ዓለም አቀፍ ዕውቅና እና ሽልማት ያገኘችው ሞዴል ሰላማዊት ለምን ስደትን መረጠች?

የፎቶው ባለመብት, Selamawit
ሰላማዊት ተክላይ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ የቁንጅና ውድድሮች ተሳትፋ በርካታ ሽልማቶችን አግኝታለች።
ሚስ ግራንድ ኢንተርናሽናል፣ ሚስ ኢትዮጵያ፣ ሚስ ቨርጅን ከተሳተፈችባቸው የቁንጅና ውድድር መድረኮች መካከል ናቸው።
በተሳተፈችባቸው መድረኮችና በሄደችባቸው አገራት ሁሉ የአገሯን ባህልና ፀጋ አስተዋውቃለች፤ የአገሯ ባንዲራ ከፍ እንዲል አድርጋለች።
ይሄ ሁሉ የሆነው ታድያ የስደት ጉዞ ከመጀመሯና ከሞት አፋፍ ለጥቂት ከማምለጧ በፊት ነው።
የምትወደውና በበርካታ አገራት የደመቀችበት የሞዴሊንግ እና የዲዛይን ሙያዋ አሁን ላይ እንደገና ብትኖረው የምትመኘው፤ ያለፈ የሕይወቷ ምዕራፍ ሆኗል።
ሰላማዊት የአገሯን ፓስፖርት እያሳየች ከአገር አገር እንዳልተዘዋወረች፣ አሁን በፍርሃትና በስጋት መካከል ተወጥራ በባዕድ አገር ኑሮዋን “ሀ” ብሎ መጀመር ግድ ሆኖባታል።
ይህቺ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሽልማትና ክብር የተጎናፀፈች ሞዴል ለምን ስደትን መረጠች?…
ስቃይንና የሞት አፋፍን አልፌ እንግሊዝ ውስጥ በስደት እየኖርኩ እገኛለሁ። ከትግራይ እስከ እንግሊዝ ድረስ ያሳለፍኩት የስደት ጉዞ ግን ቀላል አልነበረም።
ስደት የወጣሁት በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ስደት የሚባል ሃሳብ ለአንድ ቀንም እንኳ በአእምሮዬ ሽው ብሎ አያውቅም።
ከቤታችን ሴት እኔ ብቻ ነኝ፤ የተቀሩት ሦስቱም ወንዶች ናቸው።
የተወለድኩት፣ ያደግኩት እና የተማርኩት መቀለ ነው። ኮምፒዩተር ሳይንስ ባጠናም ከልጅነቴ ጀምሮ ሳልመው ወደ ነበረው ሞዴልነት አዘነበልኩ። እናም ሞዴል፣ ተዋናይ እና ዲዛይነር ነኝ።
ከልጅነቴ ጀምሮ ዲዛይነር ለመሆን አልም ነበር። ራሴ የመረጥኳቸው ልብሶችን እና ቅድ እየሰራሁ እለብስ ነበር። ፋሽን ስለሚመስጠኝ የእናቴን ልብሶችና ረጃጅም ጫማዎችን ሳደርግ አስታውሳለሁ።
ቤተሰቦቼ ከሞዴሊንግ ይልቅ ትምህርቴ ላይ ትኩረት እንዳደርግ ይፈልጉ ነበር። ግን ውስጤን የገዛው የሞዴሊንግ ህልም አሸነፈኝ።
ገና የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ መቀለ ውስጥ በተዘጋጀ የቁንጅና ውድድር 'ወይዘሪት ድንግል መቀለ’ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳደርኩ። ከውጤቱ በላይ ያስደሰተኝ የቀሰምኩት ልምድ ነበር።
ከዚያ በኋላ በ‘ወይዘሪት ሓምለዋይ ልምዓት’ እና በ‘ወይዘሪት ሃይስኩል’ ውድድሮች ተሳትፌ በጥሩ ደረጃ አጠናቀቅኩ። እንደዚያ እያልኩ የሞዴሊንግ ሥራውን ቀጠልኩበት። የሞዴልነት ዳኛና አሰልጣኝ ሆኜም ሰርቻለሁ።
ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ከፍ ባለ አገር አቀፍ የቁንጅና ውድድር ማለትም በ‘ሚስ ዎርልድ ኢትዮጵያ’ ተወዳደርኩ።
ቀጥሎ በ‘ሚስ ግራንድ ኢንተርናሽናል’ የቁንጅና ውድድር ተወዳድሬ አሸነፍኩ። በፈረንጅ በ2017 በዓለም የቁንጅና መድረክ ኢትዮጵያን በመወከል ለመጀመሪያ ጊዜ በቬትናም ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ተወዳደርኩ።

የፎቶው ባለመብት, Selamawit
‘ሚስ ግራንድ ኢንተርናሽናል’ ቬትናም!
