አደገኛው የስደት መንገድ እና እንደወጡ ባሕር ላይ የሚቀሩት ኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያለፈው እሁድ ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም. 157 ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በየመን የባሕር ዳርቻ ሰጥማ ከ60 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
አብዛኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው ተብሎ እንደሚታመን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።
ጀልባዋ የተገለበጠችው በደቡባዊቷ የመን አብያን ግዛት ሲሆን፣ በመጥፎ የአየር ጠባይ ሳቢያ መሆኑ እየተነገ ነው።
በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩ ስደተኞች መካከል ወደ 12 ገደማ ሰዎችን መታደግ ቢቻልም፤ ቀሪዎቹ ደብዛቸው እንደጠፋ የዓለም አቀፉ የስደተኞችን ድርጅት የየመን ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ተጎጂዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሎ እንደሚታመን የገለጸው አይኦኤም ክስተቱን "ልብ የሚሰብር" ሲል ገልጾታል።
ጀልባዋ እየተጓዘች የነበረው በአብዛኛው ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሚጠቀሙበት አደገኛ የባሕር ዳርቻ መስመር ነበር።
ከስደተኞቹ መካከል የ54ቱ አስከሬን በደቡባዊቷ የመን ካንፋር ግዛት ዳርቻ የተገኘ ሲሆን፤ የሌሎች 14 ስደተኞች አስከሬን ደግሞ በአብያን ግዛት ዋና ከተማ ዚንጅባር በሚገኝ ሆሰፒታል አስክሬን ማስቀመጫ መወሰዱን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በዚሁ የስደት መስመር በተደጋጋሚ በደረሱ የጀልባ መስጠም አደጋዎች ምክንያት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕይወታቸው ተቀጥፏል።
ባለፉት ወራት የተከሰቱ የጀልባ መስጠም አደጋዎች
የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ባሕረ ሰላጤው የአረብ አገራት ለሚያቀኑ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች የመን ዋና መሸጋገሪያ ሆና ቆይታለች።
የመን በተለይም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሚያቀኑ በርካታ ተስፋ የቆረጡ ስደተኞች መሸጋገሪያነቷ ቀጥሏል።
በቅርብ ወራት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በጀልባ አደጋ ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዳጡ ወይም እንደጠፉ ከአይኦኤም የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ባለፈው መጋቢት ላይ ከጂቡቲ የተነሱ እና ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎች ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጠው ከ180 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ አይኦኤም አስታውቆ ነበር።
ከሞቱት እንዲሁም የደረሱበት ካልታወቀው ስደተኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።
ከየመን የባሕር ዳርቻ ከመድረሳቸው በፊት ከተገለበጡት ጀልባዎች መካከል አንዷ 31 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ሦስት የመናውያን የጀልባው ሠራተኞችን አሳፍራ እንደነበር የኤፒ ዘገባ ይጠቁማል።
አደጋው የደረሰባቸው ጀልባዎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም የባሕረ ሰላጤው አገራት በሕገ ወጥ መንገድ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ያሳፈሩ ነበሩ።
ጥር 10/2017 ዓ.ም. በየመን ዱባብ ግዛት የባሕር ዳርቻ ላይ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ 20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውም አይዘነጋም።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም አይኦኤም በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት፤ ታይዝ በተባለው ግዛት በሚገኘው ዱባብ አካባቢ አደጋው እንደደረሰ ጠቁሟል።
በአደጋው 11 ወንዶች እና ዘጠኝ ሴቶች ኢትዮጵያውያን የሞቱ ሲሆን፣ ጀልባው በአጠቃላይ 35 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር።
ከአደጋው 15 ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሁለት የመናዊ የጀልባው ሠራተኞች በሕይወት ተርፈዋል።
በጥቅምት 2024 ላይ ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ባሕር ውስጥ ሰጥመው 48 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወሳል።

