ከተማሪዎች የቤት ሥራ እስከ ፕሬዝዳንቶች ንግግር የሚጽፈው ቻትጂፒቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምን ዓይነት መረጃ ይፈልጋሉ? ምን ዓይነት መረጃ ለማግኘት ፈልገው ወደ ኢንተርኔት ደጃፍ ብቅስ ይላሉ?
ከዚህ ቀደም ለጥያቄዎ መልስ ፍለጋ በጉግል መረጃ ማሰሻ ላይ ጽፈው ሰዓታትን አባክነው ከሆነ አሁን ብዙ ነገር ተቀይሯል።
ለጥያቄዎ ፈጣን መረጃ በማቀበል ረገድ ቻትጂፒቲ (ChatGPT ) የትንፋሽዎ ያህል ቅርብ ነው።
ከዚህ በፊት በጉግል የመረጃ ማሰሻ ፈልገው ይማሩት የነበረውን በማሻሻል፣ ክህሎት የሚጠይቀውን ጉዳይ በአጭር ጥያቄ መዳፍዎ ላይ ያስገባል።
ሚሊዮኖች መልዕክቶቻቸውን ለማርቀቅ፣ የዘፈን ግጥሞችን፣ አልፎ ተርፎም የኮምፒውተር ኮዶችን ለመቀመር ይጠቀሙበታል።
ይህ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ለሰፊው ተጠቃሚ ክፍት የሆነው ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ነው።
ዝናው ግን የዕድሜውን ያህል አጭር አይደለም።
በኅዳር 2015 ዓ.ም. 2022 ወደ ሥራ የገባው ቻትጂፒቲ (ChatGPT ) በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን አግኝቶ እንደነበር የድርጅቱ ባለቤት ኦፕን ኤአይ በወቅቱ ገልጿል።
ጉግል እና ማይክሮሶፍት ይህንን አርተፊሻል ኢንተለጀንስ አበልጽገው አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተጣደፉ ነው።
ማይክሮሶፍት ብቻ በቢሊዮኖች ዶላር መድቦ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ቻትጂፒቲ (ChatGPT) እንዴት ይሰራል?
ሁሉም ቻትቦቶች ስሪታቸው ለሚጠየቁት ጥያቄ የሰው ልጅ የሚጠቀምበትን ቋንቋ ተጠቅመው መመለስ ነው።
ቻትቦትን በቀላሉ ለመረዳት የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ናቸው ማለት ይበቃል። እነዚህ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ግን ሰው ሰራሽ የመግባቢያ ችሎታን እንዲያዳብሩ ተደርገዋል።
በዚህም የተነሳ ቻትቦቶች ንግግርንም ሆነ ጽሑፍን ተጠቅመው የሰው ልጆች ከዲጂታል ቁሶች ጋር እንዲግባቡ የሚያግዙ ናቸው።
ከተማሪዎች የቤት ሥራ እስከ ፕሬዝዳንቶች ንግግር ከዚያም አልፎ የኮምፒውተር ኮዶችን ይቀምራል።
በእርግጥ ይህንን ለማድረግ አንድ ተጠቃሚ የራሱ አካውንት መክፈት ይጠበቅበታል። ይኼ ደግሞ ቀላል ነገር ነው።
ከዚያ በኋላ ለሚጠይቁት ነገር ሁሉ በፍጥነት ምላሽ በመስጠት ሀሳብን የሚያቀል መላ ነው።
ቻትጂፒቲ የሚሰጠው ምላሽ ዓለም ያላትን መረጃ በጥቂት ደቂቃዎች በማሰስ እንደ ጥያቄው ዓይነት እና መልክ የሚቀርብ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራት የቴክኖሎጂ ፖሊሲ አጥኚ እና ተንታኝ፣ ብርሃን ታዬ በዚህ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የተደመመችውን ያህል “አስፈሪ ነው” ስትልም ትገልጸዋለች።
