ማሽን ይማራል? ተምሮስ የት ይደርሳል?

ማሽን ለርኒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማሽን ተምሮ፣ ሠልጥኖ አስደናቂ ክንውኖች ሲፈጽምም ታይቷል።

ማሽንን ኮምፒውተር ሳይንቲስቶች ያስተምሩታል። እራሱን በእራሱም ያስተምራል።

እየሠለጠነ፣ ችሎታው እያደገ በሄደ ቁጥር ሰው የሚያዘውን ሥራ በአስደማሚ ፍጥነትና ጥራት ይከውናል።

ማሽን ተምሮ፣ ሠልጥኖ እኛኑ ፈጣሪዎቹን ማስገረም ከጀመረ ሰነባበተ።

አንዳንዴ ስለራሳችን ከምናውቀው በላይ ኮምፒውተራችን ወይም ስልካችን ሲያውቅ ያስደነግጠናል።

የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ መተግበሪያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

አንድ ሰው መቼ፣ ከየት ተነስቶ የት እንደሚሄድ፣ የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚያዘወትር ያውቃል።

መተግበሪያውን ሲከፍቱ ‘መርካቶ መሄድ ፈልገው ነው? በአቅራቢያዎ ያሉት ታክሲዎች እኚህ ናቸው። አሁን ካሉበት ቦታ ወደ መርካቶ ለመሄድ ይሄን ያህል ሰዓት ይወስድብዎታል።'

'መርካቶ የሚያደርስዎት ታክሲ ይህን ያህል ብር ይጠይቅዎታል። በጊዮርጊስ መስመር የትራፊክ መጨናነቅ አለ። ያኛውን አቋራጭ መንገድ መጠቀም ይችላሉ’ የሚሉ መረጃዎች ተጠናቅረው ያገኛሉ።

በመጓጓዣው ዘርፍ ብቻ አይደለም ማሽን ውሳኔ የሚሰጠን።

በጤና፣ በመዝናኛ፣ በፋይናንስ፣ በመዝናኛ ወዘተ ጭምርም እንጂ።

ለመሆኑ ማሽን ለርኒንግ ምን ማለት ነው? ምንን ያካትታል? ዓለምን እንዴት ለወጠ? ስንል ለኤአይ ባለሙያው ዶ/ር ዳኛቸው ብሩ ጥያቄዎች ሰንዝረናል።

በኳንቲፊ የቴክኖሎጂ ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ዘርፍ መሪ ናቸው።

ማሽን ለርኒንግ ምንድን ነው?

ሰው ሠራሽ ልኅቀት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) በውስጡ ከያዛቸው ዘርፎች አንዱ ማሽን ለርኒንግ (Machine Learning) ነው።

“. . .ማሽን ለርኒንግ ስንል፣ ስማርት አልጎሪዝም በመጠቀም፣ የሚገባውን ዳታ በመጠቀም [ማሽን] ጥሩ ሥራ እንዲሠራ ማድረግ ነው” ሲሉ ዶ/ር ዳኛቸው ይገልጹታል።

ከማሽን ለርኒንግ ጋር ከሚገናኙ አልጎሪዝሞች አንዱና ዋነኛ ሆኖ የሚታወቀው ዲፕ ለርኒንግ (Deep Learning) ነው።

ባለሙያው ምሳሌ የሚሰጡት ምሥል፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል እና ንግግርን ማብላላትን (Processing) ነው።

መጀመሪያ ማሽን ብዙ መረጃ (Data) ይገባበታል። ከዚያም ምሥሎችን ዐይቶ ምን እንደሆኑ እንዲያውቅ ይሠለጥናል ማለት ነው።

Image Recognition በመባል በሚታወቀው ሂደት ማሽን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ምሥሎች መካከል ‘ይሄ ቤት ነው፣ ያኛው ውሻ ነው፣ ይህኛው ኮምፒውተር ነው’ ብሎ ይለያል።

ይህን የሚያሳልጡ መተግበሪያዎች (Applications) አሉ።

ማሽኑ ቤት አይቶ ‘ውሻ ነው’ ካለ፣ መሳሳቱ ይነገረውና ቤት እንደሆነ ይገለጽለታል። በዚህ መንገድ በቀጣይ ስህተቱን ያርማል።

“. . .ግሬድየንት ዲሰንት አልጎሪዝም [Gradient Descent Algorithm] በሚባል መንገድ ነው ማሽንን ማሠልጠን የሚቻለው። እራሱን በእራሱም ያሠለጥናል። ሚሊዮን ጊዜ [መረጃ] ይገባል፣ ስሌት ይሠራል፣ ይሠለጥናል። ሠልጥኖ ሲጨርስ ብዙ ነገር ለይቶ ማወቅ ይቻላል።”

