የዓለም ጤና ድርጅት ለትግራይ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ፍቃድ አለማግኘቱን ገለጸ

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, FABRICE COFFRINI

በጦርነት ክፉኛ በተጎዳችው ትግራይ ክልል ካለፈው ዓመት ሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ የህክምና ቁሳሶቁሶችን ለማድረስ ፍቃድ አለማግኘቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ በትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶች ለማቅረብ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሊፈቀድለት እንዳልቻለ የድርጀቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።

ሆኖም በጦርነቱ ለተጎዱት አማራና አፋር ክልሎች የህክምና ቁሳቁሶች ማድረስ መቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ለአማራ ክልል 70 ሜትሪክ ቶን እንዲሁም ለአፋር 14 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉን የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ ህይወትን ለማዳን ዋነኛው ነገር ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ነው ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በትግራይ ክልል የሚያቀርባቸው የህክምና ቁሳቁሶቹ በክልሉ እየገጠሙ ያሉ ሰብዓዊ እና የጤና ፍላጎቶችን ለማሟላት ይረዳ ነበር ብለዋል።

በእርስ በርስ ጦርነት ባለበትና አስቸጋሪ በሚባሉ የግጭት ወቅቶች እንኳን በሶሪያ፣ በደቡብ፣ ሱዳንና እና የመን የዓለም ጤና ድርጅትና አጋሮቻቸው እርዳታ መለገስን እንደቻሉም ገልጸዋል።

ነገር ግን "በትግራይ የተጣለው እገዳ ሰብዓዊ አቅርቦቶችን በመከልከል የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው" ሲሉ ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዶክተር ቴድሮስ ለሁሉም መሪዎች እና በጦርነቱ ወስጥ ዋና ዋና ባለ ድርሻ አካላት ላሏቸው "ለሰላም የሚተጉ በታሪክ የሚታወሱ ጀግኖች መሆናቸውን እንዲያስታውሱ አሳስባለሁ" ብለዋል።

"ጤና ለሰላም፣ ሰላም ለጤናም" አስፈላጊ ነው በሚል የተናገሩት ዶክተር ቴድሮስ ህይወትን ለማዳን በሁሉም የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ የሰብዓዊ እና የጤና አቅርቦት ማድረሻዎች ክፍት መሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበረብ ቡድኖች በተሻለ መንገድ ህይወትን ለማዳን የሚያደርጉትን ጥረት ያቀላጥፈዋል በማለት አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንት እየሞቱ መሆናቸውን ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ እንዲሁም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ መድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች ወደ ሆስፒታሎች ባለመድረሳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ መንግሥት ምንም አይነት እገዳ እንዳልጣለና በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ችግር ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።

በክልሉ መዲና መቀለ በሚገኘው ትልቁ የጤና ተቋም የሚገኙ ዶክተሮች እንደተናገሩት በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያስፈልጉ በደም ስር የሚሰጡ (intravenous fluids) እና የሰመመን መስጫ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ቀዶ ህክምና ማድረግ አለመቻላቸውን ነው።

የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች ባወጡት መግለጫ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና ያልተሟላ የኦክስጂን አቅርቦት ለታካሚዎች ሞት ምክንያት ነው ብለዋል።

ጓንቶች፣ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣ የህመም ማስታገሻዎች፣ በምጥ ላይ ላሉ ሴቶች ወሳኝ መድኃኒቶች እንዲሁም ለተለያዩ የአዕምሮ ህመም የሚውሉ መድኃኒቶችና መሰረታዊ የላብራቶሪ ምርመራዎች በሌሉበት ሁኔታ በሆስፒታሉ ውስጥ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ጠቅሰዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ የመገልገያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንደሚጠቀሙና ያለውም ብቸኛ አማራጭ እሱ በመሆኑ አሁንም አስቸኳይ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማንም በቻሉት መጠን እየተንከባከቡ እንደሆነ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን በማደናቀፍ እርስ በእርሳቸው ሲወቃቀሱ ይሰማል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በቅርቡ በትግራይ አንዳንድ የጤና አገልግሎቶች በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ አቁመዋል ብሏል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ከታኅሣሥ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ አልገቡም።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን ከአምስት ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ለመድረስ ከታሰበ በየሳምንቱ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ክልሉ ሊገቡ ይገባል ቢልም፣ እንደ ኦቻ ሪፖርት ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ከሚያስፈልገው አቅርቦት ውስጥ 12 በመቶ ብቻ ነው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።