብን” ሲልም አክሏል።
በቀጣይ ምን ይሆናል?
ኪም ጆንግ ኡን ለቭላድሚር ፑቲን ድጋፋቸውን መቀጠላቸው በቀጣይ ምን ይመጣል? የሚል ጥያቄ አጭሯል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ እንደሚሉት፣ ፒዮንግያንስ ለሞስኮ 16,000 ኮንቴነር መሣሪያ የሰጠች ሲሆን፣ በዩክሬን ጦር ሜዳ የሰሜን ኮርያ ባለስቲክ ሚሳኤል ቅሪትም ተገኝቷል።
በቅርቡ ፑቲን እና ኪን ጆንግ ኡን በተፈራረሙት መሠረት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በኩርስክ ግዛት ከሩስያ ጦር ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ለቢቢሲ “ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ የተመድን የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በመጣሳቸው ምላሽ እንሰጣለን” ብሏል።
ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን የስለላ እና ባለስቲክ ሚሳኤል መሣሪያ ግንባታ የሚያሳድግ ልገሳ ታደርጋለች የሚል ስጋት አለ።
የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግሂውን “ሰሜን ኮሪያ ይሄንን ድጋፍ የምትጠይቅበት ዕድል ሰፊ ነው” ብለዋል።
“በውጭ አገር ጦርነት ዜጎች እንዲሞቱ ለሚልክ አገር በሚሊዮን የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ በቂ ምላሽ ነው” ሲሉ የሰሜን ኮርያ ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ሰኪውሪቲ ስትራቴጂ የጥናት ባለሙያ ዶ/ር ጎ ሚዮንግዮን ይናገራሉ።
የሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ግንኙነትን በሱዑል በሚገኘው ኮክሚን ዩኒቨርስቲ የሚያጠኑት አንድሪ ላንኮቭ “ሩሲያ ወታደራዊ መረጃ ማጋራት ይጠቅማታል ብዬ አላስብም ነበር። አሁን ግን ስሌቱ ተለውጧል። ሩሲያ ወታደሮቹን መፈለጓ ለሰሜን ኮሪያ የተሻለ ዕድል ይሰጣታል” ብለዋል።












