ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ሾን ዲዲ ኮምብስ የቀረበበት ክስ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ በአሜሪካ የሙዚቃ ታሪክ እጅግ ገናና እና ስኬታማ ከሚባሉ የራፕ ዘውግ አቀንቃኞች አንዱ ነው።
ዲዲ የወሲብ ንግድ ማዘዋወር እና ማጭበርበር ክሶች ቀርበውበታል። ክሱን ለመከታተል በቅርቡ ችሎት ፊት ይቀርባል።
ራፐሩ ሐሙስ ዕለት ክሱን ለመስማት ፍርደ ቤት ቀርቧል። ዳኛው ችሎቱ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ግንቦት 5 እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
ግራጫ የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም ለብሶ ፍርድ ቤት የቀረበው ከጠበቃው ጋር ነበር። ዳኛው ጠበቃዎች እና ዐቃቤ ሕግ ክሱን በተለመከተ ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየት እንዳይሰጡ ሲያስጠነቅቁ ነበር።
የሾን ኮምብስ (ዲዲ) ቤተሰብ አባላትም ፍርድ ቤት ተገኝተው ከራፐሩ ኋላ ተደርድረው ተቀምጠው ታይተዋል። ራፐሩ ወደ ቤተሰቡ አባላት ዞር ብሎ “እወዳችኋለሁ” ሲል አንሾካሽኳል።
የዲዲ ሦስት ሴት፣ ሦስት ወንድ ልጆቹ እና እናቱ ችሎት ተገኝተዋል። ዲዲ በተደጋጋሚ ፀልዩልኝ በሚል ዓይነት ምልክት ሲያሳይም ነበር።
ታዋቂው ራፐር ከቀረበበው የወንጀል ክስ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ወሲባዊ ጥቃት፣ መድፈር እና ወሲባዊ ብዝበዛ አድርሶብናል ሲሉ ክስ አቅርበውበታል።
ኮምብስ የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ የሚያስተባብል ሲሆን፣ የራፐሩ ጠበቃዎችም በተደጋጋሚ ድንበኛችን ንፁህ ነው፤ የቀረቡበት ክሶች “ሐሰተኛ እና ስም አጥፊ ናቸው” ይላሉ።
የዲዲ ችሎት መቼ ይጀምራል?
አሜሪካዊው ዳኛ አሩን ሰብራማኒያን ችሎቱ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት 2025 ግንቦት 5 እንደሚጀምር ተናግረው የችሎቱ አድራሻ ማንሀታን ከተማ መሆኗን አስታውቀዋል።
ዲዲ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሐሙስ ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ ነው ፍርድ ቤት የቀረበው።
ዐቃቤ ሕግ ኤሚሊ ጆንሰን መንግሥት ክሱን ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ሦስት ሳምንታት ይፈልጋል ሲሉ ለዳኛው ተናግረዋል።
የዲዲ ጠበቃ ማርክ አግኒፊሊዮ በበኩላቸው ቡድናቸው ለመዘጋጀት የተወሰኑ ሳምንታት እንደሚፈልግ ለችሎቱ አሳውቀዋል።
የክስ መስማቱ ሒደት እንደተጠናቀቀ የዲዲ ደጋፊዎች ወደ መውጫው በር ፈጠን ብለው ተራምደው በመሄድ ራፐሩ ሲወጣ ለማየት ሲገፋፉ ተስተውለዋል።
ዲዲ የቀረበበት ክስ ምንድነው?
ራፐሩ በፌዴራል ፍድት ቤት የቀረበበት የወንጀል ክስ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ግለሰቦች የተለያዩ ጥቃቶች እና ብዝበዛዎች ፈጽሞብናል በሚል ራፐሩን ይከሱታል።
በፌዴራሉ ፍርድ ቤት ከቀረቡበት የወንጀል ክሶች መካከል አፈና፣ በመድኃኒት ማደንዘዝ እና ሴቶች ወሲባዊ ድርጊት እንዲፈፅሙ አንዳንድ ጊዜ በጦር መሣሪያ አሊያም በማስፈራራት ማስገደድ የሚሉ ይገኙበታል።
ከወራት በፊት ፖሊስ ሎስ አንጀለስ የሚገኘውን በራፐሩ ቤት ላይ ባደረገው ፍተሻ “ፍሪክ ኦፍስ” አሊያም የጋራ ወሲብ ለመፈፀም ጥቅም ላይ የሚውሉ በርካታ ቁሳቁሶችን፣ ዕፆችን እና 1000 የሚሆኑ የሕፃናት ቅባቶች ማግኘቱን አስታውቋል።
በሌሎች ክሶች ደግሞ ራፐሩ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሞብናል ያሉ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።
ከእነዚህ ክሶች መካከል የተወሰኑትን የያዙት የቴክሳሱ ጠበቃ ቶኒ በዝቢ ከ100 በላይ ወንዶች እና ሴቶች በቅርቡ ክሳቸውን እንደሚያቀርቡ እንዲሁም ያቀረቡም እንዳሉ ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ ከሳሾች ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ገና ታዳጊ ሳሉ እንደሆነ የሚናገሩ ሲሆን፣ የ9 ዓመት ታዳጊ ሳሉ ጥቃት የደረሰባቸው እንዳሉ ጠበቃው አሳውቀዋል።
የሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ የቀድሞ ፍቅረኛ የሆነችው ካሳንዳራ ቬንቹራ (ካሲ) ናት በ2023 መገባደጃ ራፐሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የከሰሰችው። ካሲ ራፐሩ ብዙ ጥቃት አድርሶብኛል እንዲሁም ደፍሮኛል ስትል ከሳለች።
