ወሲባዊ ቅሌት ፈጽሟል የተባለው የኢኳቶሪያል ጊኒው ባለሥልጣን ተባረረ

ባልታዛር ኢባንግ ኢንጎንጋ

የፎቶው ባለመብት, BALTASAR ENGONGA/FACEBOOK

የኢኳቶሪያል ጊኒ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረው ግለሰብ የወሲብ ድርጊቶች ቅሌት በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ መሠራጨታቸውን ተከትሎ ከኃላፊነቱ ተባረረ።

ባለትዳር እና የልጆች አባት የሆነው ባልታዛር ኤባንግ ኤንጎንጋ የተባለው ግለሰብ በኢኳቶሮያል ጊኒ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበረ ሲሆን፣ በቢሮው ውስጥ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ወሲብ ሲፈጽም የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ተሠራጭተዋል።

የወሲብ ቪዲዮዎቹ ከመላዋ ኢኳቶሪያ ጊኒ ውጪ ጭምር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሠራጨታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እንዲህ ያለ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ባልታዛር ቪዲዮዎቹ ይፋ ከመሆናቸው በፊት በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በዋና ከተማዋ ማላቡ ውስጥ በሚገኘው ብላክ ቢች በተባለ እስር ቤት ታስሮ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም።

ባለሥልጣኑ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዌማ ጋር ዝምድና ያለው ቢሆንም፣ የቪዲዮዎቹ ይፋ መሆንን ተከትሎ በፕሬዝዳንቱ በተፈረመ ደብዳቤ ከሥልጣኑ መባረሩ ተገልጿል።

በኢኳቶሪያል ጊኒ ዜጎች ዘንድ ቆንጆ መሆኑ የሚነገርለት ባተልታዛር ኤባንግ ኤንጎንጋ ለዚህም በቅጽል ስም ‘ቤሎ’ በመባል ይጠራል።

ግለሰቡ በመቶዎች ከሚቆጠሩ እና ከበርካታ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሚስቶች ጋር ወሲብ ሲፈጽም የቀረጻቸው ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ መሆናቸው በአገሪቱ ውስጥ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ መንግሥት ማስጠንቀቂያ እና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስድ አድርጎታል።

ከእነዚህ ቪዲዮዎች ውስጥ የተወሰኑት በአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ ውስጥ የተቀረጹ የወሲብ ድርጊቶች መሆናቸው ተገልጿል።

አንዳንዶች የቪዲዮዎቹ ይፋ መሆን እና የባልታዛር ከሥልጣን መባረር ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ለመሆን በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ካለው የሥልጣን ሽሚያ ጋር የሚያያዝ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

የባተልታዛር ኤባንግ ኤንጎንጋ አባት ለ45 ዓመታት ያህል የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ሆነው የቆዩትን እና በዕድሜ የገፉትን ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዌማን ይተካሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።

አሁን በልጃቸው ባልታዛር ላይ የቀረበው የሙስና እና የወሲብ ቅሌት የፕሬዝዳንቱ ልጅ እና የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ማንጉ በቀጣይ ሥልጣኑን እንዲረከብ በር ሊከፍት ይችላል ተብሎ ይታሰባል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሥራ ቦታ ላይ ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ የሚያዙ የመንግሥት ሠራተኞች “ከባድ እርምጃ” እንደሚጠብቃቸው ከቀናት በፊት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ቪድዮዎች ከተለቀቁ በኋላ ባወጡት መግለጫ ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ የሚያዙ የመንግሥት ሠራተኞች “ከባድ እርምጃ” እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ እንደተናገሩት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ቦታ ወሲብ ሲፈጽም ከተገኘ “የሥነ ምግባር ደንቡን በመጣስ” ምክንያት ከሥራው ይታገዳል ብለዋል።

“ሥነ ምግባር የጎደላቸውን እና ሕገወጥ ድርጊቶችን” ለመከላከልም የደኅንነት ካሜራዎች በፍርድ ቤቶች እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲተከሉ አዘዋል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው ውሳኔው የተላለፈው “የአገሪቷን ገጽታ የሚያንቋሽሹ ቪዲዮዎች” በሰፊው በመሰራጨታቸው ነው።