አንጌላ መርክል በፑቲንና በሩሲያ ጉዳይ መታማታቸውን አስተባበሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቀድሞዋ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርክል ለፑቲን ስስ ልብ እንዳላቸው የሚነገረውን ሐሜት አስተባበሉ።
አንጌላ ሥልጣን ከለቀቁ ወዲህ በሰጡት የመጀመሪያ በተባለ ቃለ ምልልስ በፑቲን እና በሩሲያ ጉዳይ ይቅርታ የምጠይቅበት አንዳችም ምክንያት የለም ብለዋል።
አንጌላ መርክል ዩክሬን ቀደም ባሉት ዓመታት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንዳትቀላቀል ተቃውሞ በማሰማታቸው አሁንም ድረስ ይተቻሉ።
ከዚህም ባሻገር መርክል የጀርመንና የሩሲያ ግንኙነት ከፖለቲካ ይልቅ ‘ንግድ መር’ እንዲሆን በማድረጋቸው የሚተቿቸው ብዙ ናቸው።
ይህን የንግድ መር ፖሊሲ መከተላቸው አሁን ጀርመን ላለችበት የኃይል (ኢነርጂ) ምስቅልቅል፣ ኢንዱስትሪዎቿ በሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ላይ ጥገኛ ስለመሆኗ እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል።
“ኖርድ ስትሪም ሁለት” የተሰኘውና ከሩሲያ በቀጥታ ወደ ጀርመን የተዘረጋው የጋዝ መስመር የተሳለጠው አንጌላ በሥልጣን ላይ ሳሉ ነበር።
ይህ መስመር እንዲቆም ያደረጉት ደግሞ አንጌላን የተኩት የአሁኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ናቸው።
ይህም የሆነው ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር በዝግጅት ላይ ሳለች በዋዜማው ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት ሩሲያ ላይ የማዕቀብ ናዳ እየጣለ ባለበት በአሁን ወቅት ጀርመን ምጣኔ ሀብቷ በከፍተኛ ሁኔታ ከሩሲያ በሚመጣ የኃይል አቅርቦት ጋር በመንጠልጠሉ ዕቀባውን በሙሉ ልብ ለመቀላቀል ሳትችል ቀርታለች።
አንጌላ ለፑቲንና ለአገራቸው በነበራቸውን ቅርበት ዙርያ ተጠይቀው፣ “መላ አውሮፓ ለሩሲያ ጎረቤት ነው፤ ሩሲያን ችላ ለማለት አይቻልም፤ ከነልዩነታችንም በሚያቀራርቡን ነገሮች በጋራ መሥራት ነበረብን” ብለዋል።
አንጌላ መርክል የሩሲያን ወረራ ‘ተቀባይነት የሌለው ቀይ ስህተት’ ሲሉ ገልጠውታል።
አክለውም፣ “በዘመን ወደኋላ እየሄድን ይህ ቦታ፣ ያ ግዛት፣ ያንተ ነው፣ የኔ ነው መባባል ከተጀመረ ዓለም ጦርነት እንጂ ሌላ ሥራ አይኖራትም” ብለዋል።
አንጌላ፣ ሩሲያ ክራይሚያን ከጠቀለለች ወዲህ በማዕቀብ መታለፏ ስህተት እንዳልነበረም ተከራክረዋል።
የሚኒስክ የሰላም ስምምነትም መጥፎ እንዳልነበረና በዚያ ጊዜ ሂደት ዩክሬን ጠንካራ አገር ሆና መውጣቷን አውስተዋል።
አንጌላ በፈረንጆቹ 2008 ዓመተ ምሕረት ዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ተቃውመው ነበር። ይህን በተመለከተም ጸጸት እንደማይሰማቸው ነው በቃለ ምልልሱ የተናገሩት።
“አንደኛ ዩክሬን አባል ለመሆን የሚያስችል ቁመና ላይ አልነበረችም፤ ሁለተኛ ከሩሲያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ወደ ቀውስ የሚከትና ፑቲንን የሚያስቆጣ ነበር የሚሆነው” ብለዋል።
ዩክሬን ዝግጁ አልነበረችም ሲባል በውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና በለከት የለሽ ሙስና የምትታመስ አገር እንደነበረች አስታውሰዋል።
የአሁኑ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው ጀርመን ያን ጊዜ ኔቶን እንዳንቀላቀል ማድረጓ ትልቅ ጥፋት ነበር ሲሉ ተሰምተዋል።
ሥልጣን በለቀቁ በስድስት ወራቸው ሰፊ ቃለ ምልልስ የሰጡት አንጌላ መርክል ለፕሬዝዳንት ዜሌንስኪና ለዩክሬን ሕዝብ ጀግንነትና ብርታት ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም።












