የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገለጹ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ ነው ያሉት ግጭት እንዲሁም ክፍፍል እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

ረቡዕ ምሽት ከጽህፈት ቤታቸው በወጣው መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በአገሪቱ በርካታ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጸሙ እከፉ የመጡ ጥቃቶች እንዲሁም እየጠነከረ ያለ ክልላዊና የብሔር መከፋፈል በእጅጉ እንዳሳሰባቸው አመልክተዋል።

ጨምረውም በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ "መጠነ ሰፊ ጾታዊ ጥቃቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች" ተቀባይነት የሌላቸውና በአስቸኳይ ሊቆሙ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል።

አሜሪካ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ ያደረኩት ጥረት ውጤት ስላላስገኘ በሚል ከቀናት በፊት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲለው እንደነበረው ሁሉ አሁንም ፕሬዝዳንቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ እንዲሁም የኤርትራና የአማራ ክልል ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ አጋጥሞ የነበረው አይነት የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ያለውን ስጋት የጠቀሰው የፕሬዝዳንት ባይደን መግለጫ፤ ሁሉም ወገኖች በተለይም የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች እርዳታ ያለገደብ እንዲቀርብ በአስቸኳይ እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል።

የአገሪቱን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅና ሕዝቡን ለመጠበቅ የኢትዮጵያ መሪዎችና ተቋማት ለእርቅ፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ብዝሃነትን ለመረጋገጥ ጥረት እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥትና የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያለቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉን አቀፍ ውይይት ፈቃደኛ እንዲሁኑ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን አክለውም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባትና በአካባቢው ያሉትን ተያያዥ ግጭቶች በሰለማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማደረግ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካው ልዩ ጄፍሪ ፌልትማን አዲስ ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

በዚህም ልዩ መልዕክተኛው ወደ አካባቢው በሚቀጥለው እንደሚያቀኑና ስላለው ሁኔታ መረጃ እንደሚያቀርቡላቸው ፕሬዝዳንት ባይደን ገልጸዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ የወጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የጣለውን እገዳ ካሳወቀ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በውሳኔው ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን እርምጃውንም በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለመፍጠር ያለመ ነው ሲል ገልጾታል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ እርምጃው "በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫናን ማድረግ መቀጠሉን" በመጥቀስ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን የምትቀጥል ከሆነ መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት መለስ ብሎ ለመመርመር እንደሚገደድ አማስጠንቀቁ አይዘነጋም።

የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ መፍትሔ እንዲገኝ በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በኩል ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ልዩ መልዕከተኞች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

አሜሪካ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳይን በቅርበት እንዲከታተሉላት አንጋፋውን ዲፕሎማት ጄፍሪ ፌልትማንን በልዩ መልዕክተኝነት ሰይማ ከሳምንታት በፊት በአካባቢው ጉብኝት አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንትም የአገሪቱ ሴኔት በትግራይ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰድ የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አሳልፎ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በውስጥ ጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለመሳደር የሚሞክሩ መንግሥታትን ጫና እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተጀመረው ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።