የላጤዎች ጉባኤ በቦሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንጅ አፍ ‘ስፒድ ዴቲንግ’ ይባላል። የአማርኛ አቻ የለውም። በአቋራጭ መተጫጨት ነው-ነገሩ። ፖለቲካዊ ቋንቋ ይመስልብናል እንጂ ‘የትዳር ማሳለጫ’ እንለው ነበር።
‘አጭሬ ጅንጀና’ ያሉትም አሉ።
ያም ተባለ ይህ፣ ነገሩ ‘የፍቅር-ጉድኝት’ ለመፍጠር የሚደረግ አጭር ጉዞ ነው። የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት አደን እንደመውጣት ያለ ነው። የትዳር አሰሳ፣ የፍቅር አፈሳ ነው።
የወደፊት ውሃ አጣጭን ለማማለል የሚሰጥ የአምስት ደቂቃ ፍጹም ቅጣት ምት ነው።
ወንዝ መውረድ፣ እንሥራ መስበር አይፈልግም። በይነ መረብ ማሰስ፣ ደብል ክሊክ ማድረግ አይኖርም።
ስፒድ ዴቲንግ በአጭር ቀጠሮ የሚደረግ ድንገቴ ትውውቅ ነው።
የሚዘወተረው በላጤዎች ነው። ፈቶች የሉበትም ማለት ግን አይደለም።
የሚሰናዳው በካፌ እና በሬስቶራንት ነው፤ አልያም በቡና ቤት። ቡና ቤት ስንል ታዲያ ‘ባር እና ላውንጅ’ ማለታችን ነው።
ባሕሉ ለኢትዮጵያ አዲስ ይመስላል። በውጭ ዓለም ግን የተለመደ ነው። ብዙ ባተሌ ፈረንጅ ውሃ አጣጪውን ያገኘው በዚህ ዘዴ ሳይሆን አይቀርም።
በፈረንጅ አገር በቤተሰብ መተጫጨት የለማ። ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ብሎ ነገር አያውቁማ። ጊዜ ወስዶ ለመጠናናት የሕይወት ሩጫ አይፈቅድማ!
ስለዚህ ስፒድ ዴቲንግን ፈጠሩ።
ጊዜ በተትረፈረፈባት ኢትዮጵያ ታዲያ ይሄ ነገር ምን ይሠራል?
የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።
በ5 ደቂቃ ሰውን ማወቅ ይቻላል?
ነገሩ እንዲህ ነው።
ላጢት እና ላጤው፣ ጭራሽ ተያይተው የማያውቁ፣ ወደውና ፈቅደው ድንገት በአንድ ሥፍራ ለ‘ፍቅር ጉባኤ’ ይታደማሉ።
ለአምስት ደቂቃ ብቻ።
አንድ ቡና ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል። ‘ቡና ቤት’ ስንል ቸበርቻቻ ያለበት ማንኛውም መዝናኛ ስፍራ ማለታችን ነው።
የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ይታወጃል። 10 ወንበሮች ግራና ቀኝ ይደረደራሉ። መሀል ላይ ጠረጴዛ ይጋደማል።
ላጤ ሴቶች ከቦታቸው አይነሱም። ላጤ ወንዶች ግን ላጤ ሴቶቹን ይዞሯቸዋል። ይንከባከቧቸዋል። ሊያማሏቸው ይሞክራሉ። ግን ‘ለመለፋደድ’ ጊዜ የለም።
ጨዋ እና ቁጥብ፣ እንደገና ደግሞ ተጫዋች እና ለዛ ያለው ሰው መሆን ይፈልጋል።
ወንዶቹ ከአንዲት ሴት ጋር ለ5 ደቂቃው እያወጉ ይነሳሉ። ተነስተው ደግሞ ወደ ሌላኛዋ ሴት ይሄዳሉ።
ዘጠኝ ፕላኔቶች ፀሐይን እንደሚሽከረከሯት 10 ወንደ ላጤዎች፣ 10 ሴተ ላጤዎችን ይዞሯቸዋል። ፕላኔቶች ቁጥራቸው ስንት ደረሰ?
