ስመጥር ራፐሮችን ከሞት ለመታደግ ተዘጋጅቶ የነበረው ምሥጢራዊው ስብሰባ

ቱፓክ ሻኩር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓውያኑ 1996 የተገደለው ቱፓክ ሻኩር

በ1990ዎቹ የአሜሪካ የራፕ ሙዚቀኞች ኢስት ኮስት እና ዌስት ኮስት በሚል ለሁለት ተከፍለው ቃላትን የሚወራወሩበት ጊዜ ነበር። ከቃል በላይ የደረሰው ግብግብ የቱፓክ ሻኩር እና የኖቶሪየስ ቢአይጂን ሕይወት እስከመቅጠፍም ደርሷል።

ሂፕ-ሆፕ በ1990ዎቹ ነበር የአድማጮችን ጆሮ መያዝ ጀመረው። ሙዚቀኞቹ ግን በልምድ የሚያውቁትን ይዘው ከመውጣት ውጪ በዘርፉ አርአያ የሚሆናቸው አልነበረም።

አንድ ግለሰብ ግን ነበራቸው። ሰውየው የሚችለውን ለማድረግም ሞክሯል።

ይህ እንደሚመጣ ቀድሞ ያወቀው ኩዊንሲ ጆንስ አንድ ምሥጢራዊ ስብሰባ በማዘጋጀት እሳቱን ለማርገብ ሞክሮ ነበር።

ኩዊንሲ ጆንስ ይባላል። የ‘ጋንግ’ አባል ነበር። በሰባት ዓመቱ ቺካጎ ውስጥ በስለት እስከመወጋት ደርሷል። በኋላ ግን ስሙን በአሜሪካ ሙዚቃ ውስጥ በደማቁ ለመጻፍ በቃ። ሬይ ቻርልስ፣ ፍራንክ ሲናትራ እና ማይክል ጃክሰን አሻራውን ካሳረፈባቸው ከዋክብት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ጃዝ፣ ስዊንግ፣ ሶል፣ ፈንክ፣ ዲስኮ እና ፖፕ በተሰኙት የሙዚቃ ዘርፎች አብዮት ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው።

ጆንስ በ91 ዓመቱ በቅርቡ ሕይወቱ አልፏል። በስፋት ስሙ የሚነሳበት ጉዳይም በሙዚቃው ዓለም ስለፈጠረው ተጽእኖ ነው። አንድ ሚናው ግን ተገቢውን ትኩረት አላገኘም።

ኩዊንሲ ጆንስ እና ፋብ 5 ፍሬዲ

የፎቶው ባለመብት, Madison McGaw/BFA.com/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ኩዊንሲ ጆንስ እና ፋብ 5 ፍሬዲ

ጆንስ የሚለው ስም ራፕን ጨምሮ በሁሉም የሙዚቃ ዘርፎች የተከበረ ነው። ቀደም ያሉት ትውልዶችም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን ያላዩትን አንድ ጉዳይ ለመመልከት ቻለ።

በሂፕ-ሆፕ እና በወጣትነቱ ገናና በነበረው ቢቦፕ ጃዝ መካከል ያለውመመሳሰል ታወቀው። “በብዙ ነገሮች ውስጥ ስላለፍን ተመሳሳይነት እንዳለ ተረዳሁኝ” ብሏል።

“ኩዊንሲ መረዳት ብቻ ሳይሆን ወዲያው አውቆታል” ሲል ራፐሩ እና የሬዲዮ አቅራቢው ፋብ 5 ፍሬዲ ተናግሯል።

ኩዊንሲ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ከበርካታ ስመጥር ራፐሮች ጋር ሠርቷል። ይህ ደግሞ በሙዚቀኞቹ ብቻ ሳይሆን በአሳታሚዎቻቸው መካከል እየተቀጣጠለ ያለ አደጋ መኖሩን እንዲገነዘብ ረድቶታል።

ይህን አደጋ ይቀለብሳል በሚል በ1995 ሙዚቀኞችን፣ አሳታሚዎችን እና በጥቁሩ ማኅበረሰብ ስም ተደማጭ የሆኑ ሰዎችን ለምሥጢራዊ ስብሰባ ጠራ።

