ከ100 በላይ ሰዎች ራፐሩ ዲዲ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሞብናል ሲሉ አዲስ ክስ መሠረቱ

አሜሪካዊው ራፐር ሾን 'ዲዲ' ኮምብስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ጥቁር አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ ላይ ክስ ሊመሠርቱ እንደሆነ የከሳሾቹ ጠበቃ አስታወቁ።

ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ፣ በመድፈር እና የወሲባዊ ብዝበዛ በመፈጸም በሚሉ ወንጀሎች ነው ታዋቂው ሙዚቀኛ ላይ አዲስ ክስ የሚመሠረተው።

የቴክሳስ ግዛቱ ጠበቃ ቶኒ በዝቢ እንደሚሉት ከከሳሾቹ መካከል አንዳንዶች ገና የዘጠኝ ዓመት ሕፃን ሳሉ ነው ወንጀሉ የተፈፀመባቸው።

ዲዲ በተሰኘ የመድረክ ስሙ የሚታወቀውን ራፐር የሚወክሉት ጠበቃ ኤሪካ ዎልፍ ደንበኛቸው ክሱን “እንደማይቀበል” ገልፀው “ሐሰተኛ እና ስም አጥፊ ናቸው” ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠበቃ በዝቢ “ሁሉንም ማስረጃ አሰባስበን ሌሎች በድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችን ለሕግ እናቀርባለን” ብለዋል።

የዲዲ ጠበቃ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ ደንበኛቸው “ችሎት ፊት ሲቀርብ እውነቱን በማፍረጥረጥ ንፁህ ስሙን ለማደስ” እንደቸኮለ አመልክተዋል።

እስር ላይ የሚገኘው ዲዲ በቅርብ ጊዜያት በርካታ ክሶች እየቀረቡበት ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ዲዲ በማጭበርበር እና በወሲባዊ ጥቃት ላይ በመሰማራት ነው የተጠረጠረው። ዋስትና ጠይቆ የተከለከለው ራፐር የፌዴራል ማረሚያ ቤት ይገኛል። ራፐሩ ውድቅ የተደረገበት ዋስትና ድጋሚ እንዲታይ ይግባኝ ጠይቋል።

ዲዲ የቀረቡበትን ሁሉንም ክሶች አልፈፀምኩም በማለት ያስተባብላል።

አሁን ከ120 በላይ ክሶች የተመሠረቱበት ሲሆን፣ ጠበቃው እንደሚሉት ከ100ዎቹ ከሳሾች መካከል ግማሾቹ ሴቶች ቀሪዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው።

አክለውም 25 ከሳሾች ድርጊቱ በተፈፀመባቸው ወቅት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነበር። ዲዲ ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም ሲከሰስ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ዲዲ ከአውሮፓውያኑ 1991 እስከ 2024 ባለው ጊዜ በሎስ አንጀለስ፣ በኒው ዮርክ እና በማያሚ ተባሉት የአሜሪካ ክፍሎች ውስጥ ጥቃት ፈፅሟል ይላሉ የከሳሾቹ ጠበቃ። አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈፀሙት በ2015 እንደሆነ ገልፀዋል።

ከከሳሾቹ መካከል በርካቶቹ እንደሚሉት ዲዲ በመኖሪያ ቤቱ እና በተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ በሚያዘጋጃቸው ፓርቲዎች ላይ ከተጋበዙ በኋላ ነው የመድፈር ወንጀል የተፈፀመባቸው።

ባድ ቦይ ሬከርድስ የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን መሥራች የሆነው ዲዲ፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድርጊቶች ቅሬታ ይቀርብበት ነበር።

ባለፈው ዓመት ኅዳር የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ ኤሊዛቤት ቬንቹራ ክፉኛ አካላዊ ጥቃት እንዳደረሰባት በመጥቀስ ራፐሩን መክሰሷ አይዘነጋም። ራፐሩ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ቢከራከርም በገለልተኛ ሸንጎ ጉዳዩን መፍታቱ ተነግሯል።

ከዚህ ክስ በኋላ የቀድሞ ፍቅረኛውን ሲደበድብ የሚያሳይ ቪድዮ መውጣቱን ተከትሎ ባለፈው ግንቦት የይቅርታ ቪድዮ አሠራጭቶ ነበር።

በራፕ የሙዚቃ ዘውግ እጅግ የተሳካላቸው ከሚባሉ ግለሰቦች አንዱ የሆነው ሾን ኮምብስ አሊያም ዲዲ ወሲባዊ እና አካላዊ ጥቃት በማድረስ በተለያዩ ሴቶች ክስ ቀርቦበት ያውቃል።