እሽክሪቱ ሲያበቃ ነገሩ ያበቃል። ይኸው ነው። ‘ስፒድ ዴቲንግ’ ያሉት ለዚህ ይሆናል። ፈጣን ስለሆነ።
በዚያች ደቂቃ ላጤው እና ላጢት የሆነች የመጣጣም ብልጭታ ካዩ ትዳር ሰመረ ይባላል።
በእርግጥ መፈላለጉ የግድ ለትዳር መሆን የለበትም። ለወዳጅነትም በቂ ነው። እንዲያው ለጨዋታው ነው እንጂ ትዳር በኋላ የሚመጣ ነገር ነው።
ይህ የ5 ደቂቃ ‘የአጠሬራ’ መጠናናት፣ ፈረንጅ ‘ሰፒድ ዴቲንግ’ ይለዋል። እኛ ለዚህ ጽሑፍ ምቾት ስንል ‘የላጤዎች ጉባኤ’ እንለዋለን።
የሆነስ ሆነና ሰውን የሚያህል ውስብስብ ፍጥረት በ5 ደቂቃ ማወቅ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Lucy Fragrances
ከኢትዮጵያ ባሕል ያፈነገጠ ነው ይላሉ
ከአንድ ዓመት በፊት ይህንኑ አጀንዳ ወደ ትዊተር ሰሌዳዋ አምጥታ ያወያየች አንዲት ዕውቅ ኢትዮጵያዊት ነበረች። ያን ዕለት አስተያየት መስጫዋ በግራ እና ቀኝ ሐሳቦች ሲላጋ ዋለ።
“በጭራሽ! ይሄ ከባሕላችን ያፈነገጠ ነው፤ የምዕራቡን ቅራንቅንቦ እያመጣችሁ አትዘርግፉብን” ከሚል ቁጡ ወግ አጥባቂ ዜጋ ጀምሮ፣ “ጥሩ ባህል ነው፤ በእኛም አገር ሊለመድ ይገባል” እስከሚል ሆደ ሰፊ ተስተናገደ።
በተለይ ሴት አስተያየት ሰጪዎች ‘የላጤ ጉባኤ’ ቢኖር- ቢጀመር-ምናለበት? ሲሉ አበረታቱ። መሳተፍ እንደሚሹም ተናገሩ።
ሐሳባቸውን ካጋሩት መካከል ‘የላጤ ጉባኤን’ የመሰለ፣ ነገር መንፈሳዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ በፕሮቴስታንት ቸርቾች አካባቢ እንደሚዘወተር ፍንጭ ሰጡ።
በዚህ የትዊተር ዥረት (Thread) ፈገግ የሚያሰኙ አስተያየቶችም ተንጸባርቀዋል።
ለምሳሌ፡ “ሐበሻ የራሺያ ካውያ ነው፣ በስፒድ ዴቲንግ ቶሎ አይግልም” ያሉ ነበሩ።
“ሐበሻን ማወቅ ጨጓራ እንደማጠብ ነው፤ ትዕግሥት ይጠይቃል” በማለት አይደለም 5 ደቂቃ 5 ዓመት በቂ አይደለም ያሉ ነበሩ።
አሁን አገር እየነደደ ስለ ስፒድ ዴቲንግ የምንወያይበት ጊዜ ላይ ነን? ሲሉ የገሰጹም የትዊተር ሠራዊት አባላት አልጠፉም።
የሆነስ ሆነና ይሄን ነገር፣ በአገር ቤት የሞከረው ሰው አለ?
