ፑቲን የጦር መሳሪያ እና ወታደሮች ለምትሰጣቸው ሰሜን ኮሪያ አንበሳ እና ድብ በስጦታ አበረከቱ

የፎቶው ባለመብት, Russian Ministry of Natural Resources and Environment
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለሰሜን ኮሪያ የእንስሳት ማቆያ አንበሳ እና ሁለት ድቦችን ጨምሮ 70 እንስሳትን በስጦታ አበረከቱ።
ስጦታው በሞስኮው እና ፒዮንግያንግ መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን ማሳያ ነው ተብሏል።
የሩሲያው የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር አሌክሳንደር ኮዝሎቭ ናቸው እንስሳቱን በዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ይዘው ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት ሲል የሚኒስትሩ ቢሮ በቴሌግራም ገፁ አሳውቋል።
የቴሌግራም ገፁ እንዳስታወቀው ከአንበሳው እና ከሁለቱ ድቦች በተጨማሪ በርካታ እንስሳት ናቸው ወደ ፒዮንግያንግ የተወሰዱት።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት ከሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ እና የተተኳሾች ድጋፍ እያገኘች መሆኗ ሲዘገብ ቆይቷል።
በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ እና ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ ባወጡት መግለጫ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ ወታደሮች ጋር ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ወደ ፒዮንግያንግ ያቀኑት የሩሲያ የአካባቢው ጥበቃ ሚኒስትር የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆን ኡንን ጎብኝተዋል።
ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የዱር እንስሳት በስጦታ መልክ ስታበረክት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ፑቲን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም 24 ያልተዳቀሉ ፈረሶች በስጦታ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ፈረሶቹ ለኪም የተሰጡት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ለሰጠችው የጦር መሣሪያ ምስጋና ለማቅረብ ነው ተብሏል።
ፑቲን እና ኪም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግንኙነታቸው የተጠናከረ ሲሆን ሁለቱም አገራት ከምዕራባዊያን ከባድ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት በዩክሬን ለሚያካሂዱት ጦርነት እርዳታ ይሻሉ። ሰሜን ኮሪያ ደግሞ የሩሲያን የሕዋ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው የሚሳዔል ማብላላት ፕሮግራሟን ታሳድጋለች።
ባለፈው ሰኔ ፑቲን ወደ ሰሜን ኮሪያ አቅንተው ኦፊሴላዊ ጉብኝት ከማድረጋቸውም ባለፈ ከኪም ጋር በደረሱት ስምምነት መሠረት ሁለቱ ሀገራት የሚመጣባቸውን ማንኛውም “ወረራ” በጋራ ለመመከት ቃል ተገባብተዋል።
ፑቲን በጉብኝታቸው ወቅት ሩሲያ የተመረተ አውረስ ሊሞዚን፣ የሻይ ማቅረቢያ እና የጥበብ ሥራ ለኪም በስጦታ አበርክተዋል።
ኪም ጆንግ ኡን የውድ መኪናዎች ወዳጅ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ሜይባክ የተባለው ውድ ሊሞዚን፣ በርካታ ሜርሴዲስ መኪናዎች፣ ሮልስ ሮይስ ፋንተም እና ሌክሰስ የስፖርት መኪና አላቸው።












