ለዩክሬን ሲዋጋ የነበረው የቀድሞ የብሪታኒያ ወታደር ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, DEAN GATLEY/FACEBOOK
የቀድሞው የእንግሊዝ ጦር አባል የነበረው ግለሰብ ዩክሬን ውስጥ መገደሉን ቤተሰቦቹ አሳወቁ።
ጆርዳን ጋትሊ ከብሪታኒያ ጦር በመውጣት ባለፈው መጋቢት ነበር በሩሲያ ከተወረረችው ዩክሬን ጎን ለመሰለፍ ወደ ጦር አውድማ ያቀናው።
የወታደሩ አባት ልጄ "ጀግና" ነው ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ፅፈዋል።
በምሥስራቃዊቷ የሰቨሮዶኔስክ ከተማ ውስጥ በነበረው ጦርነት ነው የተገደለው።
ከተማዋ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከበድ ያለ ጦርነት እያስተናገደች ትገኛለች።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ዩክሬን ውስጥ የተገለደውን ወታደር ቤተሰቦች እንደግፋለን" ብሏል።
የወታደሩ አባት በፌስቡክ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት ልጃቸው የዩክሬን ወታደሮችን እያሠለጠነ እንደነበረ ገልጠዋል።
አክለው ውጊያ ላይ እያለ ክፉኛ ቆስሎ ሕይወቱ ማለፉን አርብ ዕለት እንደሰሙም ጽፈዋል።
ወታደሩ ልጃቸው ወደ ዩክሬን ያቀናው ከራሱ ጋር "ብዙ ከመከረ" በኋላ እንደነበርም አባት አስታውሰዋል።
የቤተሰቡ መግለጫ እንደሚያትተው ወታደሩ በዩክሬን ተወዳጅነት አትርፎ ነበር።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አማካሪ የሆኑት ሚካይሎ ፖዶሊያክ ወታደሮ "እውነተኛ ጀግና" ነበር ሲሉ ትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል።
አማካሪው አክለው ዩክሬንና የተቀረውን ነፃ ዓለም ለመጠበቅ ላበረከተው እናመሰግነዋለን ብለዋል።
ቢቢሲ እንደተረዳው ወታደሩ የብሪታኒያ ጦር አባል ሳለ በኤደንብራው ሦስተኛ ክፍለ-ጦር አገልግሏል።
ጆርዳን ጋትሊ ዩክሬን ውስጥ የተገደለ ሁለተኛው ብሪታኒያዊ ወታደር ነው።
ባለፈው ሚያዚያ እንዲሁ ስኮት ሲብሊ የተባለ ሌላ ብሪታኒያዊ ተገድሎ ነበር።
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ዩክሬን ለመዋጋት የሚሄዱ ዜጎቹ ወንጀል እንደፈፀሙ ተቆጥሮ ሊቀጡ ይችላሉ ሲል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
በሰቨሮዴኔስክ ከተማ ከሰሞኑ በነበረው ከባድ የጦር መሣሪያን ባካተተ ፍልሚያ የሩሲያና ዩክሬን ጦር ጉዳት እንደደረሰባቸው እየተዘገበ ነው።
የክልሉ አስተዳዳሪ ሴርሂይ ሃይዳይ ለዩክሬን ጦር እንደተናገሩት ሩሲያ በከተማዋ የሚገኘውን የኬሚካል ፋብሪካ በከባድ መሣሪያ አጥቅታለች።
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት 800 ያክል ዩክሬናዊያን ሰላማዊ ነዋሪዎች በዚህ የኬሚካል ፋብሪካ ውስጥ ተደብቀው ይገኛሉ።
ሩሲያ ፊቷን ከኪዬቭ ወደ ሉሃንስክና ዶኔስክ ካዞረች ወዲህ በሰቨሮዴኔስክ ከተማ ቢያንስ ለአንድ ወር ያክል ጦርነት ተካሂዷል።
ሩሲያ ከተማዋን ከተቆጣጠረች የበላይነቷን እያጠናከረች ትመጣለች።