የቴክኖሎጂው ዘርፍ መነጋገሪያ የሆነው ቻትጂፒቲን በቀላል ቋንቋ ለማስረዳት የተማረ፣ የሰለጠነ፣ የሰውን ቋንቋ መረዳት ከሚችል ኢንተርኔት ጋር በጽሑፍ መነጋገር መቻል ነው።
“ሁለገብ መረጃ ለመስጠት የሚረዳን አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ ልህቀት) ነው” ትላለች ብርሃን ታዬ።
ብርሃን፣ ቻትጂፒቲ በኢንተርኔት ላይ የሚገኝን ግዙፍ ዳታ ለሚሰጠው ምላሽ እንደሚጠቀም ገልጻ፣ ይኼ ከዚህ ቀደም ከነበሩ የመረጃ ማቀበያ ዘዴዎች ሁሉ እንደሚለየው ታስረዳለች።
ማንኛውም ሰው ቻትጂፒቲን፣ ወዳጁን፣ መምህሩን አልያም አለቃውን በሚያናግርበት ቋንቋ ቢያናግረው ያንን ተረድቶ ምላሽ ይሰጣል።
ምላሹ ግን ስለ የትኛውም ጉዳይ ነው። ከዚህ መለስ የሚባል ዓይነት አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻትጂፒቲን ለመጠቀም የራስ አካውንትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የምታስታውሰው ብርሃን፣ በአብዛኛው አገለግሎቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚገኝ ነው ትላለች።
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የራሱ የሆነ የተለያዩ ሥርዓቶች አሉት የምትለው ብርሃን፣ ይህ ቻትጂፒቲ ሁሉን አቀፍ እና በጽሑፍ ምልልስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ታስረዳለች።
ከዚህም ሌላ የሰው ልጆች እንዴት እንደሚያወሩ፣ ዓረፍተ ነገሮቻቸውን እንዴት እንደሚያዋቅሩ በሚገባ ተምሮ የመጣ በመሆኑ የሚሰጠው ምላሽ በእጅጉ የተዋጣ ነው።
ቻትጂፒቲ በኢንተርኔት ላይ ያለውን ሁሉ ተጠቅሞ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እውቀቱን አደርጅቷል።
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የቋንቋ አጠቃቀሙ እጅጉን የተራቀቀ ነው።
የፊልም ጽሑፍ ማጻፍ የቻሉ፣ ቀልድ እንዲነግራቸው ጠይቀውት በሳቅ ያፈረሳቸው፣ ታሪካዊ ጉዳዮችን አፍታትቶ ያስነበባቸው በዚህ ሁሉ ሥራው ተደምመዋል።
ይህ አርተፊሸል ኢንተለጀንስ በጽሑፍ ትዕዛዝ ተቀብሎ በጽሁፍ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለብዙ ነገር መጠቀም ይቻላል።
የተለየ ነገር ለማግኘት፣ ለጥያቄ መልስ ለመፈለግ፣ የሰዋሰው ግድፈትን ለማስተካከል፣ የተወሰነ መረጃ ለመጨመር፣ የረዘመን ነገር ለማሳጠር...የምንሰጠውን ትዕዛዞችን ተከትሎ ምላሽ ይሰጣል።
ቻትጂፒቲ የሚመልሳቸው መልሶች ከዚህ በፊት ከነበሩት የአርተፊሻል ኢንጀለንስ አይነቶች የተለየ እና በዙሪያው ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ እንደሚያስጋባ ይህም አስፈሪ እንደሚያደርገው ብርሃን ታነሳለች።
የሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቭ ፒንከር ስለ ቻትጂፒቲ “ልንሰጋ ይገባል፣ ግን መረበሽ አያስፈለግም” ሲሉ ይመክራሉ።
ቻትጂፒቲ የተሰኘው የሰው ሰራሽ ልህቀት ሞዴል በግማሽ ትሪሊየን ቃላቶች መሰልጠኑንም አክለው ገልጸዋል።
እነዚህ ቃላት ደግሞ የሚገኙት በኢንተርኔት ላይ መሆኑ የስጋታቸው ምንጭ ነው።
