ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ፡ በጎንደር የጥንዚዛ ‘ራድዮ’ ከመሥራት በሆላንድ ፊሊፕስን ‘ዲጂታይዝ’ እስከ ማድረግ

ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ

የፎቶው ባለመብት, Dagnachew Biru

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ

“ስምንተኛ ክፍልን ካለፍኩ ትምህርት እቀጥላለሁ። ከወደቅኩ ግን የትምህርት ነገር በቃኝ። ነጋዴ እሆናለሁ”

ይሄ ማርሽ ቀያሪ ውሳኔ ነው።

የያኔው ታዳጊ ዳኛቸው ብሩ፣ የዛሬው ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ የሆኑት ከዚህ ውሳኔ በኋላ ነው።

ወቅቱ ኢሕአፓ የተፋፋመበት ነበር።

ወጣቱ ሁሉ ትግሉን ይቀላቀል ነበር።

ያኔ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አንድ ከተማ ከተማሩ በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ሌላ ከተማ መሄድ ያስፈልጋል።

ዳኛቸውም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጨርሰው፣ በትውልድ ቀያቸው አቅራቢያ ወዳለች ከተማ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተጓዙ።

ከጓደኞቻቸው ጋር ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰፈራቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአብዛኛው ኢሕአፓን እየተቀላቀሉ ጫካ ይገቡ ነበር።

“. . .የኛ ታላላቆች [የኢሕአፓ] ወረቀት እያመጡ ሲያነቡ ትዝ ይለኛል። እኔ ግን ወደዛ አልተሳብኩም። ለመግባትም ጥረት አላደረግኩም። ምናልባት ግን ሌሊት ተነስተው ጫካ ሲሄዱ፣ በጣም ቢያነሳሱኝ ኖሮ አብሬያቸው ልሄድ እችል ነበር. . .”

የያኔው ታዳጊ ዳኛቸው በትምህርት ለመግፋት ወይም ለማቋረጥ ገና አልወሰኑም።

በአካባቢያቸው ሁለተኛ ደረጃን ጨርሶ ይህ ነው የሚባል ደረጃ የደረሰ ሰው አላዩም።

ትምህርት የት ያደርሰኛል? ብለው ያሰቡትም ለዚያ ይሆናል።

“. . .እናቴ ጫካ እንዳልገባ ፈርታ ትምህርት እንዳቆም ትጎተጉተኝ ነበር። ያኔ ሁለተኛ ደረጃ የጨረሱ ሰዎች እኔ የምፈልገው ደረጃ ሲደርሱ አላየሁም። አርአያ የለም። ስለዚህ ቤተሰቦቼን እረዳለሁ ብዬ ትምህርቴን ተውኩት። ለንግድ ከደቡብ ጎንደር አዲስ አበባ መሄድ ጀመርኩ። ያኔ አዲስ አበባ ሄዶ እቃ ገዝቶ መመለስ ትልቅ ነገር ነበር። አባታችንም ትልቅ መኪና ነበረው። ጥሩ ገቢ ነበረው። ሄዶ ሄዶ ግን [ያለ ትምህርት መኖር] ሰለቸኝ።”

እንደገና ወደ ስምንተኛ ክፍል የተመለሱበት አጋጣሚ ሕይወታቸውን ለወጠው።

“. . .አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ ስምንተኛ ክፍል ሄጄ ልፈተን ነው አልኩት። ስምንተኛ ክፍል ሳይማሩ አጥንቶ ብቻ መፈተን ይቻል ነበር። ጥሩ ውጤት ካገኘሁ ትምህርት እጣ ክፍሌ ነው ማለት ነው። ጥሩ ውጤት ካላመጣሁ ግን በንግዱ እቀጥላለሁ አልኩት። አዲስ ዘመን ነበር ትምህርት ቤቱ ያለው። ትንሽ አጠናናሁና ስፈተን ከ90 በላይ አመጣሁ. . .

