የአውሮፓ ሕብረት ለተፈጠረው የምግብ ቀውስ ሩሲያን ተጠያቂ በማድረጉ ክሬምሊን ስብሰባውን ረግጣ ወጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ በዩክሬን የፈፀመችው ወረራ ለዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ መንስኤ ሆኗል ሲሉ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመውቀሳቸው ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ አምባሳደር የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባን ረግጠው ወጥተዋል።
ሩሲያ የምግብ አቅርቦቶችን እንደ “ሚሳኤል" በመጠቀሟ ሕዝብን ወደ ድህነት እያስገባች ነው ሲሉ ቻርለስ ሚሼል ገልጸዋል።
የሩሲያው ተወካይ ቫሲሊ ኔቤንዚያ በበኩላቸው ሚሼል የውሸት መረጃ አሰራጭተዋል ሲሉ ከሰዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የምግብ እህል ከዩክሬን ወደቦች እንዳይነሳ እንቅፋት ሆኗል።
ዩክሬን የምግብ ዘይትን ጨምሮ እንደ በቆሎ እና ስንዴ ያሉ ጥራጥሬዎችን ወደ ውጭ በመላክ ቀዳሚ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።
ሩሲያ በበኩሏ ከፍተኛ መጠን ያለው እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ ትልካለች። የእነዚህ ምርቶች እጥረት ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሆኗል።
ሚሼል በኒውዮርክ በተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ "የተከበሩ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር፣ እውነታውን እንነጋገር ከተባለ ክሬምሊን የምግብ አቅርቦቶችን እንደ ስውር ሚሳኤል በታዳጊ አገራት ላይ እየተጠቀመችበት ነው" ብለዋል።
"የሩሲያ ጦርነት ያስከተለው ዳፋ በዓለም ዙሪያ እየደረሰ ነው። ይህም የምግብ ዋጋን ከማናር ባለፈ ሰዎችን ወደ ድህነት በመግፋት በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት እያስከተለ ነው” ብለዋል።
“ለዚህ የምግብ ችግር ብቸኛዋ ተጠያቂ ሩሲያ ናት።“
በሩሲያ በተከለከለው የባሕር ኃይል እገዳ ምክንያት በዩክሬኗ ኦዴሳ ወደብ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር እህል ተከማችቶ ማየታቸውን ተናግረዋል።
ሚሼል አክለውም ሩሲያ በምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት እህል ከመስረቅ ባለፈ በዩክሬን ሰብል እንዳይዘራ እና እንዳይሰበሰብ አድርጋለች ሲሉ ከሰዋል።
ይህ አስተያየታቸው ኔቤንዚያን ስብሰባውን ረግጠው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። “እውነቱን ላለመስማት ቀላል በመሆኑ ስብሰባውን ረግጠው ሊወጡ ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ሚሼል በቀጥታ ለአምባሳደሩ ተናግረዋል።
ኔቤንዚያ ከወጡ በኋላ ለሮይተርስ እንደተናገሩት “ቻርለስ ሚሼል ለማሰራጨት በመጣው ውሸት” ምክንያት መቆየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በሌላ ስብሰባ ላይ ደግሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ የዩክሬን እህል ከአገሪቱ እንዳይወጣ እየከለከለች መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያ ጦር የዩክሬንን የእርሻ መሠረተ ልማትን አውድሟል ሲሉም ከሰዋል።
ከበጎ አድራጊዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ከግሉ ሴክተር አካላት ጋር በበይነ መረብ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ነው ብሊንከን “በኦዴሳ አቅራቢያ ወደ 20 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ስንዴ አለ። እህል የተሞሉ መርከቦችም በሩሲያ እገዳ ምክንያት ቆመዋል” ብለዋል።
ከሚሼል ጋር በሚስማማ መልኩም ሩሲያ የዩክሬንን እህል ለራሷ ጥቅም ለመሸጥ “ትዘርፋለች” የሚሉ ታማኝ ዘገባዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።