ኖቶሪየስ ቢአይጂ እና ፒ ዲዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኖቶሪየስ ቢአይጂ እና ፒ ዲዲ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢስት ኮስት የሂፕ-ሆፕ መነሻ ናት። ሾን ኮምብስ (ቀደም ሲል ፓፊ እና ፒ ዲዲ ተብሎ ይጠራ ነበር) በ1992 ኖቶሪየስ ቢአይጂ (ቢጊ ስሞልስም ይባላል) ጨምሮ ሌሎች ሙዚቀኞችን አካቶ ባድ ቦይ የተባለውን አሳታሚ ድርጅት መሠረተ።

በሌላኛው የአሜሪካ ጫፍ ደግሞ ሎስ አንጀለስ የጋንግስታ ራፕ መዲና ሆና ብቅ አለች። እዚያ ደግሞ ዶክተር ድሬ እና ቱፓክን ያካታተው ዴዝ ሮው ሪከርድስ ደግሞ በሹግ ናይት ተቋቋመ።

በ1994 ቱፓክ ስቱዲዮ ውስጥ ተተኩሶበት ቆሰለ። የቀድሞ ጓደኛው ቢጊ ስለጉዳዩ ቀደም ብሎ መረጃው ሊኖረው እንደሚችል ገመተ። ቢጊ ደግሞ ሳይውል ሳያድር ሁ ሾት ያ? [(ማን ተኮሰብህ?) የሚል ሙዚቃ ለቀቀ። ቱፓክ ሙዚቃው ለእሱ ተብሎ የተሠራ እንደሆነ ገመተ።

በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 3 ቀን 1995 ሶርስ መጽሔት ባዘጋጀው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይም አለመግባባቱ ቀጠለ። ናይት መድረክ ላይ ሆኖ ኮምብስ እና ባድ ቦይ ሪከርድስን የሚያስቆጣ ድርጊት ፈጸመ።

ቫይብ የሚባል መጽሔት የነበረው ጆንስ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ስብሰባ ጠራ።

የስብሰባው ምክንያት ግን በኢስት እና ዌስት ኮስት መካከል የተፈጠረው እሰጥ አገባ ብቻ አልነበረም። ስለሂፕ-ሆፕ ለመነጋጋር እና ቀጣዩ ትውልድ ስለሕይወት እና ቢዝነስ ከታላላቆቹ ጋር የሚመክርበት መድረክ እንዲሆን ጭምር ነው።

ራፕ የፈጠረው መጥፎ ገጽታ እና በሙዚቀኞች መካከል ያለው አለመግባባት ትልቁ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

“ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይህንን ለመቅረፍም ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ማሰባሰብ ነበር ዓላማው” ብሏል የዝግጅቱ አወያይ የነበረው ፋብ 5 ፍሬዲ።

“ለነገሮች ትኩረት ለመስጠት ጊዜው አሁን ነው እንድል ያደረገኝ ቱፓክ ነው” ሲል ጆንስ በስብሰባው ላይ ተናገረ።

ቱፓክ አልነበረም። በወሲብ ጥቃት ምክንያት ታስሮ ነበር። ሱጅ፣ ድሬ ኮምብስ እና ቢጊ ግን ነበሩ።

ስኑፕ ዶግ፣ ዶክተር ድሬ እና ኩዊንሲ ጆንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስኑፕ ዶግ፣ ዶክተር ድሬ እና ኩዊንሲ ጆንስ

ጆንስም በወቅቱ ከቱፓክ ጋር ተጋጭቶ ነበር። በ1993 በታተመችው ሶርስ መጽሔት ላይ ነጭ ሴቶችን አግብቷል በሚል ራፐሩ ፕሮዲዩሰሩን ተችቶታል።

ጆንስ በዝግጅቱ ላይ “መጀመሪያ ላይ ውጥረት ቢኖርም ግን በኋላ ላይ ተስማማን” ብሏል።

“ተነጋግረን፤ ከዚህ በፊት ማንም እንደዚህ አናግሮኝ አያውቅም አለ” ሲል አክሏል።

“እኔም ከዚህ በላይ አላባብሰውም አልኩት።”

