በዛምቢያ ገጠር በተነሱት ፎቶ በዓለም ዝነኛ የሆኑት ዘናጭ አያት

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
በዛምቢያ ገጠር ውስጥ የሚኖሩት ማርጋሬት ኮላ በ80ዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኛሉ።
የልጅ ልጃቸው ፋሽን ትወዳለች።
አያትየው ከልጅ ልጃቸው ጋር ልብስ ተለዋውጠው የተነሷቸው ፎቶዎች መነጋገሪያ ሆነዋል።
አያትየው ዘንጠው የተነሷቸው ፎቶዎች በኢንስታግራም ከ225,000 በላይ ወዳጅ አግኝተዋል።
“አዲስ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። እነዚህ ልብሶች ከዚህ ቀደም ተሰምቶኝ የማያውቅ ስሜት ሰጥተውኛል። ዓለምን መቆጣጠር የምችል ይመስለኛል” ብለዋል ማርጋሬት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
የልጅ ልጃቸው የፋሽን ባለሙያዋ ዲያና ካውምባ ፎቶዎቹን መለጠፍ የጀመረችው አምና ነበር።
የምትኖረው ኒው ዮርክ ነው።
ለአባቷ ሙት ዓመት ዛምቢያ ስትመለስ ነበር አያቷን የማዘነጥ ሐሳብ የመጣላት።
ይዛቸው የሄደቻቸውን ልብሶች አያቷ እንዲሞክሩ አደረገች።
አያትየውም “ምንም እየሠራሁ ስላልነበር ልብሶቹን ለመሞከር ተስማማሁ። ስሞት ስለምናፍቅሽ በሕይወት ሳለሁ ትውስታዎች ልስጥሽ አልኳት” ይላሉ።
ግራጫ ሱሪ አልብሳቸው የመጀሪያውን ፎቶ አነሳች።
“አያቴን ቅንጡ ልብስ አልብሼ መንደሯ ውስጥ ፎቶ ማንሳት ጥሩ ሐሳብ ነው ብዬ ጀመርኩት” ትላለች ዲያና።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
ከመዲናዋ ሉሳካ ወጣ ብሎ የሚገኝ መንደር ውስጥ ነው የሚኖሩት።
አያትየው የእንጨት ወንበር ላይ ወይም ፎቴ ላይ ተቀምጠው ፎቶ ተነስተዋል።
ከጀርባቸው የእርሻ ሜዳ፣ የማንጎና በቆሎ ሰብልና ቤቶች ይታያሉ።
“የመጀመሪያውን ፎቶ ስለጥፍ ፈርቼ ነበር። ስልኬን ለአስር ደቂቃ ሳላይ ቆየሁ። ስመለከተው 1,000 ሰዎች ፎቶውን ወደውታል። ማመን ከበደኝ። ሰዎች ተጨማሪ ፎቶዎች እንድለጥፍ ጠየቁኝ” ትላለች ዳያና።
በቀይ አዲዳስ ቀሚስ አያቷን ፎቶ አንስታ ለጠፈች። ከዚያ በኋላም በተከታታይ ፎቶዎቹን መልቀቅ ቀጠለች።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
አያቷ የሚያብረቀርቁ ሀብሎችና ዘውድ አድርገውም ፎቶ አንስታቸዋለች።
“በዓለም ብዙ ሰዎች እንደወደዱኝ ስሰማ ገረመኝ። በዚ ዕድሜዬ ተጽዕኖ ፈጣሪ እሆናለሁ አላልኩም ነበር” ሲሉ ማርጋሬት ይናገራሉ።
የሚለብሷቸው ልብሶች በቀለምም ሆነ በአሠራር የተለዩ ናቸው።
አረንጓዴ የአሜሪካ ካናቴራ፣ ቀይ ቀሚስ፣ የዛምቢያ ሰንደቅ አላማ ያለበት ልብስና ሌሎችም ቅንጡ ልብሶች አድገው ታይተዋል።
