በዓለም ላይ ስደተኞች የሚያቋርጧቸው አደገኛ መስመሮች

በሜድትራንያን ባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በባለፉት ሳምንታት ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ለማቋረጥ በሞከሩ ስደተኞች ላይ ሁለት አሳዛኝ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት አርብ ከሞሮኮ ወደ ስፔን ለመግባት በሚል ሜሊላ የተሰኝችውን የድንበር አጥር ለመሻገር ከሞከሩት መካከል ቢያንስ 23 ሰዎች ሞተዋል።

ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ሦስት ቀናት በኋላ በአሜሪካ ሳን አንቶኒዮ ከተማ ፖሊስ አሽከርካሪ በሌለው የጭነት መኪና ውስጥ ስደተኞች መሆናቸው የሚታመኑ ቢያንስ 46 ሰዎች ሞተው አግኝቷል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተፈጠረው መስተጓጎል በርካታ አገራት ጠበቅ ያሉ ገደቦችን መጣላቸውን ተከትሎ በዓለም አሉ በሚባሉ የስደት መስመሮች ላይ የሚደረጉ ጉዞዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ይመስላል።

በእነዚህ አደገኛ መስመሮች ላይ የሚደረገው ጉዞ ቁጥር ማሻቀብም የሚሞቱ ሰዎችንም ቁጥር ይጨምራል በሚል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

እንደ አሜሪካ ወይም የአውሮፓ አገራት ለመድረስ ከሞከሩት መካከል ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ሲል የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ይገምታል።

ትክክለኛው የሟቾች እና የጠፉ ሰዎች ቁጥር ከዚህም የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ተቋሙ ያምናል።

ለመሆኑ በዓለም ላይ ለስደተኞች በጣም አደገኛ የሆኑት መስመሮች የትኞቹ ናቸው? ለምን?

በሜድትራንያን ባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መካከለኛው ሜዲትራንያን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም አይኦኤም የሜድትራንያንን መስመር ለስደተኞች ገዳይ በሚል ይፈርጀዋል። መረጃዎችንም ዋቢ በምናደርግበት ጊዜ ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሜድትራንያን ባሕርን ለማቋረጥ የሞከሩ ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ይህም ቁጥር ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ያለው ነው።

ባሕሩን የመሻገር ሙከራዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከናወኑት በተጨናነቁ ጀልባዎች ወይም እንደ የጎማ ጀልባዎች ባሉ የትራንስፖርት መንገዶች ሲሆን ይህም ጉዞውን አደገኛ እና ገዳይ ያደርገዋል።

ጀልባዎቹን የሚቆጣጠሯቸውም ሆነ የሚያሽከረክሯቸው የወንጀል ቡድኖች ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ናቸው።

በመካከለኛው የሜድትራንያን መንገድ ወደ አውሮፓ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች ከሊቢያ ጋር ዋና መነሻ በሆነችው ቱኒዚያ ባሕር ላይ ሰጥመው ለሚሞቱ ሰዎች የተዘጋጀ መካነ መቃብር አለ።

“እነዚህን መቃብሮች እዚህ ስፍራ ማየቴ በጣም አሳዝኖኛል” ስትል ከቱኒዝያ ወደ አውሮፓ ጉዞዋን ለማድረግ ተስፋ ያደረገችው ቪኪ የመቃብር ስፍራውን በመጎብኘት ላይ እያለች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግራለች።

አክላም “እነዚህን መቃብሮች ሳይ የሜድትራንያን ባሕርን መሻገር እንደምፈልግ እርግጠኛ አይደለሁም” ስትል ታስረዳለች።

እንደ አይኦኤም ያሉ ተቋማት ስደተኞች አደገኛ መስመሮችን ከመከተል የሚያስቆማቸው ሁኔታ የለም የሚል ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

“በማዕከላዊ ሜዲትራንያን ባሕር ላይ የሚደረጉ የስደተኞች ጉዞዎች ቀጥለዋል። ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው በዓለም ላይ በዚህ እጅግ አደገኛ የባሕር መሻገሪያ ላይ እያጋጠመ ያለው ከፍተኛ ሞት መቀጠሉ ነው። በአገራት ተጨባጭ እርምጃ ካልተወሰደ ሕይወትን ማጥፋቱን ይቀጥላል” በማለት የአይኦኤም ቃለ አቀባይ ሳፋ መሸሊ ተናግረዋል።

የአውሮፓ የድንበር እና የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ኤጀንሲ ፍሮንቴክስ ሪፖርት መሰረት ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ በዚህ መስመር ለመሻገር የሞከሩ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መታደግ ተችሏል።

የሰሃራ በረሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ ውስጣዊ መስመሮች

ለብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ የመድረስ ህልም የሚጀምረው በራሳቸው አህጉር በሚያደርጉት ጉዞ ሲሆን፣ ይህም አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሰሜን አፍሪካ አገራት በሚወስደው መንገድ ረጅሙን የሰሃራ በረሃ ጉዞን ያካትታል።

አስከፊው የበረሃ ሁኔታ ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል። አይኦኤም በአውሮፓውያኑ 2014 - 2022 ባለው ወቅት ለ5 ሺህ 400 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሰሃራ መሻገሪያ መሆኑን ጠቁሟል።

