የአሜሪካ ረዥም ርቀት ሚሳኤል በሩሲያ ጥቅም ላይ ቢውል ጦርነቱ ምን ሊመስል ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, shutterstock
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዒላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው ተሰምቷል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በሚሳኤሎቿ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት እንዲፈጸም አልፈቀደችም ነበር።
እነዚህ ኤቲኤሲኤምኤስ ወይም The Army Tactical Missile System (ATACMS) በሚል የሚታወቁት የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን በመጠቀም ዩክሬን ሩሲያ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ባይደን መፍቀዳቸው ጦርነቱን ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።
አሜሪካ የአቋም ለውጥ ያደረገችው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሊገቡ ሁለት ወራት በቀራቸው ጊዜ ነው።
የትራምፕ መመረጥ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው የመሣሪያ ድጋፍ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

የፎቶው ባለመብት, shutterstock
አሜሪካ ለምን ሚሳኤሎቿ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቀደች?
ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ግዛቶቿ ውስጥ እነዚህን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ከአንድ ዓመት በላይ ተጠቅማለች።
የአሜሪካ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችም በሩሲያ ድንበር ኩርስክ አቅራቢያ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑ ተዘግቧል።
ሆኖም ግን እስካሁን አሜሪካ የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ሩሲያ ውስጥ ዒላማዎችን ለመምታት እንዲውሉ አልፈቀደችም።
እነዚህ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አለመፈቀዱ አንድን እጅ ወደ ኋላ አስሮ በአንድ እጅ ብቻ እንዲዋጉ የማድረግ ያህል ነው ብላለች።
በቅርቡ ሰሜን ኮርያ ወታደሮቿ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጦር ጋር ተሰልፈው በኩርስክ ግዛት ውስጥ እንዲዋጉ መላኳ ይታወሳል።
የአሜሪካ የፖሊሲ ለውጥም ይህንን ተከትሎ እንደመጣ ይታመናል።
ይህንን አካባቢ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ዩክሬን ተቆጣጥራዋለች።
የትራምፕ መመረጥ አሜሪካ በቀጣይ ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ ላይ ጥያቄ አጭሯል።
ባይደን በቀራቸው አጭር ጊዜ ለዩክሬን ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ የሚሹ ይመስላል።
የዩክሬንን ጦር ማጠንከር ለወደፊቱ የሰላም ንግግር ሲደረግ አብላጫ ሚና እንዲኖራት ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ስለ ጉዳዩ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጡም “ጥቃት የሚሰነዘረው በቃላት አይደለም። ሚሳኤሎቹ መልዕክቱን ያስተላልፋሉ” ብለዋል።

የረዥም ርቀት ሚሳኤል ምንድን ነው?
እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ የሚችል መሣሪያ ሲሆን፣ ለዩክሬን አስፈላጊ ነው።
ሎክሂድ ማርቲን በተባለው መሣሪያ አምራች ነው የተሠራው።
ኤም 270 በተባለው ሮኬት ተኳሽ ወይም ኤም 142 በሚባለው ሮኬት ተኳሽ መሣሪያ ሚሳኤሎቹን ማስወንጨፍ ይቻላል።
እያንዳንዱ የረዥም ርቀት ሚሳኤል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።
የረዥም ርቀት ሚሳኤል ከተወነጨፈ በኋላ ዒላማውን ሲመታ በከፍተኛ ኃይል ነው።
በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈንጂዎችን ይዞ መጓዝ የሚችል ሲሆን፣ ሰፊ ቦታ ላይ ያለ ዒላማን ይመታል።
ይህም የአየር መሣሪያ፣ የአየር መቃወሚያ ወይም ወታደሮችን ያካትታል።
ሳይፈነዱ የሚቀሩ ቦምቦች ተበትነው ሊቀሩ ስለሚችሉ፣ ውጊያው ከቆመ በኋላ ሊፈነዱ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል።
የረዥም ርቀት ሚሳኤሉ የሚሠራበት ሌላው መንገድ 225 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፈንጂ ይዞ ሰፊ ቦታ ላይ መውደቅ ነው።
መሣሪያው ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በአውሮፓውያኑ በ1991 በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት ነበር።
ይህንን መሣሪያ የአሜሪካ ጦር በዘመናዊ ዒላማ መቺ ሚሳኤል እየተካው ሲሆን ‘ፕሪሲሽን ስትራይክ ሚሳኤል’ የሚባሉት እነዚህ መሣሪያዎች በመጠን ያነሱ እና እስከ 500 ኪሎ ሜትር ሊጓዙ የሚችሉ ናቸው።
ዩክሬን እነዚህን መሣሪያዎች ስለማግኘቷ መረጃ የለም።
ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ ዒላማዎችን መምታት ትችላለች። በኩርስክ ግዛት ከ1,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የተያዘው በዩክሬን ወታደሮች ነው።
ዩክሬን እና አሜሪካ ሩሲያ በሰሜን ኮርያ ጦር በመታገዝ ግዛቱን ለመቆጣጠር መልሶ ማጥቃት እንደምታደርግ ይጠብቃሉ።
ዩክሬን ይህንን የረዥም ርቀት ሚሳኤል በመጠቀም ወታደራዊ መቀመጫ ወይም መሠረተ ልማት ልትመታ ትችላለች።
ይህ መሣሪያ ብቻውን የጦርነቱን አካሄድ አይለውጠውም።
ሩሲያ ይህንን ውሳኔ አስቀድማ እየጠበቀች ስለነበር የጦር ጄቶቿን ወደፊት አስጠግታ በተጠንቀቅ እየጠበቀች ትገኛለች።
ሩሲያ የጦር መሣሪያዎቿን ስታንቀሳቅስ መሸፈን ያለባት ሰፊ ቦታ በመሆኑ ወታደሮቿ ፈተና ይገጥማቸዋል። የአየር መሣሪያ በፍጥነት ለማድረስም ይከብዳል።
በሌላ በኩል የሩሲያ ጦር በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል የተሻለ እየገፋ ከመሄዱና የሕዝቡም ሞራል ከመዳከሙ አንጻር የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ዩክሬንን ይጠቅሟታል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በዩክሬን የሚገኙ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት፣ “የመጨረሻ ውጤት የሚያመጣ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ለዩክሬን ጦር ድጋፍን ያሳያል። ሩሲያ ለጦርነቱ የምታወጣውን ገንዘብንም ይጨምራል” ብለዋል።
በኦባማ አስተዳደር ወቅት የመከላከያ ምክትል ፀሐፊ የነበሩት ኤቭሊን ፋርክስ እንደሚሉት፣ ምን ያህል መሣሪያ ይሰጣል የሚለው አንድ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው።
“ምን ያህል ሚሳኤል ነው ያላቸው? የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን) ለዩክሬን የሚሰጥ ብዙም ሚሳኤል እንደሌለ ገልጿል” ይላሉ።
የረዥም ርቀት ሚሳኤል “በዩክሬን ላይ አወንታዊ የሥነ ልቦና ውጤት” እንዳለው ያስረዳሉ።
ክሬሚያን ከሩሲያ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ ሊመታ እንደሚችል ያክላሉ።
አሜሪካ መሣሪያዋ ጥቅም ላይ እንዲውል መፍቀዷ የዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ውሳኔ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል።
ጦርነቱ ይባባሳል?
