በጂቡቲ የባሕር ዳርቻ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 139 ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, International Organization for Migration
ከጂቡቲ ወደ የመን እየተጓዘ የነበረ ጀልባ ተገልብጦ 15 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 139 ስደተኞች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደኞች ተቋም አስታወቀ።
አይኦኤም ትናንት እሁድ ጥቅምት 1/ 2019 ዓ.ም. በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ጀልባው ሐሙስ ምሽት በኦቦክ የወድብ ከተማ ሲገለበጥ በአጠቃላይ 305 ሰዎችን ጭኖ የነበረ ሲሆን፣ ከስደተኞቹ መካከል በርካቶች የት እንደደረሱ አልታወቀም።
አይኦኤም ቀደም ብሎ በአደጋው 109 ሰዎች መሞቸታውን ያስታወቀ ሲሆን እሁድ ዕለት የ30 ሰዎች አስክሬን በመገኘቱ ቁጥሩ 139 ደርሷል።
ተሳፍረው ከነበሩት 80 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከአደጋው መትረፋቸውንም ድርጅቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
ለመስከረም 29 አጥቢያ ማለትም መስከረም 28/2019 ዓ. ም. ምሽት ላይ ከጂቡቲ የወደብ ከተማ ኦባክ በስተ ሰሜን በምትገኘው ጉህሬ አቅራቢያ ጀልባው መገልበጡን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ስለ ክስተቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ እና ከጂቡቲ ባለሥልጣናት አስተያየት መጠየቁን ዘግቧል።
የአይኦኤም የጂቡቲ የተልዕኮ ኃላፊ አሌክሳንድሬ ኮይሳክ "ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የድንገተኛ ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት የቡድናችን አባላት በቦታው ተገኝተዋል" ብለዋል።
"የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በዚህ የስደት መስመር የሚጓዙ ፍልሰተኞች የሚገጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያስታውስ አሳዛኝ ክስተት ነው" ሲሉም አክለዋል።
የጂቡቲ ባለሥልጣናት የጠፉትን ስደተኞች እየፈለጉ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የስደኞች ተቋም ጠቁሟል።
ከአደጋው ለተረፉ ሰዎች የሕክምና እርዳታ እየተሰጠ ሲሆን፤ ለሞቱ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓትም እየተዘጋጀ ይገኛል።
የተረፉት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የጠቀሰው አይኦኤም፣ ሟቾቹ የየትኛው አገር ዜጎች እንደሆኑ ግን በመግለጫው በግልፅ አላመለከተም።
አደጋው የደረሰው በሳዑዲ አረቢያ በሚደገፈው የየመን መንግሥት እና በሁቲ አማጺያን መካከል ውጊያ ተባብሶ በቀጠለበት ነው።
አይኦኤም ውጊያውን "አሳሳቢ" ብሎ የገለጸው ሲሆን፤ ከመስከረም አጋማሽ አንስቶ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ76,000 ወደ 200,000 ከፍ ማለቱን አስታውቋል።
ባለፉት ሳምንታት በየመን በሚካሄደው ውጊያ ምክንያት ስደተኞች ወደ ጂቡቲ መግባታቸው ይታወሳል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነትም ወደ ቀጣናው ሊሻገር ይችላል የሚል ስጋት እየተስተጋባ ነው።
አይኦኤም ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የገቡ ሰዎች ከ20,000 በላይ መሆናቸውን ገልጿል።
ከጀልባ መገልበጥ አደጋው ለተረፉ ሰዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ፣ ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ እርዳታ እየተሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል።
የአይኦኤም የጂቡቲ የተልዕኮ ኃላፊ አሌክሳንድሬ "የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ከአደጋው ለተረፉ እና የሚወዷቸውን ሰዎች በአደጋው ላጡ ሰዎች መጽናናትን እንመኛለን" ብለዋል።
የጂቡቲ ባለሥልጣናት የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የደኅንነታቸው ጉዳይ አስፈሪ መሆኑን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመግባት በጂቡቲ አድርገው ባል ኤል-መንዳብን ተሻግረው ወደ የመን ይጓዛሉ።
ስደተኞቹ ደኅንነት በማጣት እና እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመቋቋም ሲሉ እንዲሁም ለተሻለ የሥራ ዕድል እና የተረጋጋ ሕይወት እንደሚጓዙ አይኦኤም ጠቅሷል።
በየመን ያለው ውጊያ እየተባባሰ ቢሆንም ስደተኞች በአደገኛው መስመር መጓዝ መቀጠላቸውን ገልጿል።
ስደተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ከሚገጥማቸው ፈተና ባሻገር በየመንም ለጥቃት፣ ለዘፈቀደ እስራት፣ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ብዝበዛ ይጋለጣሉ።
በአውሮፓውያኑ 2025፤ ከ900 በላይ ስደተኞች በዚህ መስመር ለማለፍ ሲሞክሩ መሞታቸውን አልያም መጥፋታቸውን የአይኦኤም መረጃ ያሳያል።
የካቲት 2026 ላይ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ 45 ሰዎች ጠፍተዋል።
ይሄንን አደገኛ መስመር የሚጠቀሙ ስደተኞች ቁጥርም በ18 በመቶ መጨመሩን ተቋሙ ገልጿል።




