ጆንስ ቫይብ መጽሔቱን ይዞ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ጆንስ ቫይብ መጽሔቱን ይዞ

ሃምሳ ገደማ ተደማጭነት ያላቸው አርቲስቶች እና አሳታሚዎች ተገኝተዋል። የፐብሊክ ኤነሚው ቻክ ዲ፣ ኤ ትራይብ ኮልድ ኩዌስት አባላት፣ ኤምሲ ላይት፣ ክሪስ ክሮስ፣ ዠርሜይን ደፕሪ እና የቦይዝ ኤን ዘሁድ ፊልም አዘጋጅ ጆን ሲንግለተን ተጠቃሾች ናቸው።

ጆንስ የግል ሕይወት ታሪኩን በያዘው መጽሐፉ “እነዚህ የማይግባቡ እና በአንድ ክፍል ተቀምጠው የማያውቁ ሰዎች አንድ ላይ መሆናቸው ስጋት ፈጥሮብኝ ነበር” ሲል አስፍሯል።

ስመጥሮቹ የሙዚቃ አሳታሚዎች ክላረንስ አቫንት እና አህመት አርተጉንም ተገኝተዋል። የአሜሪካ የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የጦር ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩት ኮሊን ፖልም ተሳትፈዋል። ፖል የመጀመሪያው አፍሪካ-አሜሪካዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ለማገልገልም በቅተዋል።

ፖል ፕሬዝዳንት የመሆን ምኞት ነበራቸው። ለዚያም ነበር ጉባኤው በምሥጢር የተካሄደው። የራፕ ሙዚቃን ከበበው አሉታዊ ገጽታ ጋር የፖል ስም እንዳይያያዝ ነበር ጆንስ ምሥጢራዊ ያደረገው።

ትኩረት ላለመሳብም በመጨረሻው ደቂቃ የስብሰባ ቦታዎችን ቀይረዋል። የመቅረጫ መሣሪያዎችንም ወስደዋል።

ኢንዲያናፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መፃህፍት ውስጥ በሚገኝ እና ባልታተመ ደብዳቤ ላይ “የእኔ ውሳኔ ለእርስዎ ባለኝ ጥልቅ አክብሮት እና ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እርግጠኛ ይሁኑ” ጆንስ ሲል ለፖል ጽፏል።

“በዚህ ኮንፈረንስ ለውጥ እንደምናመጣ አውቃለሁ። ሁኔታውን ስለያዙበት መንገድ እናመሰግናለን። የጦር መርከቧን በአንድ ወይም በሁለት ኢንች ማንቀሳቀስም እንችል ይሆናል።”

ኩዊንሲ ጆንስ እና ኮሊን ፖል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኩዊንሲ ጆንስ እና ኮሊን ፖል

ጆንስ በኋላ በመጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል “አንዳንድ ወጣት ራፐሮች ማን እንደሆነ እንኳን አያውቁም ነበር። አንዳንድ ጸብ የሚያጭሩ አስተያየቶች ሲሰጡ ፖል ወታደራዊ ባህሪውን እና ሥልጣኑን በጥሩ ሁኔታ አሳይቷል።”

ፋብ 5 ፍሬዲም በፖል እና በናይት መካከል የነበረውን አንድ ንግግር ያስታውሳል። “እሱ [ናይት] የሚናገርበት እና ኮሊን ፖል ምላሽ የሚሰጥበት አጋጣሚ ነበር” ብሏል።

“ይህ ባለ አራት ኮከብ ጄኔራል ከሱግ ናይት ጋር ተነጋግሮ ናይትን በቦታው አስቀመጠው።”

ጆንስ ስለሕይወቱ በሚዳስሰው የ2018 የኔትፍሊክስ ዘጋቢ ፊልም የስብሰባውን የተወሰነ ቅንጫቢ ቪዲዮ አውጥቷል።

“ስለምትሠሩት ነገር በቁም ነገር መነጋገር አለብን” ሲል ለተሳታፊዎች ሲናገር ታይቷል።

“እነሱ አይቀልዱም፤ እመኑኝ እውነተኛ ጥይቶች አሉ” ብሏል።

ድምጹ እየተሰባባረም “በጣም ስሜት የሚነካ ነገር ነው። ቢያንስ የእኔ ዕድሜ ድረስ ስትኖሩ ማየት እፈልጋለሁ።”