ከዚህ ቀደም ግጭቱ እንዳይባባስ በሚል አሜሪካ በሚሳኤሎቿ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት እንዲፈጸም አልፈቀደችም ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን የምዕራባውያንን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች እንድትጠቀም መፈቀድ እንደሌለበት አስታውቀዋል።
ፈቃድ ከተሰጠ ግን “ሩሲያ በኔቶ አባላት እንደተቃጣ ቀጥተኛ የጦርነት ተሳትፎ” ትቆጥረዋለች ሲሉ ፑቲን አስጠንቅቀው ነበር።
“የጦርነቱን አካሄድ እና ሁኔታ ይለውጠዋል” ብለዋል ፑቲን።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ማኅበር (ኔቶ) አገራት፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ከሩሲያ ጋር “እየተዋጉ ነው” ተብሎ እንደሚወሰድ አክለዋል።
ሩሲያ ‘ቀይ መስመር’ የምትላቸው ለዩክሬን ዘመናዊ ታንክ እና ተዋጊ ጄት መለገስን ሲሆን፣ እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ለዩክሬን ከዚህ ቀደም ሲሰጡ በሩሲያ እና በኔቶ አባል አገራት መካከል ቀጥተኛ ግጭት አልተነሳም።
በኔቶ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ከርት ቮልከር፣ “አሜሪካ ዩክሬን ጥቅም ላይ ማዋል የምትችላቸውን መሣሪያዎች በመገደብ የዩክሬንን ራሷን የመከላከል አቅም ውስን አድርጋው ነበር” ይላሉ።
የረዥም ርቀት ሚሳኤልን ዩክሬን እንዳትጠቀም የተወሰነው ‘ሩሲያን ላለማስቆጣት’ ነበር ሲሉም ያክላሉ።
“ሆኖም ግን እንዲህ ያለውን የሐሳብ ለውጥ በአደባባይ መናገር ስህተት ነው። ሩሲያ የዩክሬንን ጥቃት ቀድማ ለመከላከል እንድትዘጋጅ ያስችላል” በማለትም ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, shutterstock
የትራምፕ መመረጥ ምን ይለውጣል?
ትራምፕ ከሁለት ወራት በኋላ ዋይት ሐውስ በመግባት የአሜሪካንን የመሪነት መንበር ይረከባሉ።
የዩክሬንን ጦርነት በአፋጣኝ እንደሚያቆሙ ደጋግመው ተናግረዋል።
እንዴት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ትራምፕ በዝርዝር አልተናገሩም። ሚሳኤልን ጥቅም ላይ የማዋል ውሳኔን ሊቀለብሱ ይችላሉ።
ትራምፕ ፖሊሲውን ስለማስቀጠል ያሉት ነገር ባይኖርም የቅርብ አጋሮቻቸው ፖሊሲውን ተችተዋል።
የትራምፕ ልጅ ትራምፕ ጁኒየር “አባቴ ሰላም አስፍኖ ሕይወት ከማዳኑ በፊት መሣሪያ አምራቾች ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንዲጀመር የፈለጉ ይመስላል” ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፏል።
የትራምፕ ምክትል ጄዲ ቫንስን ጨምሮ ሌሎችም አጋሮቻቸው አሜሪካ ከዚህ በኋላ ለዩክሬን መሣሪያ እንድትሰጥ አይፈልጉም።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ዋልዝ በተቃራኒው አሜሪካ ለዩክሬን በፍጥነት የጦር መሣሪያ በመስጠት ሩሲያ ወደ ድርድር እንድትገባ ጫና ማሳደር ትችላለች ሲሉ ይከራከራሉ።
ትራምፕ ምን ሊወስኑ እንደሚችሉ አይታወቅም።
ሆኖም የረዥም ርቀት ሚሳኤልን ጨምሮ ሌሎችም መሣሪያዎች ለዩክሬን እንዳይላኩ ሊያግዱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዩክሬን የሕዝብ እንደራሴ ኦሌክሲ ጎንቻርንኮ “ተጨንቀናል። ትራምፕ ውሳኔውን አይቀለብሱትም ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።