የምኖረው ሐሙሲት ነበር። የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አስደውሎ ውጤቴን ሲያስነገር በጣም ደስ አለኝ። ከመጠን በላይ። ለወላጆቼም በትምህርት ነው የምቀጥለው አልኳቸው። ለመፈተን ባልወስን ሕይወቴ ፍጹም ሌላ አቅጣጫ ይይዝ ነበር።”

የሕይወት መስመራቸውን ባይቀይሩ ኖሮ የዛሬው ዶ/ር ዳኛቸው የት እንደሚሆኑ ማን ያውቃል?

አሁን በኳንቲፊ የቴክኖሎጂ ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ዘርፍ መሪ ናቸው።

ለ30 ዓመት ገደማ በፊሊፕስ ሠርተዋል።

የፊሊፕስ ራድዮን ጨምሮ የተለያዩ የፊሊፕስ ምርቶችን ዲጂታይዝ በማድረግ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ።

በስማቸው የተመዘገቡ ከ57 በላይ የፈጠራ ውጤቶች አሏቸው።

የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ ልኅቀት) የማሽን ለርኒንግ ባለሙያ ናቸው።

የጥንዚዛ ‘ራድዮ’

ደቡብ ጎንደር ነው የተወለዱት።

ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው።

እሳቸው ትምህርት ሲያቋርጡ ታናሽ እህትና ወንድማቸው ቀጥለው በክፍል በልጠዋቸው ነበር።

አባታቸው ባሕር ዳር ቤት ገዝተው ልጆቻቸውን አስገቡ።

እየሠሩ እንዲማሩም የእህል ወፍጮ ቤት ከፈቱላቸው።

“በቅንጡ ሁኔታ ነው ስንማር የነበረው። እየሠራን ገንዘብ እያገኘን፣ ለወላጆቻችንም እንተርፍ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።

ከቴክኖሎጂ ጋር በፍቅር የወደቁት በልጅነታቸው ነው። ያውም በአቅራቢያቸው ወደ ቴክኖሎጂ እንዲገቡ የሚያበረታታ አንዳችም ነገር ሳይኖር።

ከልጅነታቸው ጀምሮ ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚሠራ ለመረዳት ይጓጓሉ።

ሞተር፣ ወፍጮ፣ ራድዮ እንዴት ነው የሚሠራው? የሚለው ያመራምራቸዋል።

በተለይ ራድዮ ይወዱ ነበር። ግማሽ ሕይወታቸውን በፊሊፕስ ያሳለፉትም ለዚያ ይሆናል።

“. . .አባታችን የድሮ ትራንዚስተር ራድዮ ነበረው። እሱን የሚያሽከረከር ኖብ [እጀታ] አለው። ሞገድ የሚገኝበት፣ ድምጽ ከፍና ዝቅ የሚደረግበት ነው። ይሄን አይተን ጭቃ አቡክተን ራድዮ እንሠራና ውስጡ ጥንዚዛ እናስገባለን። ከዚያ ሁለት እጀታዎች አስገብተን ስናሽከረክረው ጥንዚዛው ከውስጥ ጥዝዝዝ ሲል ይሰማል። በቃ ራድዮ ሠራን እንላለን. . .”

የራድዮ ድምጽ እንዴት ይመጣል? የሚለው ያስገርማቸው ነበር። ይሄን ለመረዳት ደግሞ የጥንዚዛ ራድዮ መሥራት በቂ አልነበረም።

“. . .ውስጡን ለማየት የአባታችንን ራድዮ ፈታታሁት። ራድዮው ፊሊፕስ ነበር። ድሮ ራድዮ ቲውን ሲደረግ [ሞገድ ሲስተካከል] ብረቶችና ብረቶች ውስጥና ውስጥ ይተሳሰራሉ። ዲጂታል ከመሆኑ በፊት ሜካኒካሊ በማንቀሳቀስ ነበር። እሱን ልጅ ሆኜ ሳንቀሳቅሰው ትዝ ይለኛል. . .

