የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች 615 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ክሪፕቶከረንሲ መዝረፋቸውን አሜሪካ ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የጌም ኩባንያዎችን ኢላማ በማድረግ 615 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ክሪፕቶከረንሲ መዝረፋቸውን አሜሪካ አስታውቃለች።
በሰሜን ኮሪያ የሚደገፉ የሳይበር መረጃ መንታፊዎች ባለፈው ወር ከታዋቂው የኦንላይን ጌም 'አክሲ ኢንፊኒቲ' 615 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ክሪፕቶከረንሲ መዘረፉን ነው አሜሪካ የገለጸችው።
የመንታፊዎቹ ኢላማ የሆነው ይህ የጌም ኩባንያ ጌሙን ለሚጫወቱ ወይም ለሚገበያዩ ሰዎች ክሪፕቶ የሚያገኙበትን ሥርዓት ዘርግቷል።
ታዲያ ይህ የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች ዝርፊያ በክሪፕቶከረንሲው ዓለም ትልቁ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ዘረፋ የተፈጸመው በሰሜን ኮሪያ ዋና የስለላ ቢሮ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ በሚታመነው "ላዛረስ" በተባለ ቡድን ነው ብለዋል።
ኤፍቢአይ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ ከሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ላዛረስ እና ኤፒቲ38 የተባሉ የሳይበር መረጃ መንታፊ ቡድኖች ለስርቆቱ ተጠያቂ መሆናቸውን በምርመራ ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።
ላዛረስ የተባለው ቡድን እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የሶኒ ፒክቸርስ የመረጃ መረብን ጥሶ በመግባት ሚስጥራዊ መረጃዎችን በአደባባይ መዘርገፉ ከተሰማ በኋላ ታዋቂነትን አግኝቷል።
ቡድኑ ይህንን ድርጊት የፈጸመው በወቅቱ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለመግደል የሚደረግ ሙከራ ላይ የሚያጠነጥን ይዘት ያለው 'ዘ ኢንተርቪው' የተባለው ፊልም እንዳይለቀቅ ሲጠይቅ ነበር።
በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ቡድን ፒዮንግያንግ የተዘረፉ ገንዘቦችን የኒውክሌር እና የባላስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሞቿን ለማጠናከር እና ማዕቀቧቹን ለመቋቋም እንደምትጠቀምባቸው አሳውቋል።
ሰሜን ኮሪያ የሳይበር ወንጀሎችን ጨምሮ በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ የምትሳተፍበት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ እና ትርፉንም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎቿ እና ባሊስቲክ ሚሳኤል መርሃ ግብሯቿን ለማጠናከር እያዋለች መሆኑን የአሜሪካ ግምጃ ቤት መግለጹን ቃል አቀባዩን በመጠቀስ ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 የወጣው የአሜሪካ ወታደራዊ ሰነድ የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ጥቃት ተግባር ቢያንስ በ1990ዎቹ አጋማሽ እንደጀመረ እንዲሁም ቢሮ 121 ተብሎ የሚጠራ እና ወደ 6 ሺህ የሚጠጋ ጠንካራ የሳይበር አባላት እንዳለው አሳይቷል።
ይህ ቡድን ቤላሩስ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ማሌዥያ እና ሩሲያን ጨምሮ በበርከታ አገራት እንደሚሠራ አመላክቷል።
ብሎክቼይን የሚተነትን ኩባንያ ባወጣው መረጃ መሠረት የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ቢያንስ 400 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ዲጂታል ገንዘብ እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ባደረሷቸው ቢያንስ ሰባት ጥቃቶች ዘርፈዋል።
ይህም በእሲያ አገራት ውጤታማው እና እጅግ ስኬታማ ከሆኑት የሳይበር ምንተፋዎች አንዱ ነው ብሏል።