‘ስፒድ ዴቲንግ’ በኢትዮጵያ ተሞክሯል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የፍቅር ጉባኤ ከሚያሰናዱት መሀል “አትሞስፌር ባርና ሬስቶራንት” ይገኝበታል። ቦሌ ከዓለም ሲኒማ ጀርባ ነው ያለው።
የካሪኦኪ (karaoke) መሰናዶ አላቸው። ኬሪኦኪ ታዳሚ ማይክራፎን ጨብጦ ያሻውን ሙዚቃ የሚዘፍንበት (ወይም የሚያንቋርርበት) አዝናኝ ተግባር ነው።
ደንበኞቻቸውን የሚያዝናኑበት የተለያዩ ዝግጅቶች ቢኖሯቸውም ‘ስፒድ ዴቲንግ’ የጀመሩት ግን በቅርቡ ነው። ሦስት ወር ቢሆነው ነው።
ገና ከመጀመሩ ግን “በደንበኞቻችን ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ነው ያገኘነው” ትላለች ሐና። እርሷ በድርጅቱ የኩነቶች ዋና አስተባባሪ ናት።
“ነገሩን የማውቀው በፊልም ነበር። ለምን አንሞክውም ብለን አሰብን” ትላለች።
እነ ሐና ከኩነቱ በፊት ነገሩ ምን እንደሆነ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ማስተዋወቅ ነበረባቸው። ከዚያ ደግሞ ምዝገባ አደረጉ።
የጨዋታውን ሕግ ደነገጉ። ስልክ ይዞ መግባት ከለከሉ። የ5 ደቂቃ ሕግ ወጣ። የፍቅር ፊሽካ ተነፋ።
“ወንዶቹ ሰዓት ይጨመርልን ይሉናል፤ እኛ ግን አንጨምርላቸውም” ትላለች ሐና እየሳቀች።
ከ5 ደቂቃ ትውውቅ በኋላ ሴቶቹ ቀልባቸው ያረፈበት ወንድ ካለ ስልኩ ይሰጣቸውና በ5 ደቂቃ የተለኮሰውን ችቦ እንዲያቀጣጥሉ ተባርከው ይሸኛሉ።
ሐና እንዳስተዋለችው ሴቶች በብዛት ሁለት-ሦስት ሆነው ነው ወደዚህ መሳናዶ የሚመጡት። ምናልባት በሥነ ልቦና ለመደጋገፍ ይሆናል።
ያም ሆኖ መቀመጥ የሚችሉት በተናጥል እንጂ በቡድን አይደለም።
አትሞስፌር ደንበኞቹን ለስፒድ ዴቲንግ እንደማያስከፍል ሐና ነግራናለች።
“አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ተመዝግበው ባለቀ ሰዓት የሚቀሩ ያጋጥሙናል’’ ትላለች ሐና፤ ምናልባት የወግ አጥባቂነት ባህሉ ባለቀ ሰዓት እየተጫናቸው ይሆናል።
“አንዳንድ ጊዜ 5 ደቂቃው ካለቀ በኋላ ወንበር ቀይረው እዚያው እያወሩ ቀልጠው የሚቀሩም አሉ። ሥራውን ያቀሉልናል” ትላለች ሐና እየሳቀች።
ለዚህ መሰናዶ የወጣ፣ ምክር ቤቱ ያጸደቀው የአለባበስ ደንብ የለም።
ሐና እንዲህ ትላለች፣ “በነጠላ ጫማና በፒጃማ አይምጡብን እንጂ ብዙም አንጫናቸውም፤ ነጻነት እንዲሰማቸው ነው የምንፈልገው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ወንዶች ናቸው እየተሽኮረመሙ ያስቸገሩን”
አትሞስፌር ብቻ አይደለም ይህን ነገር የሞከረው። ስፒድ ዴቲንግ በቦሌ ቢገባም ቡልቡላ ለመድረስ ጊዜ አልፈጀበትም።
ሰናይት ዳንኤል ከቢዝነስ አጋሯ ጋር የመሠረተችው ‘ሉሲ ፍሬግራንስስ’ (Lucy Fragrances) ይህን የላጤ ጉባኤ ቦሌ ቡልቡላ በሚገኝ አንድ መድረክ ላይ አሰናድቶታል። ወርሃዊ መርሐ ግብር ነበር።
አሁን በአዲስ መልክ ሊጀምሩት ከቡልቡላ ወደ ቦሌ ሄደዋል።
ዋናው ሥራችን የሽቶ ምርት ቢሆንም ‘ስፒድ ዴቲንግ’ ማሰናዳት ከጀመርን ቆይተናል ትላለች ሰናይት።
በመርሐ ግብሩ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ አዲሳ'ባ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች (Expats) ፍላጎት እንዳሳዩ ለቢቢሲ ተናግራለች።
እነ ሰናይት መጀመሪያ አካባቢ ኩነቱን ለአዲስ አበቤ ለማስተዋወቅ ተቸግረው ነበር። ነገር ግን ሰው ቶሎ ነው የተቀበለን ትላለች።
ገና እንደተዋወቀ ሴቶችም ወንዶችም በጥያቄ አዋክበዋቸዋል። ይህ የሆነው ነገሩን ገና በማኅበራዊ ሚዲያ ማስተዋወቅ በጀመሩበት ቅጽበት ነው።
“ምንድነው ደግሞ 'ስፒዴ ዴቲንግ?'፣ 'ማን ነው የሚመጣው?'፣ 'ምን ይዘን ነው የምንመጣው?'፣'ምን እልበስ? የግድ መዘነጥ አለብን? ወዘተ...”
