ኢራን በእስራኤል ላይ ስለፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት እስካሁን ምን እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች። ጥቂቶቹ የእስራኤልን ግዛት መምታት ችለዋል።
ኢራን ባለፈው ሚያዝያ እስራኤል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የኢራን የአሁኑ ጥቃት ባለፉት ጥቂት ወራት ለለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ሆኗል።
የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣናት ጥቃቱ ያለቀ ይመስላል፤ “ለጊዜውም ቢሆን” ከወደ ኢራን ምንም ስጋት የለም ብለዋል። ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥቃቱ “መዘዝ ያስከትላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ስለጉዳዩ የምናውቀውን እንደሚከተለው አጠናቅረናል።
ኢራን የፈጸመችው ጥቃት ምን ያህል ነው?
ኢራን ወደ እስራኤል 180 የሚጠጉ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን የእስራኤል ጦር አስታውቋል። ይህም ወደ እስራኤል 110 የሚጠጉ የባላስቲክ ሚሳዔሎች እና 30 ክሩዝ ሚሳኤሎች ከተተኮሱበት የሚያዝያው ጥቃት በመጠኑ ትልቅ ያደርገዋል።
በእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ የተቀረጸ ምስል ምሽት 1፡45 አካባቢ አንዳንድ ሚሳዔሎች በቴል አቪቭ ሰማይ ላይ ሲበሩ ታይተዋል።
አብዛኛዎቹ ሚሳዔሎች በእስራኤል የአየር መከላከያ ዘዴዎች አንዲከሽፉ መደረጉን የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣን ገልጸዋል። በእየሩሳሌም የሚገኝ የቢቢሲ ዘጋቢ በበኩሉ አንዳንድ ወታደራዊ ካምፖች ተመትተው ሊሆን እንደሚችል እና ሬስቶራንቶች እና ትምህርት ቤቶች ደግሞ መመታታቸውን ገልጿል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ (አይአርጂሲ) በበኩሉ 90 በመቶ የሚሆኑ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን እንደመቱ ገልጿል። ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውለዋል ሲልም አክሏል። የአይአርጂሲ ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ሦስት የእስራኤል ወታደራዊ ካምፖች በጥቃቱ ዒላማ ተደርገዋል።
በዌስት ባንክ በሚገኘው ኢያሪኮ ከተማ የሚገኘው የፍልስጤም የሲቪል መከላከያ ባለስልጣን በበኩሉ በኢራን የሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው መሞቱን አስታውቋል።
የከተማውን አስተዳዳሪ ሁሴን ሃማኤልን ያነጋገረው ኤኤፍፒ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ከሆነ ግለሰቡ የሞተው በሮኬት ስብርባሪዎች ተመትቶ ነው።
የእስራኤል ባለስልጣናት ማክሰኞ በደረሰው ጥቃት ምንም አይነት ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰ ቢገልጹም፤ የአገሪቱ የሕክምና ባለሙያዎች ግን ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
ኢራን ለምን እስራኤልን አጠቃች?
ጥቃቱ የተሰነዘረው እስራኤል አንድ ከፍተኛ አዛዧን እና በአካባቢው በኢራን የሚደገፉ የሚሊሻ መሪዎችን መግደሏን ተከትሎ መሆኑን አይአርጂሲ ገልጿል።
ይህም ከቀናት በፊት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ የተገደሉትን የሄዝቦላህ መሪ ሆኑት ሀሰን ናስራላህ እና የአይአርጂሲ አዛዥ የሆኑት አባስ ኒልፎሮሻን የሚመለከት ነው።
በሐምሌ ወር ደግሞ ቴህራን ውስጥ የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ መገደላቸውንም ጠቅሷል። እስራኤል ከሃኒዬህ ሞት ጀርባ መኖሯን ባትቀበልም፣ ተጠያቂ እንደሆነች በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ የአገሪቱ ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜህኒ የማክሰኞው የሚሳዔል ጥቃት እንዲፈጸም በቀጥታ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ኢራን የእስራኤልን የመኖር መብት ካለመቀበሏም በላይ ልታጠፋትም ትሻለች። እስራኤልን የሚቃወሙ ቡድኖችንም ለዓመታት ስትደገፍ ቆይታለች።
ኢራን የህልውናዋ ስጋት መሆኗን እስራኤል ታምናለች። በቴህራን ላይ ድብቅ ዘመቻዎችን ለዓመታት ስታካሂድ ቆይታለች።
አይረን ዶም ሚሳዔሎችን አጨናግፏልን?