ቬትናም የተካሄደው ‘ሚስ ግራንድ ኢንተርናሽናል’ የቁንጅና ውድድር በዓለማችን ካሉት ሦስት አበይት ውድድሮች አንዱ ሲሆን፣ ከ77 በላይ ወይዛዝርት አገራቸውን ወክለው ተሳተፈውበታል።
በውድድሩ ከከፍተኛዎቹ ሽልማቶች አንዱን አገኘሁ። ከዚያም በላይ ግን ሌሎች ዕድሎችን የከፈተልኝ መድረክ ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የቤተሰቦቼን ድጋፍ ያገኘሁበትና በራሴና በዝንባሌዬ የተደሰትኩበት ውድድር ነበር።
ከዚያ በኋላ ደቡብ ኮርያ ውስጥ በተካሄደ ‘ቢዩቲ ኤንድ ታለንት’ በተሰኘ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ተወዳድሬ የኢትዮጵያን ስም አስጠርቻለሁ።
ቻይና ውስጥ በተካሄደው የቁንጅና እና የልዩ ችሎታ ውድድርም ተሳትፌያለሁ።
“ህልሜን ያጨናገፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት”
ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ትግራይ ውስጥ ከመቀስቀሱ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ተመልሼ የራሴን የባህላዊና የዘመናዊ የእጅ ጥበብ አልባሳት መሸጫ ከፍቼ መስራት ጀመርኩ። ያኔ መቀለ ሞቅ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ ስለነበረ በጣም ጥሩ እየሰራሁ ነበር።
ሆኖም ሳናስበው ትግራይ ውስጥ ብዙ ሕይወትን የቀጠፈው ጦርነት ተቀሰቀሰ። በጣም የከፋና ለመግለጽ የሚከብድ ጦርነት ነው። ጦርነቱ ሲቀሰቀስ መቀለ ነበርኩ። በዚህ ጦርነት የተነሳ ትግራይ ውስጥ ረሃብ፣ ፆታዊ ጥቃትና በአጠቃላይ በቃላት የማይገለፅ መከራ ሰፈነ። በጦርነት ምክንያት ያጣነው ብዙ ነገር ነው፤ ህልማችን ተጨናግፏል።
የትግራይ ሕዝብ ያጋጠመው መፈናቀል፣ ሐዘንና መጎሳቆል በቤተሰቦቼም በራሴም ላይ ደርሷል።
ለአንድም ቀን ከአገሬ ወጥቼ እኖራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፣ ፍላጎቱም አልነበረኝም። ውጭ በሄድኩ ቁጥር ሥራዬን ጨርሼ ወደ አገሬ የምመለሰውም ለዚያ ነው።
ሁሉም ነገር ካቀድኩት ውጪ ነው፤ ሁሉም ነገር ድራማ መስሎ ነው የሚሰማኝ።
ሕይወታችን በሙሉ ተቀየረ። ትግራይ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችለኝ ሁኔታ አልነበረም።
የፌደራል መንግሥት ሠራዊት መቀለ ሲገባ በረራዎች ስለነበሩ ወደ አዲስ ኣበባ ወጣሁ። ተስፋ ግን አልቆረጥኩም። ሁሉም ነገር ሰላም ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ተስፋ እንዳደረግኩት ሰላም አልሰፈነም።
ይልቁንስ ወደ መቀለ ይደረጉ የነበሩት በረራዎች ተቋረጡ።
ያኔ ተስፋ አጣሁ። በአገሬ መኖር ስላልቻልኩ ወደ ስደት አቀናሁ።

የፎቶው ባለመብት, Selamawit
በሕይወቴ የማልረሳት ወር
ከአዲስ አበባ ፈረንሳይ እስክደርስ መለስ ብሎ ለማስታወስ እና ለመናገር የሚከብዱ ጊዜያቶችን አሳልፌያለሁ።
ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ስጓዝም በምድር እና በባሕር ከባድና አስፈሪ የሆነ ጊዜን አሳለፌያለሁ።
ጉዞው ከመክበዱ የተነሳ እንግሊዝ ቻነል ላይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው የቀሩ ወንድሞቼን አይቻለሁ።
ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ለማለፍ ያለው ፈተና ጊዜውን በረሃ ላይ ተኝቶ ማሳለፍ የግድ ነው። በረሃው ላይ ከባድ ቁር አለ፣ የሚበላ ምግብ ሆነ የሚጠጣ ውሃ ማግኘት አይቻልም፤ ስቃይ ነው….. የማያባራ ስቃይ!