ምሥል፣ ተንቀሳቃሽ ምሥልና ንግግር ለይቶ የሚያውቀው ዲፕ ለርኒንግ እያደገና ውስጡ ያሉት ለመማር የሚያገለግሉ ፓራሜትሮች እያደጉ እንደመጡ ባለሙያው ያስረዳሉ።

በጊዜ ሂደት በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ግብዓት አሁን በቢሊዮኖች ደርሷል።

ማሽን የሚመገበው መረጃ በጨመረ ቁጥር፣ ውስብስብነቱ ከፍ ባለም ቁጥር፣ የማሽኑ የመረዳት አቅምም ይጨምራል ማለት ነው።

“ብዙ ዳታ ገብቶ [ማሽን] ሲሠለጥን በጣም የተራቀቀ ውጤት ያለው ማሽን ይታያል። በዚህ መንገድ ሞዴሉ ብዙ ነገር ይረዳል። ይህም ዲፕ ለርኒንግ ነው።” ሲሉ ዶ/ር ዳኛቸው ያብራራሉ።

ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃዎች አብላልቶ ስለ ተጠቃሚዎቹ ማንነትና ፍላጎት መረዳቱ በዚህ ሊካተት ይችላል።

ከአማዞን እቃ ሲገዛ ድርጅቱ ምርት የሚጠቁምበት ሂደትም በዚህ ዘርፍ ይጠቃለላል።

ማሽን ለርኒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማሽን ለርኒንግ ዓለምን እንዴት ለወጠ?

ከ1990ዎቹ ወዲህ ነው ዘርፉ ጎልቶ የወጣው።

ቀድሞ ባከማቸው መረጃ ላይ ተመርኩዞ፣ ማሽን ለርኒንግ ይማራል፣ የወደፊቱን ይተነብያልም።

ዳታ እና አልጎሪዝም ተጠቅሞ እንደ ሰው ይማራል። በጊዜ ሂደት ችሎታውን ያሳድጋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት አሥርታት መረጃ የማከማቸትና የማብላላት አቅም መጨመር ዘርፉ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኔትፍሊክስ ቀጥሎ መመልከት ያለብንን ፊልም ሲጠቁም ያስገርመናል።

ይሄ፣ ቀድሞ ያየናቸውን ፊልሞች ይዘትና ዘርፍ መዝግቦ፣ በቀጣይ ምን ሊያዝናናን እንደሚችል አስቀድሞ የመረዳትና ይህንንም የመጠቆም መንገድ ነው።

ጥቆማውን ተከትለን ፊልሙን ካየን፣ ጥቆማው ትክክል እንደነበር በእጅ አዙር እየነገርነው ነው።

ጥቆማውን መከተላችንን፣ ከዚያ ቀደም ስለእኛ ያከማቸው መረጃ ውስጥ ስለእኛ ተጨማሪ መረጃ አድርጎ ይመዘግበዋል።

አንዱ የማሽን ለርኒንግ አስገራሚ ውጤት የሰው ልጅን ንግግር መረዳት (Speech Recognition) ነው። በድምጽ ለስልክ ትዕዛዝ የሚሰጥበትን መንገድ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

‘እስኪ በአቅራቢያዬ ያለ ቁርጥ ቤት ጠቁሚኝ?’ ስንላት ሲሪ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳትል ትታዘዛለች።

ማሽን ለርኒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የበይነ መረብ ግብይትን ጨምሮ ሌሎችም ድረ ገጽን የተመረኮዙ አገልግሎት ሰጪዎች ከደንበኞቻቸው ጋር እንዲነጋገር ውክልና የሚሰጡት ለማሽን ነው።

በደንበኞች በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይመልሳል። ደንበኞች የትኛውን የምርት ዓይነት ቢሸምቱ የተሻለ ነው የሚለውንም ያማክራል።

ስለ አንደ ጉዳይ ምንነት ለማወቅ ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በጉግል፣ በደክደክጎ ወይም በሌላ የበይነ መረብ መረጃ ማሰሻ ሲጠይቁ፣ ከጥያቄዎ ጋር ተዛማጅ የሆኑ መልሶች በቅደም ተከተል የሚመጡት እንዲሁ አይደለም። ከመልሶቹ ጀርባ ማሽን አለ።