አይኦኤም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ በሁለት ጀልባዎች ከየመን ተነስተው ወደ ጂቡቲ ሲመለሱ የነበሩት 320 ሰዎች ሲሆኑ፣ ወደ ባሕር ዳርቻው ከመድረሳቸው በፊት ጀልባዎቹን በሚያንቀሳቅሱት የሰዎች አዘዋወሪዎች ተገደው ወደ ባሕሩ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ አሰቃቂ አደጋ መድረሱ ታውቋል።
በክስተቱ ቢያንስ 48 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 75 ሰዎች ደብዛቸው እንደጠፋ መዘገቡ ይታወሳል።
ከአደጋው 197 ሰዎች መትረፋቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቢቢሲ ገልጾም ነበር።
በወቅቱ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደገለጸው፤ በባሕሩ ሰጥመው መሞታቸው የታወቀው እንዲሁም የደረሱበት ያልታወቀው ሰዎች በሙሉ ከየመን ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ስደተኞች ነበሩ።
ከዚህ አደጋ ቀደም ብሎ እሑድ ሰኔ 2/2016 ዓ. ም. አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጣ ቢያንስ 49 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለነፍስ አድን ሠራተኞች እንደተናገሩት፤ ጀልባዋ 260 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረ ሲሆን፣ ለመገልበጥ የበቃችውም በካባድ ነፋስ ምክንያት ነበር።
አይኦኤም በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 31 ሴቶች እና ስድስት ሕጻናት ይገኙበታል ብሏል።
90 ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 145 ኢትዮጵያውያን እና 115 ሶማሊያዊያን በጀልባው ተሳፍረው የነበረ ሲሆን መነሻቸውን ያደረጉት ከቦሳሶ ነበር።
"ከለላ አልባ ስደተኞች"
በ2024 ብቻ አይኦኤም 60,000 ስደተኞች የመን መድረሳቸውን እና ባለፉት አስር ዓመታት ባሕር ላይ ባጋጠሙ አደጋ 3,435 ሰዎች መሞታቸውን እና የደረሱበት እንደማይታወቅም ተቋሙ መዝግቧል። ከእነዚህ መካከል 1,416 ሰጥመው ነው ሕይወታቸውን ያጡት።
በዚህ ጉዞ በተደጋጋሚ በሚደርሱ የጀልባ መስጠም አደጋዎች ሕይወታቸው የሚቀጠፍ ኢትዮጵያውያን በተመለከተ አይኦኤም "በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በድህነት ምክንያት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በየመን በኩል አድርገው ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ይሰደዳሉ። በእነዚህ አገራት የሚጠብቃቸው ብዝበዛ፣ ጥቃት እና ለሕይወት የከፋ ሁኔታ ነው" ሲል ገልጿል።
በየመን በኩል ለሚያልፉ ስደተኞች የጤና አገልግሎት፣ ምግብ፣ መጠለያ እና ከለላ የሚሰጠው ተቋሙ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር እንደማይመጣጠንም ጠቅሷል።
አይኦኤም ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን የሚደረገውን ጉዞ "በጣም የተጨናነቀ እንዲሁም እጅግ አደገኛ ከሆኑ የስደት መንገዶች አንዱ" ሲል ነው የሚገልጸው።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው ሪፖርቶች፤ የስደተኞችን "ተስፋ መቁረጥ እና ተጋላጭነት" በመጠቀም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አደገኛ የጉዞ መስመር እንደሚቀይሱ ጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም በየመን የስደተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል የደረሱ ስደተኞች በሰጡት እማኝነት፤ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች ለማምለጥ በሚል እያወቁ አልያም በግድየለሽነት ስደተኞችን በአደገኛ መንገዶች እንደሚልኩ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, IOM
አደገኛው 'ምሥራቃዊ ኮሪደር'
ከአፍሪካ ወደ የመን ስደተኞች የሚጓዙበት መንገድ 'ምሥራቃዊው ኮሪደር' በሚል ይታወቃል።
እምብዛም ትኩረት ባይሰጠውም በብዛት ስደተኞች ከሚጓዙባቸው መንገዶች አንደኛው ነው።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በዚህ መንገድ ያለፉ ስደተኞች "እጅግ አደገኛ" ሲሉ ነው የገለጹት።
መስመሩ አደገኛ ቢሆንም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚህ መንገድ ይጓዛሉ።
ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር እንደሚለው በየዓመቱ ከአፍሪካ ወደ የመን የሚገቡ ሰዎች 100 ሺህ ይደርሳሉ።
ስደተኞቹ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ እንደ ሶማሊያ እና ጂቡቲ ካሉ የተቀሩት የአፍሪካ ቀንድ አገራትም ዜጎች ይሰደዳሉ።
ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ባለችው የመን ስደተኞች አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ የገንዘብ እና ሌሎችም ብዝበዛዎች እንደሚደርሱባቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በተደጋጋሚ ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም አይኦኤም እንደሚለው፣ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጥያቄያቸው የኢኮኖሚ ቢሆንም፤ በተለይ ከአማራ ክልል እና ከኦሮሚያ ክልል የሚሰደዱት ወጣቶች ግጭት እና እስራትን በመሸሽ ነው ከአገራቸው የሚወጡት።
ወደ የመን ለመሄድ ዋነኛው መንገድ በጂቡቲ በኩል ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ 106 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጂቡቲ ገብተዋል።
ስደተኞቹ ጂቡቲ ድንበር ለመድረስ ለሳምንታት ይጓዛሉ። በአውቶብስ ወይም በእግር ነው ይህንን ጉዞ የሚያደርጉት።
ከዚህ ቀደም በዚህ መንገድ ያለፉ ስደተኞች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ባሕር ዳርቻ ላይ ለሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች 300 ዶላር ከፍለው አደገኛውን የኤደን ባሕረ ሰላጤን ለመሻገር ይሞክራሉ።
ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር እንደሚለው፣ ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከሚደርስባቸው እንግልት እና ብዝበዛ ባሻገር አደገኛውን ባሕር አልፈው በሚደርሱባቸው አገራትም ለስቅይት ይጋለጣሉ።
በ2023 ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት የሳዑዲ አረቢያ የድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መግደላቸውን ጠቁሟል።
ስደተኞቹ እና ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ከየመን ወደ ሳዑዲ እየተሻገሩ ነበር።
በሳዑዲ የቤት ሠራተኛ ሆነው የተቀጠሩ እና በግንባታ ሥራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወደ 750 ሺህ እንደሚጠጉ ይገመታል።
ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር ባወጣቸው ሪፖርቶች ስደተኛ ሠራተኞች በባሕረ ሰላጤው አገራት ተቀጥረው ሲሠሩ ሰብአዊ መብታቸው ይገፈፋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስደትን 'መምረጥ'?
አብዛኞቹ አፍሪካውያን ወጣቶች በአገራቸውና በአህጉሪቱ ላይ ብሩህ ተስፋ እንደማይታያቸውና ስደትን እንደሚመርጡ 'አፍሪካን ዩዝ ሰርቬይ' የተሰኘ ጥናት ያትታል።
ከሦስት ዓመት በፊት የወጣው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በጥናቱ ውስጥ ከተካቱት አፍሪካውያን ወጣቶች መካከል ሁለት ሦስተኛው አገራቸውና አህጉራቸው አፍሪካ እየሄዱበት ባለው አቅጣጫ ላይ ተስፋ ሰጪ ነገር እንደማያዩ ተናግረዋል።
'አፍሪካን ዩዝ ሰርቬይ' በተባለው በዚህ ጥናት ውስጥ ከ15 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ ከ4,000 በላይ ወጣቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከተቀረው የአፍሪካ ቀንድ የሚደረግን ስደት ከድህነት፣ ከእርስ በእርስ ጦርነት፣ በፖለቲካ አቋም ምክንያት ዒላማ ከመደረግ፣ ከሰብአዊ መብት ረገጣና ከሌሎችም ተያያዥ ሁነቶች ጋር ያስተሳስሯቸዋል።
በዓለም ላይ ስደተኞች ከሚያቋርጧቸው አደገኛ መስመሮች መካከል ኢትዮጵያውያን የሚጓዙበት ይጠቀሳል።
ለብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ የመድረስ ሕልም የሚጀምረው በራሳቸው አህጉር በሚያደርጉት ጉዞ ሲሆን፣ ይህም አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሰሜን አፍሪካ አገራት የሚወስደው ረዥሙ የሰሃራ በረሃ ጉዞን ያካትታል።
አይኦኤም በአውሮፓውያኑ ከ2014 - 2022 ባለው ወቅት ለ5 ሺህ 400 ሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሰሃራ መሻገሪያ መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህ በረሃ በድካም እንዲሁም በምግብና በውሃ እጦት ስደተኞች ይሞታሉ። በአካባቢው ያሉ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና የድንበር ባለሥልጣናትም በስደተኞች ላይ እስከ ሞትና የአካል ጉዳት የሚያደርስ ጥቃት ይፈጽማሉ።
ሌላው የአደገኛ የስደት መስመር የሜዲትራንያን መስመር ሲሆን፤ አይኦኤም ለስደተኞች "ገዳይ" ሲል ይገልጸዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሜድትራንያን ባሕርን ለማቋረጥ የሞከሩ ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።
ባሕሩን የመሻገር ሙከራዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከናወኑት በተጨናነቁ ጀልባዎች ወይም እንደ የጎማ ጀልባዎች ባሉ የትራንስፖርት መንገዶች ሲሆን ይህም ጉዞውን አደገኛ እና ገዳይ ያደርገዋል።
ጀልባዎቹን የሚቆጣጠሯቸውም ሆነ የሚያሽከረክሯቸው የወንጀል ቡድኖች ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ናቸው።