እስራኤል የተራቀቀ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ትጠቀማለች። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የሚታወቀው አይረን ዶም ነው። በሐማስ እና በሄዝቦላ የሚተኮሱትን የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ለማጨናገፍ በሚል የተሰራ ነው።
በሚያዝያ ወር ከኢራን የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ጥቅም ላይ ውሏል። ሌሎች የአገሪቱ ያሏት “ላቅ ያሉ” የመከላከያ ሥርዓቶች የማክሰኞ ጥቃት ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ሳይውሉ አልቀሩም።
በአሜሪካ እና በእስራኤል በጋራ የሚመረተው የዳዊት ወንጭፍ (ዴቪድስ ስሊንግ) ከመካከለኛ እስከ ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሮኬቶችን እንዲሁም የባለስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ይውላል። የረዥም ርቀት የባለስቲክ ሚሳዔሎች ለመከላከል ደግሞ እስራኤል አሮው 2 እና አሮው 3 የተባሉ ስርዓቶችን ትጠቀማለች።
የእስራኤል አጋሮች ምን አይነት ምላሽ ሰጡ?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ጥቃቱን "የከሸፈ እና ውጤታማ እንዳልሆነ" ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚገኙት የአሜሪካ ኃይሎች "እስራኤልን እንዲረዱ" እና የኢራንን ሚሳዔሎችን እንዲያጨናግፉ አዘዋል።
የፔንታገን ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ወደ እስራኤል በሚምዘገዘጉ የኢራን ሚሳዔሎች ላይ ወደ 12 የሚጠጉ ጸረ ሚሳኤሎችን መተኮሳቸውን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ደግሞ "ይህንን የኢራን ድርጊት" በማውገዝ፤ ዩናይትድ ስቴትስ "በርካታ" ጸረ ሚሳዔሎችን መተኮሷን አረጋግጠዋል።
በዮርዳኖስ መዲና አማን ላይ የጸረ ሚሳዔል ጣልቃ ገብነት አንደነበር የሚያሳይ ምሥል እንደነበር ቢቢሲም አረጋግጧል። ኢራን በሚያዝያ ወር ባደረሰችው ጥቃት ዮርዳኖስ በርካታ ሚሳኤሎችን መትታ ጥላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም ተዋጊ ጄቶች በሚያዝያ ወር እንዳደረጉት ሁሉ ማክሰኞ ዕለትም እስራኤልን በመደገፍ ተሳታፊ ነበሩ።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ሳይሰጡ የብሪታንያ ጦር ማክሰኞ ማምሻውን "ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉንን ሚና ተጫውቷል" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር አገራቸው ከእስራኤል ጎን መቆሟን እና "ራስን ለመከላከል መብቷ" ዕውቅና እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ፈረንሣይ እና ጃፓን ደግሞ የኢራንን ጥቃት በማውገዝ ድምጻቸውን በማሰማት ግጭቱ የበለጠ ተባብሶ እንዳይቀጥል ለሁሉም ወገኖች ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ኔታንያሁ ኢራን ትልቅ ስህተት በመሥራቷ "ዋጋ ትከፍልበታለች" ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በበኩላቸው "እቅዶች አሉን። በወሰንበት ቦታ እና ሰዓት እንተገብረዋለን"ብለዋል።
የኢራኑ አይአርጂሲ ደግሞ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ከወሰደች ቴህራን የምትሰጠው ምላሽ “ይበልጥ አፍራሽ እና አጥፊ ነው” ብሏል።
በተያያዘ ዜና የእስራኤል ጦር የቤይሩት ነዋሪዎች ሄዝቦላህ ከሚገኝበት ደቡባዊ የከተማዋ ዳርቻ ለቀው እንዲወጡ ካስጠነቀቀ በኋላ በቡድኑ ዒላማዎች ላይ አዲስ የአየር ድብደባ ፈጽሟል።












