በሱዳን ጦርነት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተገመተው በላይ መሆኑን ጥናት ጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከተገመተው በላይ እንደሆነ አዲስ ጥናት ጠቆመ።
በለንደን ስኩል ኦፍ ሀይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜድስን ስር በሚገኘው ሱዳን ሪሰርች ግሩፕ በተሠራው ጥናት መሠረት፣ ግጭቱ በተጀመረበት የካርቱም ግዛት ከ61,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
በቀጥታ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 26,000 ሰዎች መገደላቸውን ጥናቱ ያመለክታል። በዋነኛነት በሱዳን ሰዎች እየሞቱ ያሉት በሕመምና ረሃብ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።
በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሞተዋል። በተለይም በዳርፉር ግዛት ከፍተኛ ግድያና ዘር ማጽዳት መከናወኑ ሪፖርት ተደርጓል።
ለ19 ወራት የቀጠለው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በዓለም ከፍተኛው ሰብአዊ ቀውስ እንደፈጠረ የተራድኦ ድርጅቶች ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል።
እስካሁን ድረስ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች 20,000 ሰዎች መሞታቸውን ሲገልጹ ነበር።
በአገሪቱ ባለው ውጊያ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ በአግባቡ እየተመዘገበ አይደለም።
ያለፈው ግንቦት የአሜሪካ ልዩ የሱዳን ልዑክ ቶም ፔሪሎ ወደ 150,000 ሰዎች መገደላቸው እንደሚገመት ገልጸዋል።
ዘ ሱዳን ሪሰርች ግሩፕ ጥናቱን ይፋ ያደረገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጦርነቱ ውስጥ የተመድን የመሣሪያ ማዕቀብ በሚጻረር መልኩ የፈረንሳይ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሏል ባለበት ወቅት ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር እየተጠቀመ ያለው የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የጦር ተሽከርካሪ እንደሆነና ይህም ከፈረንሳይ መሣሪያ ጋር አብሮ እንደሚሄድ የመብት ተሟጋች ተቋሙ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአምነስቲ ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ “በፈረንሳይ ዲዛይን የተደረጉና የተሠሩ መሣሪያዎች በሱዳን ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ጥናታችን ይጠቁማል” ብለዋል።
ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ከፈረንሳይ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ከጠቀሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምላሽ ጠይቋል።
ዘ ጋሊክስ የተባለው መከላከያ ሥርዓት የተሠራው በፈረንሳዩ ኬኤንዲኤስ እና ላክሮክስ ሲሆን፣ አጭር ርቀት ዒላማ ለመምታት ይውላል።
አምነስቲ እንዳለው መሣሪያው ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት ለመፈጸም ሊውል ይችላል። የፈረንሳይ መንግሥት መሣሪያውን ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማቅረብ እንዲቆም ማድረግ አለበትም ብሏል።
ይህ የመከላከያ መሣሪያ እንዳላቸው ያረጋገጣቸውን የተጎዱ የጦር ተሽከርካሪዎች ምሥል አጋርቷል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ፈረንሳይ በጦር መሣሪያ ረገድ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው ተገልጿል።
እአአ ከ2014 እስከ 2023 ድረስ የፈረንሳይ ተቋማት ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሣሪያ በመሸጥ 2.6 ቢሊዮን ዩሮ ማግኘታቸውንም አክሏል።
“ተቋማቱ የሰብአዊ መብትን ማክበርና መከበሩን ማረጋገጥ ግዴታቸው ነው” ሲልም አምነስቲ ከሷል።
መሣሪያዎቹን ከሚሠሩ ተቋማትና ከፈረንሳይ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ቢሞክርም እንዳልተሳካለት አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Amnesty International
“ፈረንሳይ ወደ ሌሎች አገራት የምትልከው መሣሪያ ወደ ሱዳን አለመላኩን ማረጋገጥ የማትችል ከሆነ የመሣሪያ ሽያጩን መፍቀድ የለባትም” ብሏል።
ተመድ በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የዘር ማጽዳት እየተፈጸ ነው መባሉን ተከትሎ፣ በ2004 በዳርፉር የመሣሪያ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
ማዕቀቡ ወደሌሎች የሱዳን አካባቢዎችም እንዲስፋፋና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አምነስቲ አሳስቧል።
ለሱዳን ተዋጊ ኃይሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መሣሪያ መሸጥን አገራት እንዲያቆሙም ጠይቋል።
በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና በአብደል ፈታሕ አል-ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ውጊያ ውስጥ ናቸው።
በኃይል ሽኩቻ ሳቢያ ጦርነት ውስጥ ከገቡት ጀነራሎች መካከል በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ኃይል ዳርፉር ውስጥ የዘር ማጽዳት ፈጽሟል ቢባልም ክሱን አጣጥሏል።
ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀሎች ተከሰዋል። ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሞቱበትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበት ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖች አምና ሱዳን ከጎበኙ በኋላ “በየቦታው ረሃብ አለ” ብለዋል።
“በሱዳን ያለው ሁኔታ በጣም አስጊ ነው። ሰዎች በስፋት ተፈናቅለዋል። አሁን በዓለም ቁጥር አንድ ሆኗል። ረሃብም ሌላው አደጋ ነው” ሲሉም ለቢቢሲ አክለዋል።
በሱዳን ያለው ጦርነት፣ ረሃብ፣ መፈናቀልና የበሽታ መስፋፋት በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በዩክሬን ጦርነት ተሸፍኗል።
ዘ ሱዳን ሪሰርች ግሩፕ እንዳለው፣ በካርቱም ከተከሰተው ሞት 90 በመቶው ያልተመዘገበ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ክፍተት ሊኖር ይችላል።
የጥናቱ መሪ ሜይሰን ዳሀብ እንዳሉት፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ስላለው የሞት መጠን መረጃ ማግኘት አልቻሉም።
በዚህ ምክንያትም በአጠቃላይ አገሪቱ በጦርነት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።