. . .ስፒከሩ እንዴት እንደሚሠራ ያስደንቀኝ ነበር። ከጀርባው ቫይብሬት የሚያደርገውን ቀድጄ ከውስጥ ያለው ምንድን ነው? ብዬ ሳየው ውስጡ ምንም የለም። ራድዮውን አበላሽቼው አባቴ ተቆጥቷል። ራድዮ በጣም ነበር የሚወደው። እስከሚሞት ድረስ የማታ 2፡00 ዜና ይከታተል ነበር።”

በዚህ መጠን ራድዮ ያመራመራቸው ዶ/ር ዳኛቸው ሲያድጉ ፊሊፕስ ቢገቡ፣ ገብተውም ዓመታት በፊሊፕስ ቢቆዩ ምን ይገርማል?

ፊሊፕስ ሳሉ፣ በስብሰባ መሀልም በሻይ እረፍትም፣ ይህንን የልጅነት ታሪካቸውን ለፊሊፕስ የሥራ ባልደረቦቻቸው ይተርኩላቸው ነበር።

“ያኔ ጃፓኖች ያለ ሹፌር የሚጓዝ መኪና ይሞክሩ ነበር”

ባሕር ዳር ሁለተኛ ደረጃ ሲማሩ ቴሌስኮፕና መሰል ቁሶች ይሠሩ ነበር።

ቤተ መጻሕፍት ካገኙት ኢንሳይክሎፒዲያ በጣም አስደናቂ ነገር እያዩ ለመሥራት ይሞክራሉ።

ወቅቱ ራሳቸውን በራሳቸው ያስተማሩበት እንደሆነ ያስታውሳሉ።

አሜሪካ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እየተጻጻፉ ወደ ዩኒቨርስቲዎቹ ለመግባትም ይሞክሩ ነበር።

ከባሕር ዳር፣ ከኢትዮጵያም አሻግረው ዓለምን ይከታተሉ ነበር። ሕልማቸው ትልቅ ነበር።

የማይረሳቸው፣ ያኔ ጃፓኖች ያለ አሽከርካሪ የሚጓዝ መኪና (self-driving car) ለመሥራት ይሞክራሉ እየተባለ መወራቱ ነው።

በዛ ዘመን ያለ ሹፌር መኪና ሊነዳ ነው የሚለው ዜና ትልቅ ነበር።

ያኔ የቴክኖሎጂ መሪዋ ጃፓን ነበረች። አሜሪካ መሪነቱን የተቀበለችው በቅርቡ ነው።

ኢንተርኔት ስለሌለ መረጃ የሚገኘው በራድዮ ነበር።

ዶ/ር ዳኛቸው በቅርባቸው ይኸው የሚሉት አርአያ ባይኖርም የዓለምን የቴክኖሎጂ እድገት መከታተል አበረታቸው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ባሕር ዳር ከጨረሱ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ አጠኑ።

ስምንተኛ ክፍል ላይ ትምህርት በድጋሚ ከመጀመራቸው በፊት አቋርጠው በነበረበት ወቅት አንድ የአጎታቸው ልጅ መኪና እየፈታታ ሲገጣጥም ያዩት ነበር።

ፈትቶ የሚገጣጥምበት ሂደት አስገረማቸው። ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ለማጥናት የወሰኑትም ለዚህ ነው።

ከአምስት ኪሎ ሲመረቁ ሰቅለው እዛው በአስተማሪነት ቀሩ።

በወቅቱ ፊሊፕስ ለታዳጊ አገሮች ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቶ ሁለተኛ ዲግሪ ያስተምር ነበር።