የልጅ ልጃቸው የምትወደው ፎቶ ጂንስ በካናቴራ እና ወርቃማ ዊግ አድርገው የተነሱትን ፎቶ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
“ጂንስ ለብሼ ስለማላውቅ ደስ ብሎኝ ስደንስ ነበር” ይላሉ አያትየው።
ዳያና ከ2012 ጀምሮ ስታይሊስት ናት። አያቷ ብርታትና ኩራት እንደሰጧት ትናገራለች።
ውበት የሚያጎላ ልብስና ጌጣ ጌጥ በማብዛት ደስታን መግለጽ ነው አላማዋ። ቀለማቱ ደማቅና ልብሶቹም ጉልህ እንዲሆኑ የምትፈልገውም ለዚህ ነው።
ትኩረት የሚስቡና አንዳንዴም አብረው የሚሄዱ የማይመስሉ የልብስ ዓይነቶች ትጠቀማለች።
የምትመርጣቸው መነጽሮችም በጌጣ ጌጥ የተዋቡ ናቸው።
የእጅ ጓንት፣ ቦርሳ፣ ቀለበትና ጆሮ ጌጥም ትጨምራለች።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
እነዚህን ልብሶችና ጌጣ ጌጦች የምትመርጠው በአያቷ ምክንያት እንደሆነ ዳያና ትናገራለች።
አያቷ ፐርልና ሌሎችም ጌጦች መውደዳቸው ለሷ የፋሸን ምርጫ መነሻ መሆኑን ትገልጻለች።
ሌሎቹ እሷ ከምትወዳቸውና ትርጉም ከሚሰጧት ነገሮች ተነስታ የመረጠቻቸው ናቸው። እነዚህም ፐርል አንገቱ ላይ ያጠለቀ ፍየልን ፎቶ ማንሳት ያካትታሉ።
የሚያኮራትን የበቆሎ ማሳ በፎቶዋ ታሳያለች። አያቷ በትልቅ ኩባሻ ሻይ ሲጠጡና ግዙፍ ወንበር ላይ ተቀምጠውም ይታያሉ።
በዕድሜ የገፉ ሰዎች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ማሳየት ነው ፍላጎቷ።
“ለቀጣዩ ትውልድ አሻራቸውን ያኖራሉ። ችላ መባል የለባቸውም። አንድ ቀን እኛም እንደነሱ ስለምንሆነ እስከመጨረሻው ልንወዳቸው ይገባል” ትላለች።
ከ70 እስከ 96 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አያቶች ያሏቸው የልጅ ልጆች ዳያና አያቶቻቸውን እንድታዘንጥላቸው ቀጥረዋታል።

የፎቶው ባለመብት, Luxury Media Zambia
ማርግሬት ሕልማቸው ማኅበረሰቡ ውስጥ ማን ምን ይለኛል ብለው ሳይጨነቁ በደስታ መኖር ነው።
“ለሠራችሁት ስህተት ራሳችሁን ይቅር በሉ። ያለፈውን መቀየር ባትችሉም የወደፊቱ በእጃችሁ ነው” ይላሉ።
አያትየው ከልጅ ልጃቸው ጋር ያላቸው ቅርበት ጨምሯል። ስለ ሩሯቸውም ያወጓታል።
እስከ 13 ዓመታቸው ተምረዋል። በድህነት ምክንያት ግን ለ30 ዓመት ሰው ተድረዋል።
ሦስት ልጆች ወልደዋል። በኑሯቸው ደስተኛ ስላልሆኑ ይጠጡ ነበር። በስተመጨረሻ ትዳሩን ጥለው ሄደዋል።
አሁንም ድረስ ያ ትውስታ ቢረብሻቸውም አዲስ የሕይወት መስመር ዘርግተዋል።
“አሁን ከእንቅልፌ ስነሳ የመኖር ምክንያት አለኝ። በመላው ዓለም ሰዎች እኔን ማየት እንደሚያስደስታቸው አውቃለሁ” ይላሉ።