“ኩዊንሲ ችግሩን ስለተረዳ ስሜታዊ ሆነ” ይላል ፋብ 5 ፍሬዲ።

“በጣም መጥፎው እና የሚያሳዝን ክሰተት ተፈጠረ”

ጆንስ እና ቱፓክ ቅሬታቸውን ፈቱ። ቱፓክ በ1993 ሰጠውን አስተያየት ተከትሎ የጆንስ ልጅ ሆነችው ራሺዳ (ዘ ኦፊስ በተሰኘው የአሜሪካ ሲትኮም ላይ ተሳታፊ ነበረች) ራፐሩን አብጠልጥላ ሃሳቧን ሶርስ መጽሔት ላይ ጻፈች።

ቱፓክ በአጋጣሚ ከጆንስ ሌላኛዋ ልጅ ኪዳዳ ጋር ሲገናኝ ራሺዳ መስላው ይቅርታ ጠየቃት። ቱፓክ እና ኪዳዳ ጉዳዩን ወደ ጎን ብለው የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ።

ኩዊንሲ ጆንስ እንዲህ ሲል ጽፏል “ምንም እንኳን መጥፎ አጀማመር ቢኖረንም እሱን ሳውቅው እንደ አርቲስት እና እንደ ሰው ያለውን ትልቅ አቅም አይቻለሁ።”

ቱፓክ ከዴዝ ሮው በመውጣት የጆንስን አታሚ ድርጅት ለመቀላቀል አቅዶ ነበር የሚሉ ወሬዎችም ነበሩ።

ከጉባኤው ከአንድ ዓመት በኋላ መስከረም 1996 ላይ ቱፓክ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።

ቀድሞ የወሮበሎች ቡድን መሪ የነበረው ዱአን “ኬፍ ዲ” ዴቪስ ባለፈው ዓመት ከግድያው ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበታል። እሱ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

እአአ በ1997 ደግሞ ኖቶሪየስ ቢአይጂ በጆንስ አሳታሚ እና መጽሔት ከተዘጋጀ ድግስ ሲወጣ በጥይት ተመትቶ ተገደለ። በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ክስ የተመሠረተበት ሰው የለም።

ናይት ገጭቶ በማምለጥ ወንጀል ማረሚያ ቤት ሲገኝ ኮምብስ ደግሞ ከወሲባዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ክሱን በመጠባበቅ ላይ እገኛል። ኮምብስ ግን የቀረቡበትን ክሶች አስተባብሏል።

ኩዊንሲ እና ልጁ ኪዳዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኩዊንሲ እና ልጁ ኪዳዳ

በ90ዎቹ ውስጥ የነበረው ብጥብጥ “አስፈላጊ አልነበረም” ከማለት ባለፈ ችግሩ የተፈጠረው በሙዚቃ ኢንደስትሪው ውስጥ ባሉ “የሌሎችን ቦታ በሚፈልጉ እና ወንበዴ ችግር ፈጣሪዎች” ነው ሲል ፋብ 5 ፍሬዲ ተናግሯል።

“የኢስት/ዌስት ኮስት ግጭት በዋነኝነት የተቀሰቀሰው በቅናት ነው። ይህ ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን በከፍተኛ ሁኔታ ተራግቦ እሳቱ ቢጊ እና ቱፓክ እንዲገደሉ አደረጋቸው።”

ካለው ስምን አንጻር ጆንስ እንኳን የደም መፋሰሱን ለመከላከል አልቻለም።

በስብሰባው ላይ አንዳንድ ትምህርቶች መቀሰማቸውን እና በሂፕ-ሆፕ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ እንደሚገባው ፍሬዲ ያምናል።

“በዚያ ክፍል ውስጥ መሆን የማይታመን እና የአስገራሚ ነበር።”

“አስደሳች ጊዜ ነበር። ጉዳዩ ባለመነሳቱ እዚያ ከነበሩት ሰዎች ውጪ ማንም አለማወቁ ትልቅ ቦታ ያሰጠዋል” ብሏል።