የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምጡቅነት ከሰው ልጆች ቢበልጥ ምን ይፈጠራል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቴክኖሎጂ ዕድገት ታዋቂ ከሆኑ ንድፈ ሐሳቦች አንዱ ‘The technological singularity’ ወይም ‘The singularity’ ነው።
‘ዘ ሲንጉላሪቲ’ ንድፈ ሐሳባዊ የወደፊት ነጥብ ነው። ያ ነጥብ ቴክኖሎጂ ከቁጥጥር የሚወጣበትና መቀልበስ የማይቻል እንደሆነ ንድፈ ሐሳቡ ያስቀምጣል።
በሰው ልጆች ሥልጣኔ “መገመት የማይቻል ተጽዕኖ” የሚፈጠርበት እንደሆነም ይገለጻል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተጀንስ) ከሰው ልጆች አስተውሎት የሚልቅበት (Superhuman level) ነጥብ ላይ ይደረስ ይሆን?
የሰው ልጆች በራሳቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራ ተበልጠው የሰው ልጅ ሥልጣኔ ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል?
እነዚህ ጥያቄዎች ከቴክኖሎጂው ዘርፍ አልፈው በፖለቲካና ማኅበራዊ ሕይወትም ርዕሰ ጉዳይ ሆነዋል።
ስለ ሲንጉላሪቲ ማብራሪያ እንዲሰጠን በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በሮቦቲክስ ፒኤችዲውን እየሠራ ያለውን የ‘ጉዞ ቴክኖሎጂስ’ መሥራች ዳንኤል ጌታቸውን ጠይቀናል።
ዘ ሲንጉላሪቲ ምንድን ነው?
“በሰው ሠራሽ አስተውሎት ከባድ ነገር ቢኖር ሲንጉላሪቲ ላይ መድረስ ነው” ሲል ዳንኤል ይገልጸዋል።
እንደው ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማሰላሰልና ማስተዋል ወይም ሰዋዊ ባህሪያት የላቀ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቢመጣ በሚል ነው ስያሜው የተሰጠው።
ቻትጂፒቲ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እጅግ ካስደነቁን፣ ካስደነገጡንም ፈጠራዎች መካከል ነው።
የአሜሪካ ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎችም የዓለም መንግሥታት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሕግና ደንቦች ሲያወጡ ታይቷል።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምን መልክ ይያዝ የሚለው ላይ የተከፋፈለ አቋም አላቸው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰዎች ከሚያገናዝቡት ከበለጠ ወይም የሰው ልጆችን አቅም ማለፍ ከቻለ ያ ነጥብ ሲንጉላሪቲ ይባላል።
“ሲንጉላሪቲ የልኅቀት ደረጃ ነው” ሲል ዳንኤል ያስረዳል።
ለምሳሴ፣ የሰው ልጆች የምንጠቀምባቸው ሰው ሠራሽ አስተውሎቶች እንደ ሰው ሆነው ወይም እንደ ሰው መሆናቸውን እንድናምን አድርገው ከኛ አስተውሎት ሲልቁ ማለት ነው።
በሰው ልጆችና በሰው ሠራሽ አስተውሎት መካከል ያለው መስመር የሚጠፋበት ብለን ልንገልጸውም እንችላለን።
እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ከተከናወነና ከዚያ በኋላም ከኛ የላቀ የማሰላሰልና ውሳኔ የመስጠት አቅም ያለው ነገር እየፈጠርን ከሄድን ለኛ አደጋ አይሆንም? የሚለው አከራካሪ ነው።
“ሰው እስከሚመስለን ድረስ የሚያሳምኑ ፈጠራዎች እያየን ነው። ሲንጉላሪቲ ላይ ባንደርስም መንገዱ ወደዛ ይመስላል” ይላል የቴክኖሎጂ ባለሙያው።
ሲንጉላሪቲ ያስፈራል?
በአንድ በኩል ያለው መከራከሪያ ‘ሰይጣንን ከተኛበት እየቀሰቀስነው ነው’ የሚለው ሲሆን፣ ሌላኛው መከራከሪያ ደግሞ ‘የቴክኖሎጂ ዕድገት ለሰው ልጆች በሚጠቅም መንገድ እየሠራ ነው’ የሚለው እንደሆነ ዳንኤል ያስረዳል።
ጥያቄው ግን የሰው ልጆች በቴክኖሎጂ ግስጋሴ በማናውቀው መንገድ ብንሳሳት ስላለመጥፋታችን ምን ዋስትና አለን? የሚለው ነው።
ዳንኤል፣ “የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ተቋማት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አቅም አሁን እየተረዱት ይመስለኛል። እየፈሩትም ነው” በማለት ይገልጻል።
ሰዎች የሚፈጥሩትን ነገር በአግባቡ እንደሚቆጣጠሩት ቢያስቡም፣ አሁን የሚታየው ከሚጠበቀው በላይ ቴክኖሎጂ ሲሄድ ነው።
“በይፋ የተነገሩም ያልተነገሩም አንዳንድ ተቋማት ከፈጠሯቸው በኋላ ራሳቸው ማብራሪያ ያጡላቸው ነገሮች አሉ። ይሄ አደጋ አለው” ይላል ባለሙያው።
እንደ ምሳሌ የሚሰጠው የሳይበር ጥቃትን ነው። ሰዎች በበይነ መረብ ያለውን ክፍተት ተመልክተው መረጃ ወይም ገንዘብ መመዝበር እንደሚችሉ ሲረዱ የተፈጠረ ነው።
ከሰዎች በላይ የላቀ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይህንን ዲጂታል ዓለም ተረድቶና ክፍተት ፈልጎ በኮምፒውተር ፍጥነት አደጋ ቢያደርስ፣ የሰው ልጅ ሊያደርስ ከሚችለው የከፋ ይሆናል።
አሁን ባንደርስበትም፣ በቀጣይ Artificial general intelligence ወይም AGI የሚባለው ሲመጣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በየፈርጁ ከሰው ልጆች ይልቃል።
“ያኔ ሰዎች የሠራነው ሥራ መልሶ ሰውን የሚያጠፋ ከሆነ ጥቅሙም የሚታየን አይመስለኝም” ይላል ዳንኤል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አደጋውን መቀነስ ይቻላል?
