ሩሲያና ዩክሬን ሰቨዶነስክ ከተማን ለመያዝ ኃያል ፍልሚያ እያደረጉ ነው

ሰቨዶነስክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት ከዋና ከተማዋ ኪየቭ ወደ ምሥራቅ ዩክሬን ዶንባስ ግዛት ካዞረች ወዲህ ኃያል የተባለ ዉጊያ እየተደረገ ነው።

ውጊያው በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮችና የራሺያ ጦር በጋራ ሰቨዶነስክ ከተማን ለመቆጣጠር ከዩክሬን ኃይል ጋር የሚያደርጉት ነው።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ይህ ወሳኝ ጦርነት የምሥራቅ ዩክሬን ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ጦርነት ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ወታደሮቼ በጠላት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ቢሉም በቁጥጥራቸው ሥር ትገኝ ከነበረችው ከተማ ወደ ዳርቻ እያፈገፈጉ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የሉሃንስክ አውራጃ ገዥ የሆኑት ሰርሂ ሓይዳይ የዩክሬን ልዩ ኃይል ማፈግፈግ የጀመረው ሩሲያ የአየር ጥቃት በመክፈቷ ነው ብለዋል።

ሉሃንስክ አውራጃ የዶንስክን፣ የዶንባስን እናሌሎች ግዛቶችን በውስጡ የያዘ ነው።

በከተማዋ ወደ 15ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎችመፈናፈኛ አጥተው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የአውራጃው ገዥ አስታውቀዋል።

ሩሲያ ባለፈው ማክሰኞ የሉሃንስክ አውራጃን 97 እጅ በእጄ አስገብቻለሁ ስትል በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል አሳውቃ ነበር። ሆኖም የዩክሬን ባለሥልጣናት ይህን አይቀበሉም።

የሩሲያ ወታደሮች ከዋና ከተማ ኪየቭና አካባቢው ወደ ምሥራቅ ዩክሬን ፊታቸውን አዙረው ዘመቻ የከፈቱት ባለፈው መጋቢት መጨረሻ ነበር።

አብዛኛው የዶንባስ ግዛት ወትሮም በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣይ ኃይሎች የተያዘ ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ይህ ጦርነት 1.6 ቢሊዮን የዓለምሕዝብ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም በኃይል አቅርቦት ዋጋ መናር፣ በምግብ እጥረት፣ በገንዘብ ዝውውር መታወክን የሚገለጽ ነው።

በተለይ የአፍሪቃ አገራት በማዳበሪያና በስንዴ ዕጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተመላክቷል።

አሁንም ድረስ በሚሊዮን ቶን የሚመዘን ስንዴ በዩክሬን ወደቦች ላይ የሚገኝ ሲሆን በጦርነቱ የተነሳ ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይንቀሳቀስ ሆኗል።

ለዚህ መፍትሄ ለመሻት ቱርክ ከትናንት ጀምሮ ሩሲያንና ዩክሬንን በማሸማገል ላይ ናት።

ተንታኞች የሩሲያ ምጣኔ ሃብት በተደራራቢ ማዕቀቦች የተነሳ በ15 እጅ ሊያሽቆለቁል ይችላል ብለዋል።

በተለይ ሁሉም የአውሮጳ አገራት ራሳቸውን በኃይል አቅርቦት ከሩሲያ ጥገኝነት ነጻ ካወጡ የራሺያ ምጣኔ ሃብት ከዚህም በላይ ሊጎዳ እንደሚችል ይነገራል።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ካስከተለው መጠነ ሰፊና ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ባሻገር ለ4ሺህ ንጹሐንሞት ምክንያት ሆኗል።

14 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።