ዶ/ር ዳኛቸው ዕድሉን አግኝተው ሆላንድ ሄዱ።

ሲጨርሱ ፊሊፕስ የሥራ ቅጥር ሰጣቸውና እዛው አይንዶቨን ቀሩ።

አምስት ዓመት ሠርቼ እመለሳለሁ ብለው ነበር። የተጻፈ የሕይወት መስመራቸው ግን ፊሊፕስ አቆያቸው።

“. . .ከኢትዮጵያ ወጥቶ እዛ ባለው ቴክኖሎጂ መሥራት አስደሳች ነው። ያኔ ኢትዮጵያ አዲስ ነገር ፈጥሮ ለመሥራት የሚያስችል መንገድም መሣሪያም የለም። ፊሊፕስ አዳዲስ ነገር ለመፍጠርና የባለቤትነት መብት ለማውጣት ይመቻል። ያኔ ፊሊፕስ ራሱን እያደሰ ነበር። የማስተርስ ቴሲሴ ለእነሱ የሚጠቅም ስለነበረ ሥራ እንስጥህ ሲሉኝ እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ።

. . .የክፍል ኃላፊው ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ዩኒቨርስቲ አለ ብዬ አላስብም ነበር። እንዴት እንደናንተ ያለ ሰው ይወጣል?’ ያለኝን አልረሳውም። አፍሪካ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚማር ሰው ያለም አይመስላቸውም። ከአፍሪካ ወጥቶ ሌላ ቦታ ሄዶ ተምሮ ሥራ መያዝ ማለት ያህል ፈታኝ እንደሆነ ያሳያል። አሁን የተሻለ ቢሆንም ፈተናው አለ።

በፊሊፕስ ለዓመታት የቆዩት አንድም የልጅነት ሕልማቸው ስለነበረ ነው። በተጨማሪም አዲስ ነገር ለመፍጠር ነጻነት የሚሰጥ መሥሪያ ቤት በመሆኑ።

ዶ/ር ዳኛቸው ፊሊፕስ በሠሩባቸው ዓመታት ከ57 በላይ ፈጠራዎችን በስማቸው አስመዝግበዋል።

ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ ከኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዲግሪ ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Dagnachew Biru

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ ከኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዲግሪ ሲቀበሉ

“ፊሊፕስ የሚሉ እቃ ያውቃሉ”

ፊሊፕስ የጥሩ እቃ ስም!

ፊሊፕስ የሚሉ እቃ ያውቃሉ!

በ1980ዎቹ ስለ ፊሊፕስ የተሠሩ ማስታወቂያዎች ምርቱን ያሞካሻሉ።

በብዙዎች ዘንድ ፊሊፕስ ገናና ስም አትርፏል።

እንዲያውም ጠንካራ ሰው ‘ፊሊፕስ’ የሚል ቅጽል ስም ይሰጠው ነበር።

በዚህ ገናና ተቋም ውስጥ የሚሠራ ልጅ አለኝ ማለት፣ ጓደኛ አለኝ ማለት፣ ኧረ እንዲያው በሩቁ አውቃለሁ ማለትም ያኮራ ነበር።

“. . .ቤተሰቦቼም ጓደኞቼም ፊሊፕስ ነው የሚሠራው ማለቱ ደስ ይላቸዋል። ፊሊፕስ ነው የምሠራው ማለትም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ደስ ይላል። አሁንም ድረስ ፊሊፕስ ጥሩ ስም ስላለው ለፊሊፕስ መሥራት ያኮራል።”

በአሜሪካ፣ ቦስተን ከሦስት ልጆቻቸው እና ባለቤታቸው ጋር የሚኖሩት ዶ/ር ዳኛቸው ዛሬም ድረስ አምፖላቸው ፊሊፕስ ነው።

በሸማቾች ዘንድ ፊሊፕስ በራድዮ፣ በሙዚቃ ማጫወቻ፣ በቴሌቭዥንና በአምፖል ቢታወቅም፤ ፊሊፕስ የበርካታ ምርቶች ባለቤት ነው።

አሁን ከሸማቾች ቁሳቁስ ወጥቶ እንደ ኤምአርአይ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ ማሽን የመሰሉ የሕክምና ቁሳቁሶች ወደማምረት ገብቷል።

