አብዛኞቹ አፍሪካውያን ወጣቶች ከአህጉሪቱ መሰደድ እንደሚፈልጉ ጥናት አመለከተ

አፍሪካውያን ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አብዛኞቹ አፍሪካውያን ወጣቶች በአገራቸውና በአህጉሪቱ ላይ ብሩህ ተስፋ እንደማይታያቸው አንድ ጥናት አመለከተ።

በጥናቱ ውስጥ ከተካቱት አፍሪካውያን ወጣቶች መካከል ሁለት ሦስተኛው ስለ እራሳቸው የወደፊት ተስፋ አውንታዊ ምልከታ ቢኖራቸውም፣ አገራቸውና አህጉራቸው አፍሪካ እየሄዱበት ባለው አቅጣጫ ላይ ተስፋ ሰጪ ነገር እንደማያዩ ተናግረዋል።

‘አፍሪካን ዩዝ ሰርቬይ’ በተባለው በዚህ ጥናት ውስጥ ከ15 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ ከ4,000 በላይ ወጣቶች ከአጥኚዎቹ ጋር የፊት ለፊት ቃለ ምልልስ አድርገው ነው፤ ስለአገራቸውና አህጉራቸው ያለቸውን አመለካከት ለአጥኚዎች የገለጹት።

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ሌላ አገር የመሄድ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ወደ 80 በመቶ የሚጠጉት ደግሞ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ዕቅድ አላቸው።

ወጣቶቹ በዚሁ ጥናት ላይ እንዳሉት አፍሪካውያን ወጣቶች በአህጉሪቱና በአገራቸው ውስጥ ተስፋ እንዲኖራቸው እና ዕድገት እንዲመጣ መንግሥታት ጥሩ የሚከፈልባቸው ሥራዎችን ለመፍጠር ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ ሙስናን እንዲቀንሱ እና የአየር ጠባይ ለውጥን እንዲዋጉ ሐሳብ አቅርበዋል።

በጥናቱ ከተካተቱት መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ቻይና የአሜሪካንን ቦታ በመረከብ ጠንካራዋ ኃያል አገር መሆኗን አመልክተዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ ድህነትና ግጭቶች በሚያምሷት አፍሪካ በርካታ ወጣቶች የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ አደገኛ በሆኑ መንገዶች ወደ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ይጓዛሉ።

በዚህም ሳቢያ ጥቂት የማይባሉት ወጣቶች በጉዞ ላይ ሳሉ በረሃብ፣ በበሽታ እና በባሕር ላይ በሚያጋጥሙ አደጋዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ቆይተዋል።