የማያባሩት ጥያቆዎች የሚዥጎደጎዱት ደግሞ በውስጥ መስመር እንጂ በሐሳብ መስጫው አይደለም።
ከጥያቄዎቹ በመነሳት እነ ሰናይት ኩነቱን የፍቅር ግንኙነት ክብሪት መለኮሻ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም አዲስ ሰው መተዋወቂያ መድረክ አድርገው ማስተዋወቅን መረጡ።
“ያንን ያደረግነው በተለይ ሴቶች ፍቅረኛ ፍለጋ መሆኑን ሲረዱ ሊፈሩና ሊያፍሩ ስለሚችሉ ነው” ትላለች ሰናይት።
ይህ ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ገደብም ጥለው ነበር። የተሳታፊዎችን ዝቅተኛ ዕድሜ 25 እንዲሆን ደነገጉ።
“ወጣቶች ነገሩን ለሌላ ነገር እንዳይጠቀሙበት ስለሰጋን ነው” ትላለች ሰናይት።
በመጨረሻ ቅድሚያ የተመዘገቡ 10 ወንዶች እና 10 ሴቶች ዕድሉ ተሰጣቸው።
በጽጌረዳ አበባ እና መዓዛው በሚያውድ ሻማ ያሸበረቀው ክፍል ውስጥ ገቡ።
ጠረጴዛዎቹ ላይ የወይን መጠጥ ተቀመጠ። ቆንጆ ለስላሳ የፍቅር ሙዚቃ ተከፈተ።
ላጤዎቹ ማውጋት ጀመሩ። ተሳሳቁ። ተጠናኑ። ለ7 ደቂቃ ብቻ።
ወንዶቹ ከወንበራቸው እየተነሱ ዐሥሩን ሴቶች ተዋወቋቸው።
እነ ሰናይት በዚህ ሁሉ ጊዜ ከፍርሃታቸው አልተላቀቁም። የመጀመሪያቸው ስለሆነ ኩነቱ ምንም ዓይነት እንቅፋት እንዲገጥመው አልፈለጉም።
ምናልባት ጥንዶቹ ተፋፍረው ወሬ ቢያልቅባቸውስ ብለው የሰጉት እነ ሰናይት በጥንዶቹ ጠረጴዛ ላይ ወሬ ማጣፈጫ የያዘ ካርድ አስቀምጠውላቸው ነበር።
ለምሳሌ፡ ለጓደኝነት/ለግንኙነት ወሳኝ ነው የምትሉት ጉዳይ ምንድን ነው? የሚል ዓይነት።
ሰናይት የሴቶችን መሸበር አስተውላለች።
ብዙ ሴቶች ለስፒድ ዴቲንግ መምጣት መንሰፍሰፍ/መጓጓት ስለሚመስላቸው ይጨነቃሉ።
ለምሳሌ ሴቶቹ ደበቅ ሸሸግ ያለ ቦታ ነው የሚፈልጉት። በሻማ ብርሃን ብቻ፤ ማንነታቸው እንዳይለይ።
“ፎቶ ልናነሳ ስንል ተቆጡን፣ እኛ ለማስታወቂያ እንዲሆነን ነበር የፈለግነው” ስትል ሰናይት በመጀመሪያው ዝግጅት ዕለት የገጠማትን ያልተጠበቀ ነገር ታስታውሳለች።
እነ ሰናይት ለዚህ ዝግጅት ምዝገባ ሲጀምሩ አንድ ነገር አስፈርቷቸው ነበር።
ምናልባት ወንዶች ብቻ ቢመጡና ሴቶቹ ፈርተው ቢቀሩስ የሚል።
ምን ይውጠናል የሚለው ሲያባንናቸው ነበር የቆየው።
ቀኑ ሲደርስ የተገላቢጦሽ ሆነ። ወንዶች አነሱ። ሴቶች በዙ።
“እንዲያውም ወንዶቹ ናቸው እየተሽኮረመሙ ያስገሩን” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Lissy Cleminson
ከፍቅር አሰናኝ መተግበሪያ በምን ይለያል?
ባሕል ቶሎ ቶሎ እየተቀየረ ነው። እየተቀየጠም ነው። የሩቅ የሚባል ባሕል እየጠፋም ነው። የኛ የሚባል ባሕልስ ወደፊት ይኖር ይሆን?