እንደ ቀድሞው ራድዮና ቴሌቭዥን ባያመርትም፣ ስሙን ለሌሎች ድርጅቶች ሸጦ ምርቱን ቀጥለውበታል።

ዶ/ር ዳኛቸው ለረዥም ጊዜ የሠሩት ራድዮ፣ ኮምፒውተርና መኪና ውስጥ የሚገባ ቴሌኮንዳክተር በሚያመርት ክፍል ነው።

አሁን ይሄ ክፍል ተሸጦ ራሱን የቻለ ድርጅት ሆኗል።

ድሮ ፊሊፕስ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ስም እንደነበረው ዶ/ር ዳኛቸው ያወሳሉ።

ዛሬ ግን በኤሌክትሮኒክስ ምርት ገበያው ፊቱን ወደ እስያ አዙሯል።

ለመሰናዶና ለቢሮ የሚሆን አምፖል በማምረት የሚታወቀው ፊሊፕስ ላይቲንግ ከዋናው ፊሊፕስ ወጥቶ ራሱን ሲችል ዶ/ር ዳኛቸውም ወደዛ ተዛወሩ።

ከሆላንድ ወደ አሜሪካ አቀኑ።

የፈጠራ ባለቤትነት

ከ57 በላይ በስማቸው የተመዘገቡ የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት መብቶች (patent right) አሏቸው።

ፊሊፒስ ሳሉ ብዙ ጥናት ሠርተዋል።

በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሠሯቸውና ወደ መጨረሻ ላይ የሠሯቸው የየዘመናቸውን ቴክኖሎጂ ይመስላሉ።

ድሮ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራም ተሠርቶ ውጤቱን ለማየት ሳምንት ይስዳል። አሁን ግን በሰከንዶች ይከናወናል።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲሠሩ ጥናታቸው ስለ ዲጂታል ራድዮ ቺፕ ነበር።

ራድዮ ድሮ አናሎግ ነበር።

አናሎግ ማለት ራድዮ በኤኤም ወይም በኤፍኤም ሲሰራጭ፣ ድምጹ የሚተላለፈው በአናሎግ መስመር (circuit) አልፎ ከተለወጠ በኋላ ነው።

ወደ ዲጂታል ሲቀየር ግን ድምጹ ተቀርጾ ዲጂታይዝ ይሆናል። ያ ዲጂታይዝ የሆነው ድምጽም ይሰራጫል።

ዶ/ር ዳኛቸው ራድዮን ወደ ዲጂታል የሚቀይር ሥርዓት ሠርተው ፓተንት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ሥርዓት በጣም ስኬታማ እንደሆነም ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ ደግሞ የቴሌቭዥን ምሥሎችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ ላይ አተኮሩ። ፒኤችዲ የሠሩትም በዚህ ነው።

