በአሜሪካ መነጋገሪያ የሆኑት የትራምፕን ቅንጡ መኖሪያ እና መዝናኛ የሚጠብቁት የሮቦት ውሾች

የሮቦት ውሾች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝደንታዊ ደኅንነት ጥበቃ መሥሪያ ቤት ሴክሬት ሰርቪስ ከሚጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች አንዱ በቅርቡ በቦስተን ዳይናሚክስ የተሠራው “ስፖት” የተባለው የሮቦት ውሻ ነው።

ይህ ሮቦት ከሰሞኑ ፍሎሪዳ የሚገኘውን የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቅንጡ የመኖሪያ እና መዝኛው ስፍራ የሆነው ማራላጎን እየተዘዋወረ ሲጠብቅ ታይቷል።

እነዚህ ውሾች የጦር መሣሪያ አልታጠቁም። በሪሞት አሊያም ቀድሞ በተገጠመላቸው ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው የሚንቀሳቀሱት።

በዚህ ሥፍራው የሚዘዋወሩ ሰዎች እነዚህን የሮቦት ውሾች ከተመለከቱ አንድ ትዕዛዝ መከተል አለባቸው። ይህም ትዕዛዝ “እንዳይነኳቸው” የሚል ነው።

“እኔ እነዚህን የሮቦት ውሾች መንካት የሚመኝ ሰው አላውቅም። ቀርበን እንድንዳብሳቸው የሚያደርግ ምንም ነገር የላቸውም” ይላሉ በሜንሎ ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሑሩ የሆኑት ሜሊሳ ማይክልሰን።

ስፖት የተባለው ይህ የሮቦት ውሻ ማራላጎን እየተዘዋወረ ሲጠብቅ የሚያሳይ ቪድዮ የቲክቶክ መንደር መነጋገሪያ ሆኗል። አንዳንዱ የቲክቶክ ተጠቃሚ ወዶታል፤ ግማሹ ደግሞ ጠልቶታል።

የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ የሚታዩ የምሽት መዝናኛ አቅራቢዎች እነዚህን ውሾች የተመለከተ ቀልድ አሰምተዋል። ጉዳዩ ግን በሳቅ የሚታለፍ አይደለም።

“ተመራጩን ፕሬዝደንት መጠበቅ ትልቁ ዓላማችን ነው” ይላሉ የሴክሬት ሰርቪስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንተኒ ጉግሊየልሚ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ።

በምርጫው ቅስቀሳው ወቅት ትራምፕ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ዒላማ ነበሩ። የመጀመሪያው ባለፈው ሐምሌ በፔንሲልቬኒያ ግዛት በትለር ከተማ የተሞከረባቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ባለፈው መስከረም ማራላጎ ጎልፍ እየተጫወቱ ሳለ የተቃጣባቸው ነው።

ይህ “ስጋት ውስጥ የጣለው” ሴክሬት ሰርቪስ ትራምፕን ለመጠበቅ የሮቦት ውሾችን መጠቀም አስፈላጊ ነው ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል። ውሾቹ ከመቼ ጀምሮ የትራምፕን ቅንጡ መኖሪያ ቤት መጠበቅ እንደጀመሩ የሚታወቅ ነገር የለም።

ቦስተን ዳይናሚክስ የተባለው የቴክኖሎጂ ኩባንያም ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ባይሰጥም ሴክሬት ሰርቪስ ውሾቹን እየተጠቀመባቸው እንደሆነ አረጋግጧል።

እና ለምን ይሆን የፕሬዝደንታዊው ደኅንነት ጥበቃ ክፍሉ (ሴክሬት ሰርቪስ) እነዚህን ውሾች አሁን መጠቀም የጀመረው?

የሴክሬት ሰርቪስ የቀድሞ የደኅንነት አባል የነበሩት ሮን ዊሊያምስ እንደሚያምኑት ትራምፕ ላይ የተፈፀሙት የግድያ ሙከራዎች መሥሪያ ቤቱ ተጨማሪ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሳያደርጉት አልቀሩም።

ዊሊያምስ እንደሚሉት ማራላጎ አብዛኛው ክፍሎ የተጋለጠ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሮቦት ውሾች እጅግ ጠቃሚ ናቸው ይላሉ።

“በጣም ብዙ ቦታ መሸፈን ይችላሉ” የሚሉት የደኅንነት ባለሙያው እነዚህ ሮቦት ውሾች ከዚህ በኋላ በተለያዩ ሥፍራዎች ልናያቸው እንደምንችል ይናገራሉ።