ቻትጂፒቲ እና ሐሰተኛ መረጃ
ቻትጂፒቲ ለሚጠየቀው ጥያቄ በጽሁፍ የሚሰጠው ምላሽ አንድ ተመራማሪ በአግባቡ ሰንዶ እንደሚያቀርበው ያለ ነው የምትለው ብርሃን፣ ነገር ግን በርካታ ነገሮች ከግምት ውስጥ ገብተው በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ትመክራለች።
ተጠቃሚው ምርምር አድርጎ፣ አብላለቶ ማግኘት ያለበትን መረጃ ቻርትጂፒቲ በአጭር ጊዜው ውስጥ አጠናቅሮ መስጠቱ አንዱ ጥቅም ነው።
ነገር ግን “ሁልጊዜ የሚሰጠን ነገር ትክክል ነው ማለት አይደለም” የምትለው ብርሃን፣ ቻትጂፒቲ በጣም ስህተት ያለበት እና ውሸት የሆነ ነገርንም እንደሚያወጣ ትገልጻለች።
ብርሃን ታዬ አክላም “ነውር የሆነ ነገርንም” እንደሚጽፍ ትገልጻለች።
ቻትጂፒቲ መረጃውን የሚሰበስበው ኢንተርኔት ላይ ያሉ ዳታዎችን በሙሉ ሰብስቦ በመሆኑ፣ ኢንተርኔት ላይ ያለ ዳታ ሁሉ ጥሩ እና የተጣራ ነው ማለት እንዳልሆነ ብርሃን ታስታውሳለች።
በኢንተርኔት ላይ ዘረኝነት፣ ጾተኝነት፣ እንዲሁም ለአንድ ሥርዓተ ጾታ የሚያዳላ እና ጥላቻን የሚሰብኩ ጽሁፎች እንደሚገኙ በመጥቀስ፣ እነዚህን ሁሉ ሰብስቦ ለሚጠየቀው ጥያቄ በጽሁፍ ምላሹን እንደሚያቀርብ ትናገራለች።
ስለዚህ ከአዲስ መገለገያ [ቻትጂፒቲ] የሚገኝን መረጃ ሁሉ እያጣሩ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ብርሃን ታነሳለች።
ፕሮፌሰር ስቲቭ ፒንከር ደግሞ ስጋት እንዲገባን የሚያደርገው ሐሰተኛ ዜና በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይፈበረክ በማሰብ ነው ይላሉ። ለዚህ ግን መፍትሄው የመከላከያ እና የተጠየቅ መንገዶችን ማዳበር ነው ሲሉ ይመክራሉ።

የፎቶው ባለመብት, THE WASHINGTON POST
ይህ ብቻ ሳይሆን የቻትጂፒቲ የሥራ ውጤቶችን ሁሉ እንደ መጨረሻ ውጤት መቀበልንም መጀመራችንም ሊያሰጋን ይገባል ይላሉ።
ምክንያቱም ይላሉ ፕሮፌሰር ስቲቭ፣ “ምንም ዓይነት የሚጨበጥ እውነታ እና እውነታን የማሳየት ግብ እንዲሁም ውይይትን እና ንግግርን የማስቀጠል ግብ የለውም” ይላሉ።
ከዚህም ባሻገር ረብየለሽ ነገሮችንም ሊፈጥር እና ሊያሰራጭ እንደሚችል አመልከተዋል።
ሐሰተኛ መረጃ በማሰረጨትም ረገድ የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል የምትለው ብርሃን፣ ከቻትጂፒቲ የሚገኘው መረጃ ሁሉ በንቁ ዐይኖች መጣራት እንደሚኖርበት ትመክራለች።
ብርሃን በምታከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ ይህንን አዲስ ዘዴ ስትጠቀምበት መልካምነቱን እንደተገነዘበች በመጥቀስ፣ ነገር ግን የራሱ የሆኑ ጉድለቶች እንዳሉበትም እንደተገነዘበች የራሷን ተሞክሮ ታነሳለች።
“ጉዳትም አለው ጥቅምም አለው። ዝም ብሎ ጥቅም የለውም ብሎ መወርወር አይቻልም። በቅርቡ እየሰራሁት ላለው ምርምር በዓለም ላይ ያሉ የምርጥ 100 ማኅበራትን እንዲሰጠኝ ጠይቄው ከመቶ 38ቱ ሐሰተኛ ናቸው።”
ቻትጂፒቲ በቂ ዳታዎች በማይገኝበት ሁኔታ ያሉትን መረጃዎች ብቻ መሠረት አድርጎ የራሱን ግምቶች ስለሚያካትት፣ በዚህም የተነሳ ራስን ከስህተት ለመታደግ የሚገኘውን መረጃ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ብርሃን ትመክራለች።