“ይህን እሠራ የነበረው ዲጂታል ቴሌቭዥን የሚባል ነገር በሌለበት ጊዜ ነበር። ዘመኑን ቀድሞ ማለት ነው” ይላሉ።

ቴሌቭዥን ወደ ዲጂታል ከመጣ በኋላ ደግሞ የዲጂታል ብሮድካስት ሲስተም መሥራት ጀመሩ። ይህም ሌላው ፓተንታቸው ነው።

“የአሜሪካና የአውሮፓ ስታንዳርድ የተለያየ ነው። ስለዚህ እነዚህን በአንድ ላይ ሊሠራ የሚችል ሲስተም ላይ ሠርቻለሁ” ይላሉ።

ሌላው ፓተንት አምፖልን ከኢንተርኔት አገናኝቶ ከመጠቀም ጋር ይገናኛል።

አምፓል ገመድ አልባ ሆኖ በብሉቱዝ ወይም ዋይፋይ ከኢንተርኔት ጋር እንዲገናኝ የማድረግ ሂደት ነው።

እነዚህ ሁሉ የተወጠኑት እውን ከሆኑበት ዘመን ቀድመው ነበር።

ለወደፊት ምን ሊመጣ እንደሚችል አስቀድሞ እንደመገመት ለቴክኖሎጂ ሰው የሚያስደስት ነገር ያለ አይመስልም።

ዶ/ር ዳኛቸውም “ለወደፊት እንደዚህ ሊሆን ይችላል ብሎ አስቀድሞ ማሰብና መሥራት በጣም ነው የሚያስደስተኝ” ይላሉ።

ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ

የፎቶው ባለመብት, Dagnachew Biru

የምስሉ መግለጫ, 30 ዓመት ገደማ በፊሊፕስ የሠሩት ዶ/ር ዳኛቸው

ዲጂታል ዓለም

ፊሊፕስ ወደ ዲጂታል ዓለም ባደረገው ሽግግር ጉልህ አሻራ ካሳረፉ መካከል ናቸው ዶ/ር ዳኛቸው።

አናሎግ ምርቶች ዲጂታል ሲሆኑ የሽግግሩ አካል መሆን ችለዋል።

ይህ ደግሞ ፊሊፕስ ከሚሸጣቸው ምርቶች ባሻገር ማኅበረሰባዊም ዋጋ አለው።

10 ዓመት ወደኋላ ብንመለስ የፊሊፕ አምፖል ከማብራት ማጥፋት ውጭ ምንም አይፈጥርም ነበር።

ይህ ፍዝ (dumb) አምፓል አሁን ዘመነኛ (smart) ሆኗል።

ከኢንተርኔት ጋር ይገናኛል። ሰው ከሌለ ይጠፋል። ሰው ሲመጣ ተከትሎ ይበራል።

ቀለሙ ይለዋወጣል። በስልክ ማብራት ማጥፋት ይቻላል። በአንድ ቢሮ ስንት ሰዎች አሉ? ብሎ የአየር ዝውውር ያሰላል።

ቀድሞ ፊሊፕስ አምፖሎቹን ዲጂታይዝ ለማድረግ ባለሙያዎች ሲመለምል፣ ‘የአምፖል ሥራ እንደሆነ ማብራት ማጥፋት ነው። ተቀጥሬ ብመጣ ምን እሠራለሁ?’ ያሉ መኖራቸውን ዶ/ር ዳኛቸው ዛሬ ሲያስታውሱ በፈገግታ ታጅበው ነው።

ዛሬ አምፖል ዘምኖ፣ ኮሮናቫይረስ የተነሳ ሰሞን ቫይረሱን በአልትራቫዮሌት አምፖል አቃጥሎ ለማጥፋት ተሞክሯል።

የ30 ዓመት የፊሊፕስ ቆይታቸው የተቋጨው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አስበው፣ ዘለግ ያለ እረፍት ላድርግ ብለውም ነው።

አሁን አሜሪካ በሚገኘው የቴክኖሎጂ ተቋም ኳንቲፊ ይሠራሉ።

ገና ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው አልገቡም። ሕልማቸው በአገር ቤት ኤአይ ዘርፍ መሥራት እንደሆነ ግን ይናገራሉ።

“ሕልሜ የኢንተርኔት ኮኔክቲቪቲ [ትስስር] ማበረታታት ነው። የኢንተርኔት ዝርጋታ ከሌለ መሥራትም አይቻልም። ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ትልልቅ ድርጅቶች የሚሄዱትም የተሻለ የኢንተርኔት ዝርጋታ ስላለ ነው።”

“ልጄ ምንም ሳይነካ መኪናው ኤርፖርት አደረሰኝ”

ቴክኖሎጂ ዘምኖ ልቦለዳዊ የሚመስሉ ፈጠራዎች አይተናል። ለወደፊትም እናያለን።

ዶ/ር ዳኛቸውን ከፈጠራዎች ሁሉ ምን ይገርማቸው ይሆን?