ዊሊያምስ እንደሚያስረዱት እነዚህ የሮቦት ውሾች በሴክሬት ሰርቪስ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ባሉ የሕግ አስከባሪዎች እና ወታደሮች ዘንድ ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል።

የቦስተን ዳይናሚክስ ማስታወቂያ እንደሚያሳየው ለመጀመሪያ ጊዜ “ስፖት” የተባለውን የሮቦት ውሻ የገዛው አንድ ቦምብ አምካኝ ቡድን ነው።

ባለፈው ዓመት የኒው ዮርክ ፖሊስ የሮቦት ውሾችን ለመግዛት መወሰኑን ሲያሳውቅ “ፖሊስ መሰል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ የተዳከመውን ዓለም ማሳያ ነው” የሚል ወቀሳ እንደቀረበበት ዋየርድ የተባለ ድረ-ገፅ ዘግቦ ነበር።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት እነዚህን ውሾች ጥቅም ላይ ማዋሏ ይታወቃል።

ሲክሬት ሰርቪስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሲክሬት ሰርቪስ የዶናልድ ትራምፕ መዝናኛን ሲጠብቅ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስፖት የትም ወጥቶ መግባት የሚችል የሮቦት ውሻ ነው። ደረጃ መውጣት እና መውረድ ይችላል። በጠባብ ቦታዎች እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለበት ያውቃል። በር መክፈትም ይችላል።

ነገር ግን አደጋ ተመልክቶ መለየት መቻሉ ነው የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች 75 ሺህ ዶላር እያወጡ እንዲገዙት የሚያደርጋቸው።

የሴክሬት ሰርቪስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ “የሮቦት ውሾች የደኅንነት [ስለላ] ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው እና የእኛን የደኅንነት እርምጃዎች ለማገዝ የተሠሩ ናቸው” ይላሉ።

ሮቦቱ ካሜራ ተገጥሞለት ነው የሚመጣው። በአካባቢው ያለውን ነገር “በ3ዲ” መቃኘት ይችላል። አልፎም በሙቀት አማካይነት ነገሮችን መለየት ይችላል ይላል የቦስተን ዳይናሚክስ የማስታወቂያ ቪድዮ።

ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚሆነው በሰው ቁጥጥር ነው።

“ሰዎች እጃቸው ላይ ባለ ሪሞት ነው ውሾቹን የሚቆጣጠሯቸው” ይላሉ የጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚሲ ካሚንግስ።

ሚሲ የዩኒቨርሲቲው የአውቶኖሚ እና ሮቦቲክስ ማዕከል ኃላፊ ናቸው። ስፖት የተሰጠውን መመሪያ በመከተል በራሱ መንቀሳቀስ ይችላል ይላሉ።

ከሰዎች እና ኬናይን ከተባሉ የፖሊስ ውሾች በተለየ ሮቦቶቹ በሚያዩት ነገር፣ በሽታ አሊያም በድምፅ ትኩረታቸው አይሰረቅም።

ምንም እንኳ እኒህ የሮቦት ውሾች የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቢገጠምላቸውም በቀላሉ ሥራ ሊያቆሙ አሊያም ሊበላሹ ይችላሉ።

“የፀጉር ቅባት ‘ፊታቸው’ ላይ መርጨት በቂ ነው። ከዚያ በኋላ ካሜራቸው በትክክል መሥራት ያቆማል።”

እርግጥ ነው የትራምፕ መዝናኛ ሥፍራ በሆነው ማራላጎ የታየው ሮቦት የጦር መሣሪያ አልታጠቀም። ነገር ግን መሰል ሮቦቶች የሚያመርቱ ተቋማት የጦር መሣሪያ የሚታጠቅም የሮቦት ውሻ ለማሰማራት ሙከራ እያደረጉ ነው ይላሉ ሚሲ።

“ሰዎች እነዚህን ውሾች ለማስታጠቅ እየሞከሩ ነው” የሚሉት ሚሲ በአንድ የሮቦቲክስ ስብሰባ ላይ አንድ የቻይና ሞዴል ውሻ ክላሽ ታጥቆ እንደመጣ መታዘባቸውን ይናገራሉ።

በማራላጎ የሮቦት ውሾች እየተዘዋወሩ ሲጠብቁ አጠገባቸው የሴክሬት ሰርቪስ የደኅንነት ሰዎች ነበሩ።