የስደተኞች ቅበላ ስምምነት፡ ሩዋንዳ አስጊ ወይስ ደኅንነቷ የተጠበቀ አገር?

ኪጋሊ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዩናይትድ ኪንግደም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሯ የሚገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማሸጋገር ከኪጋሊ መንግሥት ጋር ከስምምነት ደርሳለች።

በስምምነቱ መሠረት ዩኬ ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል በኩል ወደ ዩኬ የሚገቡ አብዛኛዎቹን ጥገኘነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ትሸኛለች።

ሩዋንዳ ደግሞ ከዩኬ የምትቀበላቸውን ስደተኞች የጥገኘነት ጥያቄ ትመረምራለች።

የስደተኛው የጥገኘነት ጥያቄ ምላሸ የሚያገኝ ከሆነ በሩዋንዳ እንዲኖር ይፈቀድለታል። በሩዋንዳ የመኖር ፍላጎት የሌለው ስደተኛ ወደ ትውልድ አገሩ ወይም ሊቀበለው ወደሚችለው ሦስተኛ አገር ሊዘዋወር ይችላል።

ሩዋንዳ ለዚህ ተግባሯ ከአውሮፓዊቷ አገር ዳጎስ ያለ ገንዘብ ትቀበላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩኬ እና ሩዋንዳ ስምምነት ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል። የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ሩዋንዳ የሰብዓዊ መብት የማይከበርባት እና ደኅንነቷ የማያስተማምን ናት ይላሉ።

ቦሪስ ጆንስን በበኩላቸው ሩዋንዳ ደኅንነታቸው አስተማማኝ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች ሲሉ ያሞካሻሉ።

ሩዋንዳን የጎበኙ ሰዎች ደግሞ በአገሪቱ ያዩት እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ።

በጣም ንጹህና ዓይን በሚማርኩ አረንጓዴ አካባቢዎች የተሞላች ነች። በዋና ከተማዋ ኪጋሊ ያለውም የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም አስተማማኝ ነው።

የሩዋንዳ ዜጎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ግብር በአግባቡ የሚከፍሉ ሲሆን ማንኛውም ዓይነት አገልግሎቶችም አስተማማኝ ናቸው።

የፖል ካጋሜ መንግሥት ሩዋንዳ በዓለም በጣም ደኅንነታቸው ከተጠበቁ አገራት መካከል አንዷ ናት ይላል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ሩዋንዳ የወረርሽኙ ዜና ከተሰማበት ቀን አንስቶ ፈጣንና ውጤታማ እርምጃዎችን ለመውሰድ አላንገራገረችም። የእንቅስቃሴ ገደቦችና ሌሎች መመሪያዎች በጥብቅ ይተገበሩ ነበር።

አሁን ላይ ከሩዋንዳ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ክትባት ወስዷል።

ይህ መልካም ጎን እንዳለ ሁሉ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮችም አይጠፉም።

ለምሳሌ አንድ ሰው ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ብሎ አከራካሪ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ ሐሳቡን እንዲገልጽ አይፈቀድም።

እንዲህ ዓይነት ሰው ተገቢ ያልሆነ ባህሪ አሳይቷል ተብሎ ለባለሥልጣናት ሪፖርት ሊደረግ ይችላል።

የሩዋንዳ መንግሥት ስጋት ብሎ የሚያስባቸውን አይታገስም።

"ሩዋንዳ የአፍሪካ ስዊትዘርላንድ ነው የምትመስለው። ነገር ግን አገሪቱ በጣም አፋኝ እና አስፈሪ ነች" ስትል ሩዋንዳን በተመለከተ 'ዱ ኖት ዲስተርብ' የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተመችው ሚኬላ ሮንግ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሁሌም ቢሆን በየወሩ የመጨረሻዋ ቅዳሜ ዕለት ሁሉም ሩዋንዳዊ ዜጋ በየሰፈሩ እየተሰባሰበ አካባቢውን በኅብረት የማጽዳት ባህል አለው።

መንገዶች ይጠረጋሉ፣ ቆሻሻዎች ይሰበሰባሉ እንዲሁም የተጠራቀመ ውሃ ካለም እንዲፈስ ይደረጋል። ይህ ባህል 'ኡሙጋንዳ' ይባላል። በአገሬው ቋንቋ የማኅበረሰብ ሥራ እንደ ማለት ነው።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ሩዋንዳዊ እንደሚለው ምንም እንኳን ሰዎች ኡሙጋንዳ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስገድድ ሕግ ባይኖርም ዜጎች ግን ምናልባት ለመንግሥት ሪፖርት ልደረግ እችላለሁ በሚል ፍራቻ በሥራው ተሳታፊ ይሆናሉ።

ሩዋንዳ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በገባችው ስምምነት መሠረት ስደተኞችን የሚቀበሉት ተቋማት የተደራጁና አብዛኛዎቻችን እንደምናውቃቸው ዓይነት ከፕላስቲክ በተሠሩ ድንኳኖች የተሞሉ አይሆኑም።