ለሁለትና ለሦስት ወራት እዚያ በረሃ ላይ እያደሩ፣ እየተንከራተቱ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ዕድላቸውን የሚሞክሩ፣ ከየት መጡ የማይባሉ በርካታ ሰዎችን አግኝቻለሁ።
ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ የሚያሻግሩት ደላላዎች፣ ከፖሊስ ለመሸሽ ሲሉ ስደተኞቹን የሚያሻግሩት በሌሊት ነው።
ስደተኞቹን በጅምላ ጭነው የእንግሊዝ ቻነልን አቋርጠው የሚያሻግሩ በደላላዎቹ የሚመሩ ጀልባዎች ተዘጋጅተው ነበር።
ከእኔ ጋር የነበሩ የአገሬ ልጆች በመጀመሪያ ዙር ላይ ለመሻገር ሲሞክሩ ጀልባዋ ሰመጠች። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን የሕይወት አድን ሠራተኞች አዳንዋቸው። ጉዞ ያልጀመርን ሰዎች ወሬውን ስንሰማ እጅግ ደነገጥን። ነገር ግን ካቀድነው የሚያስቀር ሌላ አማራጭ አልነበረንም።
እኛም በሌላ ቀን ጉዞ ጀመርን። የተነሳንበት ወቅት ከባድ ቅዝቃዜ ስለነበር ባሕሩ ከባድና አደገኛ ነበር።
በጅምላ ሆነን ወደምታሻግረን ጀልባ ገባን። ሕጋዊ ጉዞ ባለመሆኑ ብዛታችን ይህን ያህል ነበር ለማለት ይከብደኛል። ደላላዎቹ የሚሉንን ነገር ብቻ ነው የምናደርገው። ሕይወታችንን ልናድንባት ወዳሰብነው አገር ወደ እንግሊዝ ጉዞ ጀመርን..!
ጉዟችን በጨለማ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን… የሞት ጥላ ያንዣበበበት ጭምር ሆኖ አገኘነው።
ስንጓዝባት የነበረችው ጀልባ ድንገት ሞተሯ ወደቀና ባሕሩ ላይ ተንሳፈን ቀረን። ከእኛ ጋር የነበረ አንድ አረብ ሞተሩን አወጣለሁ ብሎ ሲሞክር ባሕሩ ውስጥ ገባ።
ባሕሩ በጣም ከመቀዝቀዙ የተነሳ እኔ ነኝ ያለ ዋናተኛ ራሱ የሚችለው አይደለም። እና ሲያቅተው አንድ ወንድማችን ሊረዳው ወደ ባሕሩ ገባ።
እሱ ግን ሳይመለስ ቀረ። ፈለግን፤ ፈለግን፤ ግን ልናገኘው አልቻንም። ድረሱልን ብለን ደወልን። የሕይወት አድን ሠራተኞች በቦታው የደረሱት ከሦስት ሰዓታት በኋላ ነበር። ዓይኔ እያየ ወንድማችን ሰጥሞ ቀረ! ሞትን በዓይኔ አየሁት። እህህህ…!!!
