ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ትኩረት ለጥቁሮች አልሰጠም ሲሉ ወቀሱ

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድኃኖም (ዶ/ር) የዓለም ማኅበረሰብ እርዳታን ለሚሹ ጥቁርና ነጮች የሚሰጠው ትኩረት ሚዛናዊ አይደለም ሲሉ ወቀሱ፡፡

ዳይሬክተሩ ለዚህ ወቀሳቸው እንደማሳያ ያነሱት በቅርቡ ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ሰብአዊ እርዳታ ሩቡን እንኳ ለተቀረው ዓለም አለመሰጠቱን ነው፡፡

ተዘንግተዋል ካሏቸው አገሮች ውስጥ እንደ አብነትም ኢትዮጵያን፣ የመንን፣ አፍጋኒስታንና ሶሪያን አንስተዋል፡፡

‹‹ዩክሬንን መርዳት እጅግ ጠቃሚም ተገቢም ነው፡፡ ምክንያቱም ተጽእኖው ለመላው ዓለም የሚተርፍ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ነገር ግን በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል፣ የመን፣ አፍጋኒስታንና ሶሪያ፣ ዩክሬን ከዓለም ማኅበረሰብ ያገኘችውን ትኩረት አላገኙም፡፡›› ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

‹‹ዓለም ለጥቁርና ነጭ ሕይወት የሚሰጠው ትኩረት ተመጣጣኝ ነው ብዬ ለማለት እቸገራለሁ፡፡›› ሲሉም ነው በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያወሱት፡፡

‹‹በዚህ ጉዳይ ግልጽና ቀጥተኛ መሆን አለብኝ፤ ዓለም የሰው ዘርን ሁሉ እኩል እያስተናገደ አይደለም፡፡ አንዳንዶች ከሌሎች የተሻለ እኩል ናቸው፤ ይህን ሀቅ ስናገር ያመኛል፤ ምክንያቱም የማየው ነው፤ ለመቀበል ይቸግራል ግን እውነታው ይኸው ነው፡፡›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

ትውልዳቸው ከትግራይ የሆኑት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የተባበሩት መንግሥታት በቀን 100 ተሸከርካሪዎች ሕይወት አድን ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ መግባት እንዳለበት መወሰኑን በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካውን ለሦስት ዐሥርታት በበላይነት ሲመራ በነበረው ህወሓትና በመንግሥት መካከል በተነሳ ጦርነት በርካቶች ሲገደሉ በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፡፡

ሌሎች ሚሊዮኖች ደግሞ አጣዳፊ የሰብአዊ እርዳታን ይሻሉ፡፡

መንግሥት ይህን እርዳታ ወደታቀደለት ስፍራ እንዳይደርስ እንቅፋት አየፈጠረ ነው በሚል ይተቻል፡፡

መንግሥት በበኩሉ ይህን ክስ በተደጋጋሚ ያስተባብላል፡፡

በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ጅምላ ግድያና ጾታ ጥቃት ስለመሳተፋቸው የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አጋልጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት በዓለም አስከፊው የሰብአዊ ቀውስ ያለው በየመን እንደሆነ ይናገራል፡፡

በአፍጋኒስታን ደግሞ 24 ሚሊዮን ሕዝብ በሕይወት ለመቆየት አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታን እንደሚሻ የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርጓል፡፡

ሶሪያ ለ11 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝቧን በእርስ በእርስ ጦርነቱ አጥታለች፡፡ ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችው ከ50 ቀናት በፊት ነበር፡፡ቡቻ በምትባለው፣ ከኪየቭ ወጣ ብላ በምትገኝ የዩክሬን አነስተኛ ከተማ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ እየተጣራ ነው የሚገኘው፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ሩሲያ የዘር ጭፈጨፋ (ጄኖሳይድ) መፈጸሟን በግላቸው እንደሚያምኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