የኢራን ሚሳዔል፡ መጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ደወል ሰማን፤ ቀጥሎ ‘ቡም’ የሚል ፍንዳታ

የሚሳኤል ጥቃቶቹ ደመና ጥሶ ሲመጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአካባቢው አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡30 የሁሉም ሰው ስልክ ይጮህ ጀመር።

ስልካቸው ላይ የተነበበው መልዕክት “በፍጥነት ወደ መጠለያ ግቡ፤ ሌላ መልዕክት እስኪደርሳችሁ እንዳትወጡ” የሚል ነው።

ይህን መልዕክት የላከው የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ዕዝ ነው።

ሕዝቡ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ መሸሸጊያ መፈለግ ያዘ። ይህ ሲሆን የኢራን ሚሳዔሎች ወደ እስራኤል እየተምዘገዘጉ እየመጡ ነበር።

በመላው ሀገሪቱ የተሰማው እንደ አምቡላንስ ዓይነት ድምፅ ያለው የማስጠንቀቂያ ደወል ለሚሊዮኖች ደርሷል።

ቢቢሲ በእየሩሳሌም ቢሮ አለው። ቢሮው ለመሰል የአደጋ ጊዜ የተሠራ ድብቅ እና መስኮት አልባ ክፍል ታኮ ነው የተገነባው። ደወሉ ሲሰማ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ ድብቁ ክፍል እየሮጡ መግባት ያዙ።

ቀጥሎ የፍንዳታ ድምፅ መሰማት ያዘ። ግማሹ ሚሳዔል ዒላማውን ሲመታ የተቀረው ደግሞ በእስራኤል ሚሳዔል መቃወሚያ ሲወድቅ የሚሰማው የፍንዳታ ድምፅ ከባድ ነው።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ሚሳዔሎቹ የእስራኤልን ሰማይ ጥሰው ወደታች ሲመዝገዘጉ መብራት ይፈጥራሉ። የሚፈጥሩት መብራት ጉም በጥሶ ሲወርድ ማየት ልብ ያርዳል።

አንድ እስራኤላዊ አባት ከፍንዳታው ቤተሰቡን ለማሸሽ ሲሞክር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምሽት 2፡00 ገደማ የእስራል መከላከያ ሠራዊት ሚሳዔል መቃወሚያዎቹን ደግኖ እየተከላከለ እንደሆነ አሳወቀ። ነገር ግን ሰዎች ከተሸሸጉበት ሥፍራ በፍፁም እንዳይወጡ አሳሰበ። ቀጥሎ “የምትሰሙት ፍንዳታ ሚሳዔሎች ሲመክኑ የሚወጣ ነው” የሚል መልዕክት ላከ።

ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚለው ወሬ መሰማት የጀመረው ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ነበር።

እስራኤል “ውሱን እና ዒላማውን የጠበቀ” በማለት ሊባኖስን ከወረረች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው ቴል አቪቭ እና ሌሎች ከተሞች የሚሳዔል ናዳ የወረደባቸው።

ወረራው የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላሕ መሬት ለመሬት ጦርነት ለመፋለም እንደሆነ እስራኤል ትገልፃለች።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሚሳዔል ጥቃቱ የሐማስ፣ ሔዝቦላሕ እና ነባሩ የኢራን ጦር አዛዥ መገደላቸውን ለመበቀል እንደሆነ አስታውቋል።

የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለነዋሪዎች በስልካቸው ከተላከላቸው አንድ ሰዓት ገደማ አልፎታል። የእስራኤል ጦር አሁንም ሌላ መልዕክት ላከ። ፅሑፉ “አሁን ከተሸሸጋችሁበት መውጣት ትችላላችሁ” ሲል ይነበባል።

ከሚሳዔል ጥቃቱ በኋላ መግለጫ የሰጡት የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በማዕከላዊ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች አንዳንድ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን መትተዋል ብለዋል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ቪድዮዎች እንደሚጠቁሙት በተለይ በቴል አቪቭ በሚሳዔል ጥቃቱ ምክንያት የጎረጎደ መሬት አለ።

በእስራኤል ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ዌስት ባንክ በምትገኘው ጄሪኮ አንድ ሰው በጥቃቱ መገደሉን የፍልስጤም ሲቪል ሰርቪስ ባለሥልጣን አስታውቋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ግለሰቡ የተገደለው ከሰማይ ወደ መሬት በወደቁ የሚሳዔል ፍርስራሾች ምክንያት ነው።

ማክሰኞ ዕለት የተሰማውን የሚሳዔል ጥቃት ተከትሎ ምን ያክል ጉዳት ደረሰ ስለሚለው ጉዳይ የእስራኤል ባለሥልጣናት እስካሁን ማብራሪያ አልሰጡም።