ዩክሬን የሩሲያ ግዛት ውስጥ ዘልቃ በአሜሪካ ሚሳኤሎች እንድትመታ ባይደን ፈቃድ ሰጡ

ኤቲኤሲኤምኤስ ሚሳዔል

የፎቶው ባለመብት, White Sands Missile Range

ዩክሬን አሜሪካ የሰጠቻትን የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች ተጠቅማ ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ መምታት እንደምትችል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፈቃድ ሰጡ።

እርምጃው አሜሪካ በፖሊሲዋ ላይ ያደረገችው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ አረጋግጠዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አገራቸው ከድንበራቸው አልፈው ለመምታት እንዲችሉ ኤቲኤሲኤምኤስ በመባል የሚታወቁት ሚሳኤሎች ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ለወራት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ዕሁድ በሰጡት አስተያየት "እንዲህ ያሉ ነገሮች አይነገሩም፤ ሚሳዔሎች በራሳቸው ይናገራሉ" ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀደም ሲል የምዕራባውያን አገራት ከእንዲህ ዓይነት እርምጃ እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል። ካልሆነ ግን ኔቶ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ "በቀጥታ መሳተፉን" እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ እስካሁን በውሳኔው ላይ አስተያየት ባይሰጡም ከፍተኛ የክሬምሊን ፖለቲከኞች ግን ውሳኔውን ጦርነቱን እንደማባባስ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የዋሽንግተን በኤቲኤሲኤምኤስ ዙሪያ ያሳለፈችው ውሳኔ ኪዬቭ በነሐሴ ወር ድንገተኛ ወረራ ባደረገችበት በሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ያሉ የዩክሬን ሃይሎች ጥበቃ ብቻ እንዲውል ተወስኗል።

በዚህም ዩክሬን የያዘችውን አነስተኛ የሩሲያ መሬት በመያዝ ወደፊት ለሚደረገው ማንኛውም ድርድር እንደትልቅ መደራደሪያ ልትጠቀመው እንደምትችል የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን አስታውቋል።

በኪዬቭ የሚገኘው የዩክሬን የጸጥታ እና የትብብር ማዕከል ሊቀመንበር ሰርሂ ኩዛን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጆ ባይደን ውሳኔ ለአገሪቱ “በጣም ጠቃሚ” ነው።

“ጦርነቱን የሚቀይር ውሳኔ ባይሆንም ግን ኃይላችንን የበለጠ እኩል የሚያደርግ ይመስለኛል” ብለዋል።

ኤቲኤሲኤምኤስ እስከ 300 ኪሜ መምዘግዘግ ይችላል። ስማቸው ያልተጠቀሰው የአሜሪካ ባለስልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ እና ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት የክሬንን ኤቲኤሲኤምኤስ እንድትጠቀም በባይደን የተፈቀደው የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ ጎን ሆነው በዩክሬን እንዲዋጉ ለፈቀደችበት ውሳኔ ምላሽ እንዲሆን ነው።

ኩዛን በበኩላቸው የእሑዱ ውሳኔ የዩክሬን ሃይሎችን ከሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ለማስወጣት ታስቦ በሩስያ እና በኮሪያ ወታደሮች ሊከፈት ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው ጥቃት አስቀድሞ የመጣ ነው ብለዋል። ጥቃቱ በቀጣይ ቀናት እንደሚፈጸም ይጠበቃል።

እንደዩክሬን ከሆነ በኩርስክ 11 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እንዳሉ ግምቷን አስቀምጣለች።

የፕሬዚዳንት ባይደን ውሳኔ ብሪታንያ እና ፈረንሣይ ስቶርም ሻዶው የተባሉ የረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን ዩክሬን እንድትጠቀም ፈቃድ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

ዩናይትድ ኪንግደምም ሆነች ፈረንሳይ ከባይደን ውሳኔ ጋር በተያያዘ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እና ፕሬዝዳንት ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዘለንስኪ ባለፈው ወር እንዳረጋገጡት ከሆነ የሩሲያ ዒላማዎችን ለመምታት አሜሪካ ያቀረበችውን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን ዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅማለች።

ዩክሬን በምስራቅ ዶኔትስክ ክልል ቀስ በቀስ ወደ ቁልፍ ከተማዋ ፖክሮቭስክ የሚገሰግሱትን የሩስያ ወታደሮችን ለመመከት ለወራት ስትታገል ቆእታለች። ከተማዋ ለዩክሬን ጦረር ዋነኛ የአቅርቦት ማዕከል ናት።

ሞስኮ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የምታደርሰውን ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ጨምራለች። በጥቅምት ወር ብቻ ከ 2 ሺህ በላይ ተጠቅማለች ሲል የዩክሬን ጦር አስታውቋል። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የተመዘገበ ትልቁ ቁጥር ነው።

ቅዳሜ ምሽት ሩሲያ ካለፉት ወራት ወዲህ ትልቁን የተቀናጀ ጥቃት ፈጽማ ቢያንስ 10 ሰዎችን ገድላለች። እንደ ዘለንስኪ ከሆነ 120 ሚሳኤሎች እና 90 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተወንጭፈዋል።

ጥቃቱ እሑድ ማምሻውን ቀጥሎ በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ በመኖሪያ ህንጻ ላይ በተፈጸመ የሚሳኤል ጥቃት ሁለት ልጆችን ጨምሮ ሌሎች ስምንት መሞታቸውን የሱሚ ክልል ባለስልጣናት ዘግበዋል።

በድንበር አካባቢ በምትገኘው ሩሲያዋ ብራያንስክ ክልል የሚገኙ የአገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው እሑድ ምሽት የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት መሰንዘራቸውን ቢገልጹም፤ የአገሪቱ ጦር ግን 26 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መምታቱን አስታውቋል።

አጋሮቿ አገሪቱ ራሷን በብቃት እንድትከላከል የሚያስችል በቂ ድጋፍ አልሰጡኝም ስትል ዩክሬን ለወራት ስትከራከር ቆይታለች።

በጥር ወር ከዋይት ሃውስ የሚለቁት ጆ ባይደን ለዩክሬን ተጨማሪ እርዳታ ለማድረስ ሲሠሩ ቆይተዋል።

ተተኪያቸው ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ተጨማሪ ድጋፉን ይቀንሳሉ ወይም ያቆማሉ የሚል ስጋት አለ። ወታደራዊ ድጋፉ የአሜሪካን ሃብት ማውደሚያ እንደሆነ ገልጸው ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ጠቁመዋል። ይህንን እንዴት እንደሚያሳኩ ግን አልገለጹም።

አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ ነች። ጦርነቱ ከጀመረበት አንስቶ እስከ ሰኔ 2024 መጨረሻ ድረስ 55.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎችን አቅርባለች ወይም ለመላክ ቃል ገብታለች ሲል ኪየል ፎር ዎርልድ ኢኮኖሚ ኢንስቲትዩት የተባለ የጀርመን የምርምር ድርጅት ገልጿል።