በዚያች ቅፅበት የወሰንኩት ውሳኔ ስህተት እንደሆነ ገባኝ። በሕይወቴ ከባድ ጊዜ ነበር። የቀረነው ከመአት የተረፍነው ድረሱልን ብለን ደውለን እጃችንን ለፖሊስ ሰጠን።
እኛ ከገባን በኋላ ፈረንሳይ ውስጥ ቀርተው የነበሩት ለሦስተኛ ዙር ጉዞ ተነሱ። መጥፎ ዜና ደረሰን። እንግሊዝ ቻናል ውስጥ ሰመጡ። ከሞቱት መካከል ሁለቱ የአገሬ ሴቶች ነበሩ። በተለይ አንዷ በደንብ የማውቃት የመቀለ ልጅ ናት።
የማውቃቸው ብዙ ሰዎች ከጀልባ ወደ ባህር ወድቀው ሰምጠው ቀርተዋል። በሕይወቴ በጣም ተስፋ የቆረጥኩበ፤ ምን አጥፍተን ነው ብዬ የተማረርኩበት፤ በጣም የሚሰቀጥጥ ጊዜ አሳለፍኩ። ወላጆቼ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ አልፌ እዚህ መድረሴን አያውቁም።
በአገሬ ካሳለፍኩት መከራ አይብስም። ከዚህ የከፋ አይቻለሁ ብዬ ጀመርኩት እንጂ ይህንን ጉዞ ማንም ሊሞክረውና ሊያየው የማይገባ አደገኛ መንገድ ነው። እንዲህ ያለ ጉድ ውስጥ እንድንገባ ያደረገን ምክንያት ደግሞ በአገራችን የሚሰቀጥጡ ነገሮች አይተን መምጣታችን ይመስለኛል።
“የተሳሳተና የሚያሳዝን የእንግሊዝ ውሳኔ”
ወደ እንግሊዝ እንደገባሁ ያሳለፍኩትን ሳስብ፣ ያለፈው ተመልሶ አይገኝም እንጂ፣ ትግራይ ውስጥ እንደተዘጋብን ከቤተሰቦቼ ጋር ብሆን እመርጣለሁ።
ቢብስ እንኳን ሁሉንም ነገር ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ እጋፈጠው ነበር። ትግራይ ውስጥ እየተከሰተ ባለው መከራ ምክንያት መምጣት ነበረብኝ ብዬ ሳስብ ደግሞ አሁን ላለኝ ሕይወት ስል ያን ሁሉ መከራ ማየትና እስከ ሞት ጥግ መድረስ ነበረብኝ ወይ? እላለሁ። በጣም ይሰማኛል፤ ያሳለፍኩት ነገር ሁሉ መልሶ ያስደነግጠኛል።
አሁን እንግሊዝ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቄ ነው ያለሁት። መጀመሪያ ሆቴል ውስጥ ነበር ያስገቡን። አሁን ግን የጋራ መኖሪያ ሰጥተውናል። ጉዳዬ እስከሚታይ ድረስ ሥራ መስራት አልችልም፤ ከዚህ ውጪም መንቀሳቀስ አይፈቀድልኝም።
በአሁኑ ወቅት እንግሊዝ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የማባረር ዕቅድ አውጥታ ተግባራዊ ለማድረግ ከጫፍ ደርሳለች።
እዚህ ያለው ስደተኛ ሁሉ የሕይወት ዋስትና ለማግኘትና የተሻለ ኑሮ ለመኖር ሲል ስንት መስዋዕትነት ከፍሎ የመጣ ነው። ይሄ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመመለስ ውሳኔ የተሳሳተና የሚያሳዝን ውሳኔ ነው፤ ምክንያቱም መንገዱ [ስደቱ] እንዴት እንደሆነ አይቼዋለሁ።
ከምወዳቸው ቤተሰቦቼና ከሕዝቤ ተለይቼ ወደ ስደት እስካመራሁበት ወቅት በቁንጅና ውድድር፣ በዲዛይኒንግ፣ በዘፈን ክሊፖችና በተዋናይነት ሰርቻለሁ።
መቀለ ውስጥም ባህላዊ እና ዘመናዊ አልባሳትን ዲዛይን አድርጌ የምሸጥበት የራሴ የንግድ ድርጅት ነበረኝ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ራሴን ስደት ውስጥ ሳገኘው ጥሩ ስሜት አይሰማኝም።
በዚህ ሰዓት ለነገ የምመኘው ነገር ካለ ሰላም ብቻ ነው። ሰላም እመኛለሁ። በዚህ ሰዓት ሰላም የሚባል ነገር አጥቻለሁ። ውስጤ ጥሩ ስሜት የለም። ለሰላም እጓጓለሁ። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር ሊስተካከል ይችላል። ፈጣሪ ሰላም ሰጥቶን ሁሉም ነገር እንዲስተካከል እመኛለሁ።












