ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ጦርነት በትራምፕ ዘመነ ሥልጣን ‘በፍጥነት ይቋጫል’ አሉ

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በትራምፕ ዘመነ መንግሥት ከሩሲያ ጋር ያለው ጦርነት “በፍጥነት እንደሚቋጭ” እርግጠኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

ዜሌንስኪ ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ “ገንቢ ውይይት” ማካሄዳቸውን ገልፀዋል።

ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ሊደረግ ስለሚችል ንግግር የተለየ ቅድመ ሁኔታ ስለማቅረባቸው ባይናገሩም የትራምፕ አቋም ከዩክሬን ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል።

ትራምፕ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ጦርነቱን ማስቆም እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ሩሲያ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ነው ዩክሬንን የወረረችው።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የዩክሬኑ ጦርነት የአሜሪካን አቅም እያሟጠጠ ነው ሲሉ ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን እርዳታ ይተቻሉ።

ከወራት በፊት የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ማፀደቁ የሚታወስ ነው።

አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ከሚያቀርቡ ሀገራት ቁንጮዋ ስትሆን ከጦርነቱ ጅማሬ እስካሁን 55 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ መሣሪያ ልካለች።

ነገር ግን በተለይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች የሆኑ አሜሪካዊያን ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ይነቅፋሉ።

ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት በተደጋጋሚ የዩክሬኑን ጦርነት “በአንድ ቀን” እንደሚቋጩት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ቢሆንም ይህን እንዴት እንደሚያሳኩት ያሉት ነገር የለም።

“አሁን ወደ ዋይት ሐውስ በሚገባው ቡድን ፖሊሲ መሠረት ጦርነቱ በፍጥነት እንደሚቋጭ እርግጠኛ ነኝ። ይህ ለዜጎቻቸውም የገቡት ቃል ነው” ሲሉ ዜሌንስኪ ሰስፕላይን ከተሰኘው የዩክሬን ሚድያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ተናግረዋል።

አክለው “ዩክሬን ጦርነት በሚመጣው [የፈረንጆቹ] ዓመት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሚቻላትን ሁሉ ማድረግ አለባት” ብለዋል።

ትራምፕ እና ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያ ወታደሮች በጦርነቱ በርካታ አውድማዎችን እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ። ዩክሬን በ2023 ያወጀችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የታሰበለትን ግብ ሳይመታ ቀርቷል።

የሩሲያ ወታደሮች በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን ያሉ ቦታዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን አሁን በዋናነት ጦርነት እየተካሄደበት ያለበት ሥፍራ ምስራቃዊ ዶንባስ ነው።

አርብ ዕለት የሩሲያ ወታደሮች በምስራቁ ግንባር ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ወደፊት መግፋታቸውን ኢንስቲትዩት ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ዋር የተባለ የዋሺንግተን ዲሲ ተቋም አስታውቋል።

ባለፈው ክረምት የዩክሬን ወታደሮች ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው ይታወሳል። የዩክሬን ወታሮች ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ሩሲያ ምድር የገቡ የመጀመሪያዎቹ የውጭ ኃይሎች ሆነዋል።

ዜሌንስኪ ይህን ያደረግነው የሩሲያ ኃይሎች ከዩክሬን እንዲያፈገፍጉ ለማድረግ ነው ቢሉም ዘመቻው ውጤታማ መሆኑ ግን አጠራጣሪ ነው።

ሩሲያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አሰልፋ እየተዋጋች ሲሆን በተነፃፃሪ ጥቂት ወታደሮች ያሏት ዩክሬን ከምዕራባዊያን በሚቀርቡላት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ላይ ጥገኛ ናት።

ዜሌንስኪ በተደጋጋሚ የዩክሬን ግዛቶች እስካልተመለሱ ድረስ ለንግግር እንደማይቀመጡ ሲያስታውቁ ቆይተዋል። እሳቸው እንደሚሉት በአውሮፓውያኑ 2014 በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ክሬሚያም መመለስ አለባት።

ምንም እንኳ ትራምፕ እና ዜሌንስኪ ያላቸው ግንኙነት በውጣ ውረድ የታጀብ ቢሆን ተመራጩ ፕሬዝደንት ግን ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም እንደሆነ ይናገራሉ።

የትራምፕ ተቃዋሚ የሆኑ ዲሞክራቶች ግን ተመራጩ ፕሬዝደንት በጦርነቱ ዙሪያ ያላቸው አቋም ዩክሬን ራሷን አሳልፋ እንድትሰጥ የሚያደርግ ነው በማለት ለሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ስሱ አመለካከት አላቸው ሲሉ ይወቅሷቸዋል።

ትራምፕ ምርጫ ካሸነፉ ከቀናት በኋላ ከፑቲን ጋር የስልክ ልውውጥ አድርገዋል፤ በውይይታቸውም ትራምፕ ግጭቱ እንዳይካረር ፑቲንን አስጠንቅቀዋቸዋል የሚል ዘገባ መወጣቱን ሩሲያ አስተባብለለች።