“ሁሌም አስገራሚ ፈጠራ የዛሬው ነው” ይላሉ።

የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭነት አንዱን አድንቆ ሌላውን ለመተው ጊዜ አይሰጠም።

ስለዚህ ዛሬ በደረሱበት ዘመን ባዩት ይገረማሉ።

የቴክኖሎጂ ውስብስብነትና ፍጥነት ሁሌም ይደንቃቸዋል።

ታዳጊ ሳሉ ጃፓኖች ያለ ሹፌር የሚሄድ መኪና እየሞከሩ ነው ሲባል ሰምተው መደነቃቸውን አይዘነጉም።

ያኔ የገረማቸው ነገር ዛሬ እውን ሆኖ አይተውታል።

“. . .ሰልፍ ድራይቪንግ ካር [ያለ ሹፌር የሚጓዝ መኪና] በየቦታው ኢሜጅ ሴንሰር [ምሥል የሚያጤን] ካሜራ ተገጥሞለት መንገዱ በዚህ ነው፣ ፍጥነቱ ይሄ ነው ብሎ መሄድ መቻሉ አስደናቂ ነው። ልጄ ተስላ ገዝቶ ወደ ኤርፖርት ሲወስደኝ በጣም ነው የገረመኝ። ልጄ ምንም ሳይነካ መኪናው ኤርፖርት አደረሰኝ።”

ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ

የፎቶው ባለመብት, Dagnachew Biru

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ዳኛቸው በእግር መንሸራሸር ያዘወትራሉ

ተፈጥሮና ቴክኖሎጂ

የቴክኖሎጂ ሰው ቢሆኑም የተፈጥሮ አድናቂ ናቸው። ለነገሩ ቴክኖሎጂና ተፈጥሮ ማን ይጣላሉ አለ?

እንዲያውም ቴክኖሎጂ የተፈጥሮ ቅጂ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ።

ዶ/ር ዳኛቸው ተፈጥሮ እንዴት ይሠራል? ስንራመድ፣ ስንበላ በሰውነታችን ምን ይፈጠራል? ቀልብ (consciousness) እንዴት ይሠራል? የሚሉትን ጥያቄዎች ያመላልሳሉ።

የአንዱ መኖር ለሌላው ሕልውና ሲሰጥ በማየት ስለ ነፍሳት፣ እንስሳት፣ እጽዋትና ከባቢ አየር ጥምረት (ecosystem) ያጠይቃሉ።

ከትንንሽ ነፍሳት እስከ ትልቁ መሬትና ፕላኔቶችም የተዋቀሩበት መንገድ ዶ/ር ዳኛቸውን ግርም ይላቸዋል።

ያው ሳይንስም ሃይማኖትም የየራሳቸውን ማብራሪያ ቢሰጡም አእምሯቸው እነዚህን መላልሶ ያስባል።

ወጣት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ማገዝ (mentorship) ሌላው ደስ የሚላቸው ነገር ነው።

በእግራቸው መንሸራሸርም ያዘወትራሉ።

የሰው ልጅ ኑሮው እንዲቀልና ጤናው እንዲጠበቅ ቴክኖሎጂ ያሻዋል ብለው ያምናሉ።

ቴክኖሎጂ ሰውን ለማጥፋት ሲውልም ይታዘባሉ።

ለምሳሌ በቤተ ሙከራ በሽታ ይፈጠራል። አገር አገርን ይወጋል።

በተቃራኒው አንድ ሰው ሕመሙ ምን እንደሆነ ታውቆ፣ ለዛ ሰው ብቻ የሚውል መድኃኒት (precision medicine) እየተሞከረ ያለበት ዘመን ነው።

ዶ/ር ዳኛቸው ስምንተኛ ክፍልን አልፈው ከንግድ ወደ ትምህርት የተመለሱበት ውሳኔ ምስጋና ይግባውና፣ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን በበጎ ወደፊት እንዲያሻግር ከሚጥሩ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው።