ሩሲያ እና ዩክሬን "የኤነርጂ ተኩስ አቁም" ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ትራምፕ አስታወቁ

ፕሬዚደንት ትራምፕ፣ ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ እና ፕሬዚደንት ፑቲን [ ከግራ ወደ ቀኝ)
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬን "የኤነርጂ ተኩስ አቁም" ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለስምምነቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ስምምነቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ገልጸዋል።

ኪየቭ በበኩሏ ውሳኔውን እንደምትደግፍ የገለጸች ሲሆን ሩሲያ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ "ሩሲያ የምትደግፈው ከሆነ ኪየቭም ይህንኑ እንደምታደርግ" ከመግለጻቸው በፊት በውሳኔው መደነቃቸውን ተናግረው ነበር።

ትራምፕ ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ዘይት መሠረተ ልማት ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት እንድታቆም እያሳሰቡ ሰሆን፣ ይህም ሩሲያም ነጭ ናፍጣ ለአሜሪካ እና ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ ያስችላል ብለዋል።

የነጭ ናፍጣ ስምምነቱ ከሩሲያ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በጊዜያዊነት የሚቀለብስ ሲሆን ውሳኔው በርካታ ትችቶችን እያስተናገደ ነው።

ዜሌንስኪም ይህ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ስጦታ ነው" ሲሉ ጠርተውታል።

የአውሮፓ ባለሥልጣናት እና የትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲን ጨምሮ የተወሰኑ የአሜሪካ ፖለቲከኞችም ውሳኔው እንደማይደግፉት ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን በሁለቱ አገራት መካከል ተደረሰ የተባለው ስምምነት ትራምፕ ከአጋማሽ ምርጫ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ያጋጠመውን የነዳጅ ዋጋ ንረት ለመቀነስ ያደረጉት የቅርብ ጊዜ ጥረት ነው።

የአጋማሽ ምርጫው የሚካሄደው ትራምፕ ከኢራን ጋር በተጀመረው ጦርነት ምክንያት የዓለም የነዳጅ በተለይም የናፍጣ ዋጋ በማሻቀቡ እና የፍጆታዎች ዋጋ በመናሩ ለወራት በርካታ ፖለቲካዊ ውዝግቦችን ካስተናገዱ በኋላ ነው።

ዘሌንስኪ ለአክሲዮስ የዜና አውታር ቀደም ብለው በሰጡት አስተያየት የኤነርጅ ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ ለእርሳቸው "ዜና" መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በኋላ ላይ ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ባለሥልጣናቶቻቸው " አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያደረገችውን ንግግር ዝርዝር እንደሚመለከቱ" ገልጸዋል።

ጨምረውም " ዩክሬን የሩሲያ የኤነርጂ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ላለመፈፀም ዝግጁ ናት፤ ሩሲያም በተመሳሳይ ይህንኑ እንደምታደረግ እናስባለን" ብለዋል።

ቢቢሲ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ዋይት ሃውስን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም እንግሊዝ "የፕሬዚደንት ትራምፕን የኤነርጂ ተኩስ አቁም ስምምነት ወዲያውኑ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀረቡትን ጥሪ በጥብቅ እንደምትደግፍ" የተናገሩ ሲሆን ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና አውሮፓ ኅብረትም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ለወራት አንዳቸው በአንዳቸው የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል። አሁንም ጥቃቶች እና ውጊያዎች እንደቀጠሉ ነው።

አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ በጀመሩት ጦርነት ሳቢያ ከዓለም የነዳጅ ምርቶች አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ናፍጣን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦቶች ላይ ከፍተኛ ውስንነቶች ገጥመዋል።

ከፍተኛ የነዳጅ አምራች የሆነችው ሩሲያ እና ዩክሬን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳቸው የሌላኛቸው የኃይል መሠረተ ልማቶችና የትራንስፖርት ተቋማት ላይ የሚፈፅሟቸውን ጥቃቶች አጠናክረው ቀጥለዋል። ይህም ቀድሞውኑም ፈተና የተጋረጠበትን የነዳጅ ኃይል አቅርቦት ገበያ የበለጠ ጫና ውስጥ ከቶታል።