የማልኮም ኤክስ ቤተሰብ ኤፍቢአይ፣ ሲአይኤ እና የኒው ዮርክ ፖሊስን ከሰሰ

ማልኮም ኤክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማልኮም ኤክስ በ39 ዓመቱ ነው የተገደለው

የጥቁሮች ሰብዓዊ መብት ተሟጋች የነበረው ማልኮም ኤክስ ቤተሰብ ኤፍቢአይ፣ ሲአይኤ እና የኒው ዮርክ ፖሊስ ላይ ክስ መሥርቷል።

የስለላ እና የፀጥታ መሥሪያ ቤቶቹ በማልኮም ኤክስ ግድያ እጃቸው ስላለበት የ100 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈል ነው የተሟጋቹ ቤተሰብ የጠየቀው።

የክስ መዝገቡ መሥሪያ ቤቶቹ በግድያው ሤራ ተሳትፈዋል እንዲሁም ግድያውን ማስቆም ሳይችሉ ቀርተዋል ይላል።

“እኛ እንደምናምነው ሁሉም በማልኮም ኤክስ ግድያ ዙሪያ እጃቸው አለበት። ማልኮም ኤክስ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከታዩ እጅግ ድንቅ መሪዎች አንዱ ነበር” ሲሉ ቤተሰቡን የወከሉት ጠበቃ ቤን ክራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ማልኮም ኤክስ በአውሮፓውያኑ 1965 ነው የተገደለው። ኒው ዮርክ ውስጥ ንግግር ሊያደርግ እየተዘጋጀ ሳለ ነው ሶስት የታጠቁ ሰዎች መጥተው 21 ጊዜ በጥይት መትተው የገደሉት።

የክስ መዝገቡ በመሥሪያ ቤቶቹ መካከል “ሙሰኛ፣ ሕግ አልባ እና ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ” ግንኙነት ነበር። ይህ ደግሞ “ጨካኞቹ ገዳዮች” ድርጊቱን እንዲፈፅሙ ፈቅዶላቸዋል ይላል።

“ለዘመናት በገዳዮቹ እና በመሥሪያ ቤቶቹ መካከል ያለው ግንኙነት ሳይጣራ ቆይቷል። በየጊዜው ይህ ሚስጢር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጥበቃ ሲደረግለት ነው የቆየው” ይላል የክስ መዝገቡ።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ጣቢያ ከሌሎቹ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ከግድያው ከቀናት በፊት የማልኮም ኤክስን ጠባቂዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል፤ አልፎም ንግግድ ከሚደረግበት አዳራሽ ፖሊሶችን አስወጥቷል የሚል ክስ ተካቷል።

በድብቅ የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ የፌዴራል የደኅንነት ሰዎች በግድያው ወቅት በአዳራሹ ውስጥ ነበሩ፤ ነገር ግን ጣልቃ ሳይገቡ ቀርተዋል ሲል ቤተሰቡ ክሱን አቅርቧል።

የማልኮም ኤክስ ቤተሰብ ባለፈው ዓመት ነበር እኒህን መሥሪያ ቤቶች እንደሚከስ ያስታወቀው።

የኒው ዮርክ ፖሊስ “በቀረበው ክስ ዙሪያ አስተያየት አንሰጥም” ያለ ሲሆን ሲአይኤ እስካሁን ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። ኤፍቢአይ በበኩሉ በመሰል የክስ ጉዳዮች ላይ ምላሽ አለመስጠት “የተለመደ ነው” ሲል አሶሲየትድ ፕሬስ ለተሰኘው የዜና ወኪል ተናግሯል።

ማልኮም ኤክስ የኔሽን ኦፍ ኢስላም ቁጥር አንድ አቀንቃኝ ነበር። ኔሽን ኦፍ ኢስላም ጥቁር አሜሪካዊያን ከነጮቹ መገንጠል አለባቸው ብሎ የሚያምን ተቋም ነው። ነገር ግን ከመገደሉ በፊት ባሉት ዓመታት ራሱን ከኔሽን ኦፍ ኦስላም አግልሎ ነበር።

ማልኮም ኤክስ በ39 ዓመቱ ነው የተገደለው።

በአውሮፓውያኑ 2021 በማልኮም ኤክስ ግድያ ምክንያት ለዓመታት እስር ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች መለቀቃቸው ይታወሳል። የኒው ዮርክ ቀጣናዊ ፍርድ ቤት ዳኛ የፍትሕ መዛባት ነበር በሚል ነው ሁለቱ ሰዎች በነፃ እንዲለቀቁ የወሰኑት።

የኒው ዮርክ አቃቤ ሕግ ሁለቱ ግለሰቦች ነፃ ሊያደርጋቸው የሚችል ማስረጃ እያለ ነገር ግን ለችሎት አልቀረበም በሚል ሁለቱ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው ብሏል።

በሐሰት ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች ቤተሰቦች ኒው ዮርክ ከተማን ከሰው የ26 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ያገኙ ሲሆን ከኒው ዮርክ ግዛት ደግሞ የ10 ሚሊዮን ካሳ ተከፍሏቸዋል።