አገሪቱ 13 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ሲሆን እስካሁን ድረስ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመተባበር ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ 900 ጥገኝነት ጠያቂ አፍሪካውያንን ከሊቢያ ተቀብላለች።

'ጋሾራ' በመባል የሚታወቀው የጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተናገጃ ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, 'ጋሾራ' በመባል የሚታወቀው የጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተናገጃ ማዕከል

'ጋሾራ' በመባል የሚታወቀው ይህ የጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተናገጃ ማዕከል በዋነኛነት በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን ቋሚ ህንጻዎችና ማዕከላት አሉት። አብዛኛዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ደግሞ ከሊቢያ የመጡ ናቸው።

ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ከተረጉት ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል ከግማሸ በላይ የሚሆኑት ወደ ስዊድን፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ፈረንሳይ እና ቤልጄም ተዘዋውረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚተዳደረው ይህ ማዕከል በርካታ መከራዎችን ላሳለፉ ስደተኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

አዲስ ሕይወት ለመጀመር የሚያስችላቸውን ክህሎትም ይማራሉ። ማዕከሉ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ያለው ሲሆን ጥገኝነት ጠያቂዎች ቋንቋዎችንና ሌሎች ነገሮችንም መማር ይችላሉ።

ባሳለፍነው ዓመት ዴንማርክ አሁን ዩኬ ለማድረግ ያሰበችውን ዓይነት ዕቅድ ይፋ ባደረገችበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ አውጥቶ ነበር።

"መሰል እርምጃ ለአፍሪካውያን ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ ነው'' ብሎ ነበር የአፍሪካ ኅብረት።

አፍሪካ በዓለማችን ውስጥ ካሉት ስደተኞች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑትን የምታስተናግድ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ደግሞ ስደተኞቹ የሚኖሩት በጣም በተጣበቡና ለኑሮ በማይመቹ ድንኳኖች ውስጥ ነው።

በሌላ በኩል ያደጉት አገራት ግን 15 በመቶ የሚሆኑትን ብቻ ነው ተቀብለው የሚያስተናግዱት።

''ጥገኝነት ጠያቂዎችን የመገደብና የመያዝ ፍላጎት ያለው ውሳኔ ነው። በአፍሪካ ያሉ ችግሮችን ለማምለጥ ከአገራቸው የሚሰደዱ ሰዎች ወደ ሩዋንዳ መሄድ በጣም ነው የሚያስፈራቸው'' ትላለች ሚኬላ ሮንግ።

የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ

አሁን ላይ ዩኬ በሩዋንዳ ለማቋቋም ያሰበችው ማዕከል ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ሩዋንዳ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩና ሕይወታቸውን እንዲመሠርቱ ይረዳቸዋል ተብሎለታል።

እስካሁን ድረስ ሩዋንዳ ምን ያህል ስደተኞችን መቀበል እንደምትችል ግልጽ ያልተደረገ ሲሆን የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ግን በመጪዎቹ ዓመታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሩዋንዳ ለማቆየት መታቀዱን ገልጸዋል።

ሚኬላ ሮንግ እንደምትለው ከዋና ከተማዋ ኪጋሊ ውጪ በሚገኙ አካባቢዎች በብዛት በግብርና ላይ ተመሥርተው የሚኖሩ ዜጎች የሚበዙባቸው ናቸው።

ለግብርና የሚሆን ማንኛውም ዓይነት ለም አፈር ያለበት አካባቢ በሙሉ ጥቅም ላይ መዋሉ ደግሞ ስደተኞች እንዴት ነው የሚኖሩት? የሚለውን ጥያቄ ከባድ ያደርገዋል።

ባለፈው ዓመት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ለሰብአዊነት ሲባል የስደተኞች ማዕከላት እንዲቋቋሙ እንደሚፈቅዱ ገልጸው ነበር።

ነገር ግን ጥቂት እንኳን ቢሆኑም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውሳኔው ገንዘብ ለማግኘት እንጂ ለሰብአዊነት ተብሎ የተደረገ አይደለም ብለው ተቃውመው ነበር።

በርካታ የምዕራቡ ዓለም አገራት ሩዋንዳ ከዓመታት በፊት ከተከሰተው የዘር ማጥፋት በኋላ እያሳየችው ባለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለውጥ የተገረሙ ይመስላል። ነገር ግን በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ሥርዓት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት።

ሩዋንዳ ከአፍሪካ አገራት የሚመጡና ወደ አውሮፓ አገራት መሄድ ለሚፈልጉ ስደተኞች መጠለያ ለመስጠት መስማማቷ ምናልባት በመጪው ሰኔ ወር የሚካሄደውን የኮመንዌልዝ አገራት ስብሰባ ለማስተናገድ ካላት ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ የሚገልጹም አልጠፉም።