ካሲ ክሱን ባቀረበች በነጋታው ዲዲ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ከፍሎ ክሱ እንዲዘጋ ማድረግ ችሏል። ነገር ግን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል አስተባብሏል።
ከካሲ ክስ በኋላ በርካታ ሴቶች ዲዲ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብናል ሲሉ ክስ ማቅረብ ጀመሩ። አንዳንዶቹ ክሶች ወደኋላ ተጉዘው በአውሮፓውያኑ 1991 ተፈፅሟል የተባለ ጥቃትን የሚያነሱ ናቸው።
ከከሳሾቹ መካከል አንደኛዋ የ17 ዓመት ታዳጊ ሳለች “የወሲብ ድርጊት ዝውውር” እንደተፈፀመባት እንዲሁም ራፐሩ እና ሁለት ሌሎች ሰዎች “በጋራ ደፍረውኛል” ስትል ከሳለች።
እኒህን ወቀሳዎች ተከትሎ ባለፈው ታኅሣሥ በኢንስታግራም ገፁ ምላሽ የሰጠው ዲዲ “ይበቃል ማለት ይበቃል ነው” ብሎ ነበር።
“እኔ እነዚህን አስነዋሪ ድርጊቶች አልፈፀምኩም። ለስሜ መታገሌን እቀጥላለሁ፤ ለቤተሰቤ እና ለእውነታው እታገላለሁ” ሲል በኢንስታግራም ገፁ መፃፉ ይታወሳል።
ከዚህ መልዕክት ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ የቀረበበት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዲዲ አሁን የት ነው ያለው?
ዲዲ ኒው ዮርክ ግዛት ብሩክሊን ከተማ በሚገኘው የሜትሮፖሊታን ማረሚያ ቤት ውስጥ ነው የሚገኘው። ካለፈው መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በዚህ ማረሚያ ቤት ይገኛል።
ጠበቆቹ ማረሚያ ቤቱ “አስከፊ ነው” በማለት ችሎቱ እስኪደርስ ድረስ እንዲለቀቅ ጠይቀው ነበር።
የኒው ዮርክ ፌዴራል ዳኛ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርገው ኮምብስ በዋስ ከተለቀቀ “ከአገር ሊጠፋ ይችላል” ብለዋል።
ቀጣይ ምን ሊገጥመው ይችላል?
ዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛው ካሲ ቬንቹራን አንድ ሆቴል መተላለፊያ ላይ ሲመታት የሚያሳይ ቪድዮ ከማስረጃነት እንዲወጣ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ጠበቃዎቹ ይህን ያሉት ቪድዮውን ለሲኤንኤን ቴሌቪዠን ጣቢያ አሳልፎ የሰጠው መንግሥት ነው በማለት ነው። አክለውም ይህ ቪድዮ “ኮምብስ ፍትሐዊ የሆነው ፍርድ እንዳያገኝ የሚያደርግ እና ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት ሚዛናዊ ያልሆነ አስተሳሰብ እንዲኖር የሚያደርግ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።
የመንግሥት ጠበቃዎች ቪድዮውን ለመገናኛ ብዙኃን አሳልፈው ሰጥተዋል የተባለውን ወቀሳ ውድቅ አድርገው ቪድዮው ይፋ ከመሆኑ በፊት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ይህ ዲዲ የቀድሞው ፍቅረኛውን ሲደበድባት የሚያሳየው ቪድዮ ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ ራፐሩ “በድርጊቱ ተፀፅቻለሁ” ሲሉ የይቅርታ መልዕክት መልቀቁ ይታወሳል።
የራፐሩ ጠበቃዎች አሁንም በዋስትና እንዲለቀቅ እየታገሉ ይገኛሉ። ጠበቃዎቹ እንደሚሉት ራፐሩ ችሎት እስኪደርስ ድረስ “እንቅስቃሴው ተገድቦ” ለመቀመጥ ተስማምቷል።
“ኮምብስ ነፃ ነው። ወደ ኒው ዮርክ ተጉዞ እጁን የሰጠው ነፃ እንደሚወጣ ስለሚያውቀው ነው” ይላሉ ጠበቆቹ።
ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘስ?
ራፐሩ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስር ይፈረድበታል።
ዲዲ በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሊጠብቀው ይችላል። በወሲብ ማዘዋወር ክስ ደግሞ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል።
የዲዲ ችሎት ለሕዝብ ክፍት ይሆናል። ሁሉም የአሜሪካ የፌዴራል ችሎቶች ለሕዝብ ክፍት ናቸው። በዝግ ችሎት የሚደረጉት በጣም ጥቂት ክሶች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ የብሔራዊ ደኅንነትን የተመለከቱ ናቸው።
የዲዲ የችሎት ውሎ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሕዝቡ ክፍት ሆኖ ይቆያል። ነገር ግን ችሎት ፊት ቀርቦ ሳለ በቀጥታ ማስተላለፍ አይቻልም። በርካታ የአሜሪካ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ካሜራ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች አይፈቅዱም።
ዲዲ ተጨማሪ የወንጀል ክሶች ይቀርቡበታል ወይ የሚለው ግልፅ አይደለም። ቢሆንም አቃቤ ሕግ “ምርመራውን እንደሚቀጥል” አስታውቆ በደል ደረሰብን ያሉ ሰዎች ለባለሥልጣናት እንዲያሳውቁ መክረዋል።












