በትግራይ ሆስፒታል ህሙማን እየሞቱ ነው - ዶክተሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጦርነት ክፉኛ በተመታችው ትግራይ ክልል የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን እየሞቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ መድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች ወደ ሆስፒታሎች ባለመድረሳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ለሮይተርስ እንደተናገሩት መንግሥት ምንም አይነት እገዳ እንዳልጣለና በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ችግር ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።
በክልሉ መዲና መቀለ በሚገኘው ትልቁ የጤና ተቋም የሚገኙ ዶክተሮች እንደተናገሩት በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያስፈልጉ በደም ስር የሚሰጡ (intravenous fluids) እና የሰመመን መስጫ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ቀዶ ህክምና ማድረግ አለመቻላቸውን ነው።
የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች ባወጡት መግለጫ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና ያልተሟላ የኦክስጂን አቅርቦት ለታካሚዎች ሞት ምክንያት ነው ብለዋል።
ጓንቶች፣ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣ የህመም ማስታገሻዎች፣ በምጥ ላይ ላሉ ሴቶች ወሳኝ መድኃኒቶች እንዲሁም ለተለያዩ የአዕምሮ ህመም የሚውሉ መድኃኒቶችና መሰረታዊ የላብራቶሪ ምርመራዎች በሌሉበት ሁኔታ በሆስፒታሉ ውስጥ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ጠቅሰዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ የመገልገያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንደሚጠቀሙና ያለውም ብቸኛ አማራጭ እሱ በመሆኑ አሁንም አስቸኳይ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማንም በቻሉት መጠን እየተንከባከቡ እንደሆነ አስፍረዋል።
በተጨማሪም የነርቭ ቀዶ ህክምና (neurosurgery) ቡድኑ ሲቲ ስካንም ሆነ ኤምአርአይ መሳሪያዎች እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን በማደናቀፍ እርስ በእርሳቸው ሲወቃቀሱ ይሰማል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በቅርቡ በትግራይ አንዳንድ የጤና አገልግሎቶች በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ አቁመዋል ብሏል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።












