ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዚዳንት ባይደን በምን ጉዳዮች ላይ ተወያዩ?

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትና ዋይት ሐውስ ባወጡት መግለጫ አመለከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት አድርገዋል።
ጨምረውም ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ መከባበር ላይ መሰረት በማደረግ ገንቢ ግንኙነት በማድረግ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ በሰሜናዊ ክፍሏ ስላካሄደችው ሕግ የማስከበር ዘመቻ" ያለበት ሁኔታ መግለጻቸውን ጠቅሷል።
እንዲሁም ስለ ሰብአዊ እርዳታ፣ ሰብአዊ መብቶችን እና በቅርቡ ነጻ በወጡ አካባቢዎች መልሶ ግንባታን በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት አንስተው ማብራራታቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለከትተው በሁለቱ መሪዎች መካከል በአገሪቱ እየተካሄደ ስላላው ጦርነት እና ሰለምና እርቅ ለማውረድ ስላሉ ዕድሎች የስልክ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በቅርቡ ስለተፈቱት የፖለቲካ አስረኞች በተመለከተ ያላቸውን በጎ አስተያየት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለጹ መሆኑን መግለጫው ጠቅሶ፣ መሪዎቹ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ማድረግን በተመለከተ ተነጋግረዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባላፈው ሳምንት ማብቂያ ለብሔራዊ መግባባትና አገራዊ አንድነት ለማጠናከር በሚል በእስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የመሰረተውን ክስ አቋርጦ እንዲፈቱ ማድረጉ ይታወሳል።
በተጨማሪም በመላው ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በሚሻሻልበት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎችና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይም መነጋገራቸው ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በቅርቡ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን ጨምሮ የቀጠለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣ አሜሪካ ከአፍሪካ ሕብረትና አካባቢያዊ አጋሮች ጋር በመሆን ግጭቱ በሰላም እንዲያበቃ ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው ጠቅሷል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተፈናቃዮች ካምፕ ላይ ተፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በአየር ጥቃቶቹ ምክንያትም የእርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሥራቸውን መቋረጣቸውን ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካ ግጭቱ በድርድር እንዲቆጭ ጥሪ ስታቀርብ ከመቆየቷ በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ሰይመው ለማሸማገል ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት አሜሪካ በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑት ወገኖች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቪዛ ዕገዳ ቀዳሚው ነበር።
በተከታይነትም ፕሬዝዳንቱ ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የተለያዩ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ባለፈው መስከረም ወር የፈረሙ ሲሆን ይህም የኢትየጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት፣ የአማራ ክልል አስተዳደርና የህወሓት አባላትን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።
በተከታይነት ኢትዮጵያን የአፍሪካ አገራት ወደ አሜሪካ ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ምርታቸውን እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአፍሪካ የእድገትና የዕድል ድንጋጌ- አጎዋ ተጠቃሚነት እንድትታገድ የሚያደርግ ውሳኔን ፕሬዝዳንት ባይደን ከአንድ ሳምንት በፊት ፈርመው ተግባራዊ ሆኗል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት እየተካሄደ ባለው ጦርነት አሜሪካ ህወሓትን በመደገፍ ከመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር በት አንስቶ በተለያዩ ሁኔታዎች ጫና እያደረገች ነው በማለት ሲከስ ቆይቷል።
ይህ በፕሬዝዳንት ባይደንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከሻከረ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ውይይት ነው።
ከፕሬዝዳንቱ ባሻገር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከወራት በፊት እየተካሄደ ስላለው ጦርነት የተወያዩ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረው አያውቁም ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ጉዳይ በተመለከተ ከጎረቤት አገር ኬንያ ፕሬዝዳንት ጋር በተደጋጋሚ መወያየታቸው የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም በዚህ ሁኔታ ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይህ የፕሬዝዳንት ባይደንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስልክ ውይይት የተካሄደው የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ፣ ከሦስት ቀናት በፊት ደግሞ በእስር ላይ የነበሩ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ከአስር መለቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
