የእንስራ መስበር ዘመን ተሸኝቶ፣ የሰፈር ልዝብ ትንኮሳም አከርካሪው ተመቶ፤ የሎሚ ውርወራ ዘመን ‘በምብል’ እና ‘ቲንደር’ እየተካው ነው።
‘ልጅዎን ለልጄ’ ሥርዓት እየጠፋም - እየመጣም ይመስላል፤ ሄድ-መለስ ነገር።
ወደፊት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ባህሪያችንን ጥንቅቅ አድርጎ ተረድቶ ብረት መዝጊያ የምትሆን ሚስት ወይም ባል ሊያመጣልንም ይችላል።
ማን ያውቃል?. . .
ይህ የላጤዎች ጉባኤ ከስውር ትውውቅ (Blind date) እና የፍቅር አሰናኝ መተግበሪያ (Dating app) ይለያል።
በስልክ መተግበሪያ ውሃ አጣጪን መቅዳት የልብ አያደርስም ይላሉ፤ ብዙ ወጣቶች እና ጎልማሶች።
የመተግበሪያ ትውውቅ ሰው-ሰው አይልም። የልብ አይደርስም። የፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎች የቀላልነታቸውን ያህል ከባድም ናቸው።
ልብ ያዝላል። ምርጫው ያ’ይን አዋጅ ነው። በጽሑፍ መልዕክት መፋተግ - የጉልበት ሥራ ያህል አድካሚ ነው።
በዚህ የስልክ ግንኙነት ሂደት ያለፉ ሴቶች - ወንዶችን “የልብ ካውያዎች ናቸው” ይሏቸዋል፤ አታካችነታቸውን ለመግለጽ።
ከሁሉም በላይ አስከፊው ነገር ደግሞ ሰዎች በበይነ መረብ ውስጥ ሌላ ማንነት ይላበሳሉ። በአካል ሲገኙ ግልባጩን ይሆናሉ. . . ፎቶ ያታልላል።
ስፒድ ዴቲንግ - ላጤዎች ጉባኤ የተሻለ የሚሆነው በዚህ በዚህ ነው። ‘ፍቅር ባ’ይን ይገባል’ እንደሚባለው።
እርግጥ ነው ሰውን ለማወቅ 5 ደቂቃ በቂ ላይሆን ይችላል። ልብ ለመደንገጥ ግን 5 ሴኮንድም ሲበዛበት ነው።
ምናልባት ያቺ 5 ደቂቃ ፍቅርን-ትዳርን-ልጅን በአጠቃላይ ቤተሰብ ምሥረታን ልታስከትል ትችል ይሆናል። ማን ያውቃል?
ምናልባት ቻይና ታውቃለች።
የፈረንሳዩ ለ-ሞንድ መጽሔት በቅርቡ አንድ አስገራሚ ዘገባ አስነብቦ ነበር።
የቻይና መንግሥት የሕዝብ ቁጥር መመናመን አሳሰበው። ወጣት ዜጎቹ ለፍቅር-ዋዛ-ፈዛዛ ጊዜ እንደሌላቸው ተረዳ። ይሄኔ መላ መታ።
ከብዙ መብሰልሰል በኋላ የዢ ጂንፒንግ መንግሥት ዜጎቹ ተፋቅረው እንዲጋቡ እና ልጅም እንዲወልዱ እንደ አቅጣጫ ያስቀመጠው ‘ስፒድ ዴቲንግ’ን ነው። የላጤ ጉባኤ በአስቸኳይ ይጀመር ተባለ።
ይሄ ቀልድ አይደለም።
ጉዳዩን እንዲያሳልጡ የኮሚኒስት የወጣቶች ሊግ እና የቻይና የሴቶች ፌዴሬሽን አደራ ተባሉ።
እነሱም አደራውን ተቀብለው ቻይናዊት ላጢት እና ቻይናዊት ላጤን በቅልጡፍ የፍቅር ጎዳና (Speed Dating) ያስተሳሰሩ ጀመር።
ይነስም ይብዛ ሠርቶላቸዋል። የለ-ሞንድ ዘገባ እንደሚለው ፍቅርም ትዳሩም አሁን በፍጥነት እየተሳለጠ ነው። ልክ ቻይናዎቹ እንደ ሚገነቡት ማሳለጫ።
ይሄ ነገር ለኢትዮጵያ ይሠራል?












