በትግራይ በተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 56 ሰዎች መገደላቸውን የእርዳታ ሠራተኞች ገለጹ

በትግራይ ክልል ደደቢት ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ታዳጊ በመታከም ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 56 ሰዎች ሲገደሉ በርካታ መቁሰላቸውን የእርዳታ ሠራተኞች ገለጹ።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በክልሉ ሰሜናዊ ምዕራብ በምትገኘውና የኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ባለች ደደቢት ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት አርብ ምሽት መሆኑንም የእርዳታ ሠራተኞቹ ተናግረዋል።

ከጥቃቱ በኋላም የተጎዱ ሰዎች ህክምና ሲደረግላቸው የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጋርተዋል።

ጥቃቱ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቃባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንዲሁም የመንግሥት ቃለ አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ ጥቃቱን አስመልክቶ ምላሽ እንዳልሰጡት ሮይተርስ ዘግቧል።

በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጡም በዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና አጋሮቹ ከህወሓት ኃይሎች ጋር በመሬት ላይ የሚያደርጉት ጦርነት በጊዜያዊነት ቢቆምም በአማጽያን ቦታዎች ላይ የሚደረገው የአየር ጥቃት ቀጥሏል።

ቅዳሜ ዕለት የእርዳታ ሠራተኞች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የሟቾች ቁጥር በአካባቢው ባለሥልጣናት መረጋገጡን ነው።

ስማቸው ያልተጠቀሱት እኒህ የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ህፃናትን ጨምሮ በሆስፒታል ውስጥ ያነሷቸውን የቆሰሉ ሰዎችን ፎቶግራፍ ለሮይተርስ መላካቸው ተገልጿል።

ተጎጂዎች ለህክምና የተወሰዱበትን ሽሬ ስሁል አጠቃላይ ሆስፒታል ከጎበኙት የረድኤት ሠራተኞች መካከል አንደኛው እንደገለጹት መጠለያ ካምፑ በርካታ ህፃናት እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ያሉበት ነው።

ትምህርት ቤቱ እንዴት እና ለምን ጥቃት እንደደረሰበት ግልፅ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል በአየር ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርግ ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው መግለጫ ከታኅሣሥ 10 አስከ 15 ድረስ በትግራይ ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን አስፍሯል።

ኦቻ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከጥቅምት ወር ወዲህ ከተከሰቱት በጣም አስከፊና በርካታ ሞቶች ሪፖርት የተደረጉበት በተከተታይ ጥቃት ተፈጽሟል ብሏል።

በርካታዎቹ ጥቃቶች ሪፖርት የተደረጉት በደቡብ ትግራይ ከተሞች በአላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መኮኒ እና ሚላዛት መሆኑን ጠቅሷል።

ነገር ግን በአካባቢው ባለው ውስን ተደራሽነት እና የፀጥታ ችግር ምክንያት የሰብአዊ አጋሮች የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን ማረጋገጥ እንዳልቻሉም ጠቅሷል።

ከሰሞኑም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ሦስት ኤርትራውያን በማይ አይኒ የስደተኞች ጣቢያ በአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።

ከሦስቱ ኤርትራዊያን ስደተኞች መካከል ሁለቱ ሕፃናት መሆናቸውን ኮሚሽኑ በኦፊሴላዊ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ባለፈው አርብ መንግሥት የቀድሞ የህወሓት አመራሮችን ጨምሮ ታዋቂ የፖለቲካ አመራሮችን ከእስር መልቀቁን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እርምጃው ብሔራዊ እርቅን ለማምጣት እና "አንድነትን" ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛምቶ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ ሦስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።