ቢዮንሴ በግራሚ አዋርድ 99 ጊዜ በመታጨት ክብረ ወሰኑን ያዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂዋ አሜሪካዊት ድምጻዊት ቢዮንሴ በግራሚ አዋርድ ታሪክ 99 ጊዜ እጩ በመሆን ክብረ ወሰኑን ያዘች።
የ2025 የግራሚ አዋርድ ዕጩዎች በትናንትናው ዕለት ይፋ ሲደረግ ቢዮንሴ በ11 ዘርፎች ታጭታለች።
ከእርሷ በመቀጠል እያንዳንዳቸው በሰባት ዘርፎች የታጩት ኬንድሪክ ላማር፣ ቻርሊ ኤክሲኤክስ እና ቢሊ አይሊሽ ናቸው።
ቢዮንሴ አሁን ከማንኛውም የሙዚቃ ባለሙያ በበለጠ በግራሚ 99 ጊዜ በመታጨት ክብረ ወሰኑን የያዘች ቢሆንም፣ የዘርፉ ከፍተኛ ሽልማት ነው የተባለውን የዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ ግን እስካሁን አላሸነፈችም።
የ67ኛው የግራሚ ሽልማት አሸናፊዎች የሚታወቁት ጥር 25/ 2017 ዓ.ም.ነው።
በዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ዕጩዎች መካከል በ11 ዘርፍ የታጨችው ቢዮንሴ ኖውልስ ባለቤቷን ጄይዚን በልጣዋለች።
ከዚህ ቀደም ጥንዶቹ 88 ጊዜ የታጩ ሲሆን አሁን ቢዮንሴ ካውቦይ ካርተር (Cowboy Carter) በተሰኘው አልበሟ በ11 ዘርፎች መታጨቷን ተከትሎ የበላይ ሆናለች።
ቢዮንሴ በዚህ ዓመት ግራሚ የታጨችባቸው ዘርፎች በምርጥ አልበም ዘርፍ፣ ምርጥ የአገረሰብ ሙዚቃ አልበም፣ እንዲሁም ቴክሳስ ሆልድ ‘ም (Texas Hold 'Em) የሚለው ስራዋ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃ በሚል ዘርፍ ነው።
በዚህ ዓመት የግራሚ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ዘ ቢትልስ በ ‘ናው ኤንድ ዜን’ አልበማቸው በዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ ታጭተዋል።
ይህ አልበም የቡድኑ አባል የነበረው ጆን ሌነን በሕይወት በነበረበት ወቅት ያላጠናቀቀውን አንድ ሙዚቃ ስራ የሰው ሰራሽ አስተውልሆትን በመጠቀም አጠናቅቀው እንዳካተቱበት ተነግሯል።
ቢዮንሴ የግራሚ አዋርድን በግሏ 32 ጊዜ፣ ከዴስትኒስ ቻይልድ ጋር በጋራ በመሆን ደግሞ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ከፍተኛዋ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።
ይኹን እንጂ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ያህል የዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ ላይ ብትታጭም እስካሁን ድረስ አላሸነፈችም።
በ2024 በነበረው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ላይ ይህ ያንገበገበው ባለቤቷ ጄይ ዚ፣ የትዳር አጋሩ በምርጥ የሙዚቃ አልበም ዘርፍ አለማሸነፏ እንዳሳዘነው ገልጾ "ከማንም የበለጠ የግራሚ ሽልማቶችን ወስዳለች፤ ነገር ግን የዓመቱ ምርጥ አልበምን አላሸነፈችም። በራሳችሁ ስሌት እንኳ ብታዩት ይህ አያስኬድም። እስቲ አስቡት ከፍተኛ ግራሚ ያሸነፈ የዓመቱ መርጥ አልበምን አላሸነፈም" ሲል በቁጭት ተናግሮ ነበር።
ቢዮንሴ ዘንድሮ በ11 ዘርፎች መታጨቷን ተከትሎ በአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ በከፍተኛ ዘርፎች የታጨች ሴት አርቲስት ሆናለች።
በዚህ ዓመት ቢዮንሴ በምርጥ አልበም ዘርፍ ከፍተኛ ፉክክር የሚኖራት ከማንም በላይ እስካሁን አራት ጊዜ የዓመቱን ምርጥ አልበም ካሸነፈችው ቴይለር ስዊፍት ጋር ነው።
ቴይለር ስዊፍት በቅርቡ በአድካሚ ተከታታይ በሆነ የመድረክ ስራ ዓለምን እየዞረች ባለችበት ወቅት የለቀቀችው 'ዘ ቶርቸርድ ፖየትስ ዲፓርትመንት' የተሰኘ አልበሟ በምርጥ አልበም ዘርፍ ታጭቷል።
ለ15 ተከታታይ ሳምንታት በአሜሪካ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ በአንደኝነት ሲደመጥ የነበረው ይህ የስዊፍት ሰባተኛ የሙዚቃ አልበም የዓመቱ ምርጥ አልበም በሚል ዘርፍ ታጭቷል።
በዚህ ዘርፍ በተጨማሪም አንድሬ 3000፣ ሳብሪና ካርፔንተር፣ ቻርሊ ኤክሲኤክስ፣ ጃኮብ ኮሊየር፣ ቻፔል ሮአን እና ቢሊ አይሊሽም እጩዎች ናቸው።
በ2025 የግራሚ አዋርድ እጩዎች ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ዘርፎች ከታጩት መካከል ቢዮንሴ 11 ጊዜ በመታጨት ቅድሚያ ስትይዝ፣ ቢሊ አይሊሽ፣ ኬንድሪክ ላማር፣ፖስት ማሎኔ እና ቻርሊ ኤክሲኤክስ እያንዳንዳቸው ሰባት ጊዜ ታጭተዋል። ቴይለር ስዊፍት፣ ሳብሪና ካርፔንተር እና ቻፔል ሮን ደግሞ ስድሰት ስድሰት ጊዜ ታጭተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በእድሜ የገፉ የግራሚ አዋርድ ዕጩ ሆነዋል።
ፕሬዝዳንቱ በ100 ዓመታቸው በድምጽ ቅጂ በተሰራጨ መጽሐፋቸው የተነሳ ነው ዕጩ ለመሆን የበቁት።
ፕሬዝዳንቱ 'ታንክስ ቱ ላስት ሰንዴይስ ኢን ፕሌይንስ' ሲሉ የሰየሙት ይህ መጽሐፋቸው በሰንበት ትምህርት ቤት መምህርነት ለአሥርት ዓመታት ሲያገለግሉ የሰበሰቧቸውን የጸሎትና የምሳሌዎች አካትቶ የያዘ ነው።
በ66ኛው የግራሚ አዋርድ ላይ ቴይለር ስዊፍት ሚድናይትስ በተሰኘው አልበሟ ማሸነፏን ተከትሎ በምርጥ አልበም ዘርፍ አራት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ መሆኗ ይታወሳል።