ሌላው በፋይናንስ ዘርፉ ሊፈጸሙ የሚችሉ ማጭበርበሮችን መለየትና መያዝ (Fraud Detection) ነው።

ለምሳሌ ባንኮች አጠራጣሪ የገንዘብ ልውውጦች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ማሽንን በማሠልጠን፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ልውውጦች እንዲጠቁም ያደርጋሉ።

ወደ ጤናው ዘርፍ ስንሄድ ደግሞ ታካሚዎች ያሉበትን የጤና ሁኔታ ማለትም ማገገማቸውን ወይም ሕመም መባባሱን የመከታተል ሚና ሲሰጠው ይስተዋላል።

ወንጀል ሊፈጸም የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ወይም አካባቢዎችን አስቀድሞ በመጠቆም በደኅንነት ዘርፍ ይጠቀሳል።

ግብርናም በማሽን ለርኒንግ መቃኘት ጀምሯል።

አርሶ አደሮች በአነስተኛ ጉልበት የላቀ ምርት የሚያገኙበትን መንገድ ይጠቁማል።

የትኛው ሰብል፣ የት ቦታ ቢተከል ምርታማነትን መጨመር ይቻላል የሚለውን ለማወቅ ያግዛል።

እንደ ትዊተር ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጽሑፎችን በቅደም ተከተል የሚያስቀምጡበት መንገድ ማሽን ለርኒንግን ያማከለ ነው።

ማሽን ለርኒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምን ያሰጋናል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማሽን የሰው ልጅን ዕውቀትና ችሎታ እያስናቀ መሄዱ ጤናማ ነው? መቆም ያለብንስ የቱ ጋ ነው? የወደፊቱ የቴክኖሎጂ ዓለም በምን መንገድ መቃኘት አለበት? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም በሙያተኞች ዘንድ ይንሸራሸራሉ፣ ያከራክራሉም።

አማካሪ፣ ጠቋሚ፣ አድራጊ ፈጻሚ ማሽን ከሆነ የሰዎች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ሌላው ጥያቄ ነው።

እያንዳንዱ የምንጎበኘው ድረ ገጽ መረጃችንን ሙጥጥ አድርጎ መመዝገቡ ሳይነሳ አይታለፍም።

የምንወደውን፣ የምንጠላውን ይመዘግብና ለመረጃ ደላሎች ይሸጣል።

የመረጃ ደላሎች ለአምራቾች ይሸጡና ፍላጎታችን ከግምት ያስገባ ማስታወቂያ ሰለባ ያደርጉናል።

ስለ ጤናችን፣ ስለምንኖርበት አካባቢ፣ ስለ ቤተሰባችን መረጃ ያለ ፈቃዳችን ወይም ያለ እኛ ዕውቅና ይሰበስባሉ።

ሌላ ነጥብ እናንሳ። ለምሳሌ ማሽን ወንጀል ለመከላከል ሲውል፣ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል ብሎ የሚገምተው ማኅበረሰብ መድልዎ የተሞላበት መሆኑ ነው።

ዘርፉ ጥቁርና ቡናማ ሰዎችን ያላማከለ እንዲሁም ፆተኛ እንደሆነ የሚተቸው ያለ ምክንያት አይደለም።

የሥራ ፈላጊዎችን የሥራ ልምድ ማስረጃ (CV) ቃኝቶ ቅደም ተከተል እንዲያወጣ የሠለጠነ ማሽን፣ በፆታ እንዲሁም በቆዳ ቀለም መድልዎ የፈጠረባቸው አጋጣሚዎች እንደ ማሳያ ይጠቀሳሉ።

የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ትግበራ የሚከታተል፣ እንዴት እንደሚሠሩ መርህ የሚያወጣ እንዲሁም መርህ ሲጣስ ተጠያቂነት የሚያሰፍን አካል መኖር አለበት ብለው የሚከራከሩ አሉ።

ትርፍ ማጋበስን ቀዳሚ ግባቸው ያደረጉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞችን በአገር አቀፍ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠያቂ ማድረግን እንደ መፍትሄ የሚያስቀምጡ ባለሙያዎች አሉ።

በእነዚህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ውክልና በዘር፣ በፆታና በሌላም የማንነት መገለጫ ማስፋት ሌላው ምክረ ሐሳብ ነው።

ማሽን ለርኒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images