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በኃላፊነት እንዲሠራና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚረዳው የሥነ ምግባር መመሪያ (AI ethics) እንዲከበር ባለሙያዎች ደጋግመው ያሳስባሉ።
ዳንኤል እንደሚለው፣ ሕግ ከሌለ ቀጣዩ የጦር መሣሪያ የሚሆነው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይሆናል።
የቴክኖሎጂ ተቋማት ‘በኃላፊነት’ እንሠራለን ቢሉም በየቤተ-ሙከራው የሚሠራው ነገር ይፋ እስከሚወጣ ድረስ እየተሠራ መሆኑም ላይታወቅ እንደሚችል ይናገራል።
“ቻትጂፒቲ ከመውጣቱ በፊት ኦፕንኤአይ ምን እየሠራ እንደነበር ብዙ ሰው ላያውቅ ይችላል። ገበያ ላይ ሲለቀቁና መጠቀም ስንችል ነው ብዙዎቻችን የምናውቀው። ገበያ ላይ ያልዋሉ መንግሥታት እጅ ሥር ያሉም አሉ። ባለው የፖለቲካ እሰጣ ገባ አንዱ አንዱን ለማጥፋት ከሠራ ለሰው ልጅ ባጠቃላይ አደጋ እየሆኑ ይሄዳሉ።”
ብዙዎች የመጠቀ የአስተውሎት ደረጃ (Superintelligence) ልብ ወለዳዊ ቢመስላቸውም፣ ዳንዴል ግን “የሚቻል ነው” ይላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በቂ መረጃ ተሰጥቶት ማብላላት እስከቻለ ድረስ እየተመነደገ መሄዱን ይቀጥላል።
“ብቸኛው መከላከያ መንገድ በሕግ እንዲገዙ ማድረግ ነው። ቤተ ሙከራዎችና ባለሙያዎች በቅርበት ካልታዩ የሰው ልጆች ባልተረዳነው መልኩ ጥፋቶችን ሳናውቅም ልንፈጥር እንችላለን” ይላል ባለሙያው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ከሰው በላይ ማሠልጠን?
ይሄ ሊፈጠርም ላይፈጠርም የሚችልበት መንገድ አለ።
ሊፈጠር የሚችልበት አቅሙም ቴክኖሎጂውም አለ። ነገር ግን ለሰው ልጆች ጠቃሚው የቱ ነው? የሚለውን መወሰን የሚችሉት የሰው ልጆች ናቸው ሲል ዳንኤል ያስረዳል።
ከሰዋዊ ባሕሪያት መካከል ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊከብዱ ከሚችሉ መካከል አንደኛውን ከፊልም በወሰደው ምሳሌ ያብራራል።
አንድ ሰው በጣም አስቆጥቶን የይስሙላ ስቀን እንሄዳለን። ይሄ ውስብስብ ስሜት ነው። ቁጣም አለው፤ ሳቅም አለው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲህ ያሉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ባሕሪያትን እንዲወርስ ማድረግ ከተቻለ የወደፊቱ ዓለም ፈተና ሊገጥመው ይችላል።
በአንጻሩ ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ለምሳሌ ሰው ገጭተው የሚሄዱ መኪኖችን በተሻለ መቆጣጠር ይችላል። በዚህ ረገድ “ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጥቅማ ጥቅም ስለማይደለልና ስለማይደክም የተሻለ ይሆናል” ይላል ዳንኤል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎችም ታዳጊ የአፍሪካ አገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚኖረው ሚና ቀላል አይሆንም።
በአህጉሪቱ ካለው የአቅምና ግብዓት ውስንነት አንጻር ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በግብርና፣ በሕክምና፣ በመጓጓዣ፣ በትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች መጠቀም የተሻለ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለሙያው እንደሚለው፣ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሰጠው መብት፣ ማን ሠራው፣ ምን መረጃ ተጠቅሞ ሠራው በሚለው ይወሰናል።
“እስከ አሁን ድረስ የዴሞክራሲና የአምባገነን ሥርዓትን አይተናል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ አንድ የመንግሥት ሥርዓት አቅም እስከሚገነባ ድረስ ማድረግ የሚችለው ላይታየን ይችላል” ይላል።
አገራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት በልጠው ለመገኘት ሩጫ ውስጥ የገቡት ለዚህ ነው።
የሰው ልጆች የሚገዙለት ሥርዓት ነው የሚመጣው? የሚለው ጥያቄ ውስጥ ነው።
በሚጠቅመው ሰው ሠራሽ አስተውሎት መጠቀም እንዳለ ሆኖ፣ ሊጎዳ የሚችል ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሳይታወቅ እየመጣ ከሆነ ሕጋዊ ቁጥጥርን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
“እኛ ራሳችን አሁን ባለን ልኅቀት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምን እንደሚሠራ መገመት አንችልም። ምክንያቱም ማሰብም የምንችለው እንደራሳችን ልኅቀት ልክ ስለሆነ” ይላል ዳንኤል።