ይህ በዚህ ዘመን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዋነኛ መነጋገሪያ የሆነው ቻትጂፒቲ የሚያርበው መረጃው በኢንተርኔት ላይ ከሌለ ምንም ዓይነት ነገር ሊያገኝ አለመቻሉ ያለበት ክፍተት ነው።
ኢትዮጵያን በተመለከተም በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግርኛ የተጻፉ መረጃዎች እንደሚበዙ የምትጠቅሰው ብርሃን፣ እነዚህ መረጃዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ ካልሆነ በስተቀር መረጃውን ማግኘት አይቻልም።
አክላም በኢንተርኔት ላይ እስከ አሁኑ ሰከንድ ድረስ በርካታ አዳዲስ መረጃዎች የሚካተቱ ቢሆኑም እስከ 2021 (እአአ) ድረስ ያሉትን ብቻ ነው ቻትጂፒቲ ሊያካትት የሚችለው።
ብርሃን ይህም አንዱ የቴክኖሎጂው ክፍተት መሆኑን በመጥቀስ፣ የቅርብ ጊዜ የሆኑ እና በኢንተርኔት የሌሉ መረጃዎችን ማግኘት እንደማይቻል ገልጻለች።
ተማሪዎች እና መምህራንን ያፋጠጠው ቻትጂፒቲ
ብዙ ተማሪዎች የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ወደ ቻትጂፒቲ ይዘው በመምጣት እና ጥያቄውን በማስገባት ምላሽ ያገኛሉ።
ይህንንም ራሳቸው እንደጻፉት አድርገው ለመምህራኖቻቸው ያቀርባሉ።
“ይህ እንደኩረጃ የሚቆጠር ነው” የምትለው ብርሃን፣ ለመምህራንም ቢሆን ተማሪው የሠራውን ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ እርዳታ መለየት አዳጋች መሆኑን ትናገራለች።
ነገር ግን ተማሪዎች ለሚጠበቁባቸው የቤት ሥራዎች ቻትጂፒቲን አትጠቀሙ ማለትም ከባድ መሆኑን ታነሳለች።
የተሰጣቸውን የቤት ሥራ በሙሉ እንዲሰራ ከማድረግ ኢንተርኔትን በሙሉ አስሰው በአንድ ጊዜ ማግኘት የማይችሉትን እና የቤት ሥራቸውን ለመስራት ለመነሻ የሚሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት ቢጠቀሙበት ውጤታማ እንደሚሆኑ ትናገራለች።
አሁን አሁን በእነዚህ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የተጻፉ ጽሁፎችን የሚለዩ ሌሎች የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶች እየተሰሩ መሆኑ ለቁጥጥር አንድ መንገድ ይጎናል።
ብርሃን ይህንን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው፣ ሁሉም መረጃ በኢንተርኔት ላይ በሚገኝበት ዘመን እንዴት አድርገው መጠቀም ይችላሉ የሚለውን ማስተማር ይገባል ትላለች።
ተማሪዎች የምርምር ጽሑፎቻቸውን ሲሰሩ ጊዜያቸውን ለመቆጠብ መረጃዎችን በአንድ ቋት ተጠናቅረው ለማግኘት እና ጠንካራ ሥራ ለመስራት አንዲጠቀሙበት ማድረግ ይቻላል ትላለች ብርሃን።
ቻትጂፒቲ ከሚሰጠው ጥቅም ጎን ለጎን አሰባስቦ የሚሰጠው መረጃ ሐሰተኛ እና መላምት የያዘ ሊሆን ስለሚችል የመጠንቀቅን አስፈላጊነት ብርሃንም ሆነች ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች አጥብቀው ይመክራሉ።












