ማሽን የወደፊቱን ‘መተንበይ’ ይችላል?

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም ከ570 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እንዳሉ ይገመታል።

የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። የገበያ ሁኔታ ተለዋዋጭነት ሌላው ፈተና ነው።

የአየር ሁኔታ እንዲሁም ገበያ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚጠቁም መረጃ ማግኘት የአርሶ አደሮችን ሥራ ያቀላል። ምርት እና ትርፍም ይጨምራል።

የቴክኖሎጂ ሰዎች ግብርናን የሚያዘምኑ መተግበሪያዎች የሚፈጥሩትም ለዚሁ ነው።

ለም መሬት ከመምረጥ አንስቶ፣ የትኛው ሰብል ተመራጭ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት የአየር ሁኔታ እንደሚጠበቅ፣ ምርት ገበያ ላይ ስንት እንደሚያወጣ እና ሌሎችም ተያያዥ ነገሮች በመተግበሪያ እየተገመቱ ነው።

ማሽን ከግብርና በተጨማሪ በንግድ፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በባንክ እና በሌሎችም ዘርፎች ለወደፊት ምን እንደሚጠበቅ ግምቱን ያስቀምጣል።

መረጃ ላይ የተመሠረተ ትንበያ ብለን ልንገልጸው እንችላለን።

በእንግሊዘኛው ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ (Predictive Modelling) ይባላል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ገናና ከሆኑት አንዱ ነው።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ምንድን ነው? ጥቅሙስ ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲሰጡን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ባለሙያው ዶ/ር ዳኛቸው ብሩን ጋብዘናል።

ዶ/ር ዳኛቸው፣ በኳንቲፊ የቴክኖሎጂ ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ዘርፍ መሪ ናቸው።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ምንድን ነው?

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ከማሽን ለርኒንግ ዘርፎች አንዱ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።

“. . . ለምሳሌ የአየር ሁኔታው ምን ሊመሰል ይችላል የሚለውን መገመት ሊሆን ይችላል። ባህሪን መገመት (Behavioural Prediction) ሌላው ምሳሌ ነው። የስቶክ ገበያን የሚገምቱም አሉ።”

የትራፊክ ፍሰት መገመት ሌላው ቀላል ምሳሌ ነው።

ሰኞ 2፡00 ያለውን የትራፊክ ፍሰት መዝግቦ፣ በቀጣይ በሚመጣው ሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት መንገዱ ሊጨናነቅ ይችላል? የሚለውን ይተነብያል።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ የሚሠራው በዲፕ ለርኒንግ (Deep Learning) እንደሆነ ዶ/ር ዳኛቸው ያብራራሉ።

ዲፕ ለርኒንግ አንድ የማሽን ለርኒንግ ስልት ሲሆን፤ ኮምፒውተር አልያም ሌላ ማሽን የተለያዩ ክንውኖችን እንዲፈጽም ትምህርት የሚሰጥ ሂደት ነው።

ያለ አሽከርካሪ የሚጓዝ መኪና ቀይ መብራት አይቶ የሚቆመው፣ አረንጓዴ ሲበራ ደግሞ ጉዞ የሚጀምረው የተሰጠውን ሥልጠና ተመርኩዞ ነው።

ዶ/ር ዳኛቸው እንደሚሉት፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ማሽንን ለማሠልጠን የሚውለው ዳታ ውስን ነበር። ዲፕ ለርኒንግም ገና አልመጣም ነበር።

ዳታ [Data] የሚለውን በግርድፉ የመረጃ ክምችት እንበለው።

ዶ/ር ዳኛቸው ማሽን በቀጣይ የሚፈጠረውን የሚገመትበትን ሂደት እንዲህ ያስረዳሉ።

“. . . ድሮ ዲፕ ለርኒንግ ሳይኖር በፊት ውስን ዳታ ይህንን በመጠቀም ነበር የወደፊቱ የሚተበየው። አሁን ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ በዲፕ ለርኒንግ ቴክኒክ ነው የሚሠራው። አሁን ላይ ብዙ [የኮምፒውተር] ችግሮች የሚፈቱት በዲፕ ለርኒንግ ነው። ምክንያቱም ብዙ ዳታ አለ። ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ የተለያዩ አልጎሪዝሞች አሉት።”

ምን ይጠቅመናል?

ራንደም ፎረስት (Random Forest) እና ፌስቡክ የፈጠረው ፕሮፌት (Prophet) በፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ከሚጠቀሱ መተግበሪያዎች መካከል ናቸው።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ለወደፊት ሊሆን የሚችለውን የመገመት ሂደት ነው።

ለምሳሌ የስቶክ ገበያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት እንዲሁም በሌሎችም ሁነቶች ምክንያት ተለዋዋጭ ነው። ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግን በመጠቀም ገበያውን አስቀድሞ ለመተንበይ የሚሞከረውም ለዚህ ነው።

በኢንሹራንስ ዘርፍ ደግሞ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ወይም ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን ይገምታል።

ኔትፍሊክስ እና አማዞን፤ ምን ፊልም ልንወድ እንደምንችል እንዲሁም ቀጥሎ ምን ምርት ልንገዛ እንደምንችል ለመገመት የሚጠቀሙትም ይህንን መንገድ ነው።

