ዩኬ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመርያ ጊዜ ኤም 270 የተባሉ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ልትሰጥ ነው።
ዩኬ እነዚህን እጅግ ዘመናዊ ሮኬት ማስወንጨፍያ መሣሪያዎች መቼ እና በምን ያህል መጠን ወደ ዩክሬን እንደምትልክ አልገለጸችም።
ሆኖም ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ለመነሻ ያህል ሦስት ሚሳኤል ማስወንጨፍያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ዩኬ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከአሜሪካ ጋር ከመከረች በኋላ ነው።
የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲን አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው የጦር መሣሪያ ብዙ እንዳስቆጣቸው ተሰምቷል።
ትናንት እሑድ ፑቲን እንደተናገሩት አሜሪካ ይህን የጦር መሣሪያ ልገሳ የማታቆም ከሆነ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርሰው ጥቃት መጠኑ እየሰፋ እንደሚመጣ ዛቻ ሰንዝረዋል።
ዩኬ ይህን ውስብስብና ዘመናዊ መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ ለዩክሬን ወታደሮች በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ስልጠና እሰጣለሁ ብላለች።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ነበር ኤም142 ተወንጫፊ ሚሳኤል ሲስተምን ወደ ዩክሬን የላከችው።
አሜሪካ ይህን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ መሣሪያ ብትሰጥም ዩክሬን ይህን መሣሪያ ወደ ሩሲያ ግዛት እንዳትተኩስ በማሳሰብ ነው።
አሁን ከዩኬ ለዩክሬን የሚለገሰው ኤም270 ሮኬት ሲስተም 300 ኪሎ ሜትርየሚወነጨፍ ሲሆን በአንድ ደቂቃ 18 ዙር ሮኬት ሊያስወነጭፍ ይችላል።
25 ቶን የሚመዝነው ይህ ሮኬት በሰዓት 64 ኪሎ ሜትር በመክነፍ የጠላትን ኃይል መምታት የሚችል ነው።
ፑቲን ትናንት ከአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ምዕራባዊያን ለዩክሬን መሣሪያ በገፍ እየለገሱ ያሉት ይህን ጦርነት በተቻለ መጠን ቶሎ እንዳይጠናቀቅ ለማድረግ ነው።
ሩሲያ ከኪየቭ ወደ ምሥራቅ ዩክሬን ዶንባስ ግዛት ትኩረቷን ካደረገች ወዲህ ትናንት እሑድ ለመጀመርያ ጊዜ ኪየቭ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች።












