የአፍሪካ ህብረት ዩክሬን የእህል ወጪ ንግድ ሂደትን እንድታቀል ጠየቀ

የኦዴሳ ወደብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ዩክሬን የእህልን ወጪ ንግድ ለማቃለል ከኦዴሳ ወደብ ፈንጂዎችን እንድታስወግድ አሳሰቡ።

ሊቀ መንበሩ ይህንን ያሉት ከፈረንሳይ ሚዲያዎች አርኤፍአይና ፍራንስ 24 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ሩሲያ በኦዴሳ ላይ ጥቃት እንደማትፈፅም ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማረጋገጫ እንደደረሳቸውም ተናግረዋል።

ሩሲያ የዩክሬን የስንዴ ወጪ ንግድ እያደናቀፈች ነው የተባለ ሲሆን ሩሲያ ግን አስተባብላለች። ሩሲያ እንደምትለው ዩክሬን መተላለፊያ የሆነው ኦዴሳ እና ሌሎች ወደቦች ዙሪያ ያለውን አካባቢ ፈንጆች ማንሳት አለባት ብለዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዩክሬን በወደቦቿ ዙሪያ ያሉትን ፈንጆች ማንሳት አትችልም ብለዋል። ሩሲያ “ደቡባዊ ዩክሬንን ለማጥቃት የእህል መተላለፊያ ኮሪደሮችን ትጠቀማለች” የሚል ነው ምክንያታቸው።

የእህል ወጪ ንግድ ወደ አፍሪካ እንደገና ካልተጀመረ በዩክሬን እና በሩሲያ የእህል ምርቶች እና ማዳበሪያዎች ላይ ጥገኛ ለሆነችው አህጉር አሳሳቢ የሆነ የረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከታትና ከፍተኛ ጉዳትም እንደሚያስከትል አስረድተዋል፥።

ሩሲያ እና ዩክሬን 29 በመቶ የሆነውን የአለም አቀፍ የስንዴ ወጪ ንግድን ይሸፍናሉ።

ሊቀ መንበሩ በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዋነኝነትም ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት የአውሮፓ ህብረት የጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ ፕሬዚዳንት ማክሮን ግፊት እንዲያደርጉ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።