አንድ ሬስቶራንት ሽንኩርት፣ ቲማቲም ወይም ሌላ ግብዓት ከመግዛቱ አስቀድሞ፤ በየትኛው ቀን ምን ያህል ምግብ እንደሸጠ ከመዘገበ በኋላ ለየትኛው ቀን የትኛውን ግብዓት፣ በምን መጠን ልግዛ ብሎ ይገምታል።

ጥቅም ላይ ሳይውል የሚትረፈረፍ ወይም የሚጣል ግብዓትን ይቀንሳል።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ ሰው ምን ሊሸምት ይችላል? ስለ አንድ ጉዳይ ምን አቋም ሊኖረው ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች በማሽን ይገመታሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚገፉ ሐሳቦች እንዲሁም ምርቶች በዚህ ዳሰሳ ላይ የተመረኮዙ ይሆናሉ።

አንድ ሰው ብድር ከመውሰዱ በፊት የባንክ ሒሳቡ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ተመዝኖ፣ ለወደፊት ገንዘብ ቢሰጠው በምን መንገድ ጥቅም ላይ ሊያውለው እንደሚችል እና ብድሩን የመመለስ አቅም ካለው በማሽን ይቃኛል።

ወደ ማሽኑ የሚገባው መረጃ በተለዋወጠ ቁጥር ግምቱም ማሻሻያ ይደረግበታል።

ይህም ማለት ግምቱ ቋሚ ሳይሆን ተለዋዋጭ ነው ማለት ነው።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ ያሰጋናል?

በየትኛውም ዘርፍ ቢሆን ስለወደፊቱ የሚደረግ ትንበያ ጊዜና ገንዘብ እንደሚቆጥብ እንዲሁም ቀድሞ በማንቃት ለዝግጅት እንደሚረዳም ባለሙያዎች ያምናሉ።

በሌላ በኩል ትንበያው የሚመሠረትበት መረጃ መጠን አከራካሪ ነው። ምን ያህል መረጃ ይወሰድ? የሚወሰደው መረጃ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? መረጃው እስከምን ድረስ ለትንበያ ይውላል? የሚሉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

የሰዎች የግል መረጃ ደኅንነት ለአደጋ መጋለጡ ሌላው መከራከሪያ ነጥብ ነው።

ማሽን መረጃ ማብላላት የሚችለው በተሰጠው መረጃ መጠን እና በተቀመጠለት አቅጣጫ ብቻ ነው። ከተሰጠው ስሌት አይወጣም።

ሳይንቲስቶች ካስተማሩት ውጪ ለየዐውዱ የተለያየ አሠራር ሊዘረጋ አለመቻሉ እንደ ክፍተት ይጠቀሳል።

የሰው ልጅ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ቀድሞ ከወሰዳቸው እርምጃዎች የተለየ ውሳኔ የመተግበር የአእምሮ አወቃቀር አለው።

ማሽን ከዚህ በተቃራኒው፣ ምክንያትን ወይም የሐሳብ ለውጥን ለመረዳት ይቸገራል።

ይህም የወደፊቱን ለመገመት ሙሉ በሙሉ ማሽን ላይ ብቻ መተማመን እንዳይቻል ያደርጋል።

ፕሪዲክቲቭ ሞዴሊንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ተመሳሳይ ወይም ተገማች ድርጊቶችን እንዲፈጽም ሊገፋፋው የሚችለውን ያህል፤ በተለያዩ ውጫዊና ውስጥዊ ምክንያቶች ተለዋዋጭም ነው።

ታዲያ ማሽን ይህንን ለውጥ ባገናዘበ ሁኔታ ግምት ያስቀምጣል? የሚለውም አከራካሪ ነው።

ማሽን፤ ታሪካዊና አሁናዊ መረጃ ተጠቅሞ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ውጤቶችን መገመቱ በጎ ሆኖ ሳለ፣ የአካታችነት ጥያቄ ሲነሳበትም ይስተዋላል።

የፆታ፣ የዘር እንዲሁም ሌሎችም መድልዎችን በማስቀጠል የሚተቹት ባለሙያዎች፣ የማሽን ትንበያ ፍትሐዊ እንዲሆን የባለሙያዎች የፆታ እና የዘር ስብጥርን እንደ መፍትሔ ይጠቁማሉ።

ማን ወንጀል ሊፈጽም ይችላል? ብድር ለማን ይሰጥ? የሚሉና ሌሎችም ቁልፍ ውሳኔዎች ለማሽን ከተተዉ፣ ለመድልዎ ሊጋለጡ እንዲሁም ዐውድን ያማከሉ እንደማይሆኑም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አንድ ሰው በቀጣይ ምን ሊሸምት ይችላል? የሚለው ግምት ሊቀመጥ ይችላል።

አንድ ሽያጭ ላይ ተመስርቶ በቀጣይ ሊከናወኑ የሚችሉ ሽያጮችን ሲገምት ሁሌም ትክክል ይሆናል ማለት አይደለም። ለግምት የሚጠቀምበትን መረጃ በየጊዜው የሚከልሰውም ለዚህ ነው።