“በበረሃ ውስጥ ሰዎች ሲሞቱ ይታያል። አንዳንዶች ጉልበታቸው ዝሎ በድካም ላይመለሱ አሸልበዋል። አንዳንዶች ደግሞ በውሃ እጦት ይሞታሉ” በማለት በሰሃራ በረሃ የተሻገረው አብዱላሂ ኢብራሂም የተባለ ስደተኛ ያየውን አስመልክቶ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

በስደተኞች ላይ ሌላው የተደቀነው ትልቅ ስጋት በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መኖራቸው ነው።

“በቀጠናው ህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ድንበር ባለሥልጣናት በስደተኞች ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት እንዲሁም ሞት በሰሃራ በረሃ በተመዘገቡ የስደት መስመሮች ከፍተኛው ነው” ሲል አይኦኤም በቅርብ ጊዜ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

ስደተኞች ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ለመሻገር ሲሞክሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ-ሜክሲኮ የድንበር መሻገሪያ

በአሜሪካ አህጉር ውስጥ ያሉ የስደት መስመሮች መጨረሻው ወደ አሜሪካ ለመድረስ ብቻ ባይሆኑም፣ በአብዛኛው ግን አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ላቀዱ የመጨረሻው መዳረሻ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል ያለው ድንበር አስቸጋሪ ፈተናን የጋረጠበት ነው። ቀጠናው በረሃማ አካባቢዎችን ጨምሮ ምቹ ባልሆነ አቀማመጡ የበርካታ ስደተኞችን ጉዞ የሲዖል አድርጎታል።

ስደተኞች በአብዛኛውን ሁለቱን አገራት በሚያስተሳስረው አደገኛው የሪዮ ግራንዴ ወንዝ በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት ይሞክራሉ።

በዚህ መስመር መስመጥ ከዋና ዋናዎቹ የሞት መንስኤዎች አንዱ ሲሆን አይኦኤም ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሞቱ ይገምታል።

የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመሸሽ የሚሞክሩት ደግሞ በተሽከርካሪዎች ውስጥ በመደበቅ በሳን አንቶኒዮ ሞተው እንደተገኙት አይነት የተለያዩ አደጋዎችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ።

“በቅርቡ ወደ አሜሪካ በሚደረጉ የፍልሰት መስመሮች ላይ ከፍተኛ የሰው ሕይወት የጠፋባቸው ሌሎች ክስተቶች ነበሩ” በማለት የአይኦኤም ቃለ አቀባይ ሳፋ መሴህሊ ያስረዳሉ።

ቃል አቀባዩ ከሚጠቅሷቸው መካከል ባለፈው ዓመት ቺያፓስ፣ ሜክሲኮ ውስጥ ስደተኞች ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ በደረሰበት አደጋ 56 ስደተኞች ሞተዋል።

የሮሂንጋ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስያ መስመሮች

እንደ አይኦኤም ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2020 በዓለም ዙሪያ ከ10 ስደተኞች መካከል ከ4 በላይ የሚሆኑት በእስያ የተወለዱ ሲሆን አህጉሪቱ በርካታ ዋና የስደተኛ መንገዶች እንዳሏትም ተገልጿል።

በተቋሙ መረጃ መሰረት ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች በእስያ ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል።

አብዛኞቹ የሞቱት የሮሂንጋ እና የባንግላዴሽ ስደተኞች ሲሆኑ የቤንጋልን የባሕር ወሽመጥ እና የአንዳማን ባሕርን አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገራት ወይም ወደ አውሮፓ ለመድረስ ይሞክራሉ።

የተለያዩ መስመሮችን ለማቋረጥ በሚሞክሩበት ጊዜ የሚገጥማቸው ፈተና በእጅጉ ከባድ ነው።

“ተርበን ነበር፣ ውሃ ስላልነበረ በጥም ተቃጠልን። ምግብ የለም፣ ሩዝ የለም፣ መብላት አልቻልንም። በዚህም ሰቆቃ ለአንድ ወር ያህል በባህር ላይ እንደዚህ ነው የተጓዝነው” በማለት የሮሂንጋ ስደተኛ የሆነው የ37 ዓመቱ መሐመድ ኤሊያስ ለፈረንሳይ የዜና አገልግሎት ተናግሯል።

መሐመድ ሲጓዝበት የነበረው ጀልባ ከደረሰበት አደጋም የሕንድ የባሕር ኃይል ታድጎታል።

ልክ እንደሌሎች የስደተኞች መስመሮች በእነዚህ መስመሮች የሚያልፉ ስደተኞችም አብዛኛውን ጊዜ የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ቡድን ብዝበዛ ሰለባ ይሆናሉ።

ሌላው ችግር ያለበት የስደተኞች መሻገሪያ መስመር በኢራን እና በቱርክ መካከል ያለው ድንበር ሲሆን ታሊባን ወደ ሥልጣን መመለሱን ተከትሎ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የአፍጋኒስታን ስደተኞች በብዛት ሲጎርፉ ይታያል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) እንዳስታወቀው ከሁለት ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን በኢራን እና በአካባቢው አገራት ውስጥ በስደተኛነት ተመዝግበዋል።