ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ምን ያህል ስጋት ነው?

ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጀርባ ታንክ፣ የተኛ ልጅ፣ እንዲሁም ሠልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ላለፉት 18 ወራት ዓለም ትኩረቱን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ አድርጎ ቆይቷል።

በእርግጥ የጦርነቱ ስፋት እና ያደረሰው ቀውስ ለትኩረቱ ሰበብ መሆኑ የሚጠበቅ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ጥቃቶች እንዲሁም መነሻቸውን ሃይማኖት ያደረጉ ግጭቶችም ተስተውለዋል።

እነዚህ ግጭቶች አንዳንዴ ሰበባቸው ብሔር ቢሆንም መዳረሻቸው ግን ሃይማኖት ሆኖ፣ ወይንም ደግሞ በተቃራኒው መነሻቸው ሃይማኖት ሆኖ መዳረሻው ብሔር የሆነባቸው ጊዜያት አሉ።

እነዚህ በብሔር እና በሃይማኖት ጽንፈኞች የተነሳ እዚህም እዚያም ሲቀሰቀሱ የምንሰማቸው ግጭቶች እና ጥቃቶች ኢትዮጵያን ምን ያህል ያሰጓታል?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በኢትዮጵያ የድኅረ ምረቃ የሥነ መለኮት ኮሌጅ መምህር የሆኑት ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) ብዙ ሰዎች ጽንፈኝነትን ከአጥባቂነት ጋር ያምታቱታል ይላሉ።

እንደ ተካልኝ (ዶ/ር) ጽንፈኝነት ሌላው የሚምታታው በሃይማኖት ውስጥ ካለ መነቃቃት ጋር ነው።

ጽንፈኝነት ከማንኛውም ጉዳይ ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚሉት ምሁሩ፣ ርዕሰ ጉዳዩ ሃይማኖት ሲሆን የሃይማኖት ጽንፈኝነት፣ ፖለቲካ ሲሆን ደግሞ የፖለቲካ ጽንፈኝነት እንደሚባል ገልጸዋል።

የጽንፈኝነት መለያ ባሕርያት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጽንፈኝነት ቀዳሚ መለያ ባሕሪው ራሱን የእውነት ብቸኛ ባለቤት ማድረጉ ነው።

ተካልኝ (ዶ/ር) እኔ ከማየው አተያይ ውጪ ያሉት አተያዮች በሙሉ ከእውነት ተጻርረው የቆሙ ሐሰቶች ናቸው፣ ከክፋት ጋር የወገኑ ናቸው፣ ስለዚህ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ልንታገላቸው ያስፈልጋል የሚል የአእምሮ ቅኝት አለው ሲሉ ያብራሩታል።

ከሌላው ጋር በአብሮነት፣ በመደራደር፣ በመነጋገር ነገሮችን ከመፍታት ይልቅ ጉልበትን እና ጥቃትን መጠቀምን እንደ መፍትሔ አድርጎ ይጠቀማል።

ሌላኛው የጽንፈኝነት መገለጫ ባሕርይ ደግሞ ሃሳቡን ሊቀበል የማይችል ሰውን ካለበት ቦታ እንዲወገድ፣ እንዲጸዳ ይፈልጋል።

ስለዚህ ጽንፈኝነት ግቡን ለማስፈጸም የሚሄድበት መንገድ፣ ሌላውን ሰው የሚመለከትበት መንገድ መጠንተኝነት የሚጎድለው ነው።

በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፍሎሪዳ በሃይማኖት እና በአፍሪካ ጥናት ማዕከል ውስጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ቴሪ ኦስቴቦ በበኩላቸው ጽንፈኝነት በተለያየ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል መሆኑን ያብራራሉ።

ጽንፈኝነትን ኃይል ከሚጠቀም አካል ጋር አዛምዶ መጠቀም የተለመደ መሆኑን የሚያነሱት ፕሮፌሰሩ፣ የሌሎችን ሃይማት በአሉታ ለሚመለከቱ ሰዎችም ስያሜው አገልግሎ እንደሚያውቅ ያብራራሉ።

ቃሉ ለትርጉም የተጋለጠ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ቴሪ፣ ከሌሎች በተለየ ሃይማኖቱን በተለየ መንገድ የሚመለከት ልንለው እንችላለን ይላሉ።

ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የምንኖርባት ዓለም የሃይማኖት ብዝሃነት ያላት ብትሆንም፤ የሃይማኖት ብዝሃነትን ተቀብሎ፣ አቻችሎ ከመኖር ይልቅ ከተቻለ ሌላኛውን ማጥፋት፣ ካልሆነ ደግሞ ሌላኛውን በሁከተኛነት ለማስተናገድ የሚፈልግ ይሆናል።

ይህንን በማድረግ ሂደት ውስጥ ደግሞ ኃይልንም ጭምር መጠቀም የሚፈልግ የአተያይ ዓይነት ነው ይላሉ ዶ/ር ተካልኝ።

የሙስሊም እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት አባቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሃይማኖት ጽንፈኝነት እና ኢትዮጵያ

 ኢትጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጽንፈኝነት ብቅ ያለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመሆኑን ዶ/ር ተካልኝ ያብራራሉ።

ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከወጣ ወዲህ ባሉት አምስት ዓመታት (1983-1987) በተለይ ደግሞ በ1986 እና 1987 አካባቢ ጽንፈኝነት ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ይነሳ እንደነበር ያስታውሳሉ።

የዚህ መነሻ ምክንያቱ በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሱ የቦንብ ጥቃቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።

በተለይ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ የመገናኛ ሚኒስትር በነበሩት አብዱል መጂድ ሁሴን ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ፣ የግብፅ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ከተቃጣባቸው ጥቃት ጋር ተያይዞ የእስልምና አክራሪነት ይነሳ እንደ ነበር ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ የሚገባ፣ በዋነኛነት ኢትዮጵያውያን ያልተሳተፉበት ዓይነት ጽንፈኝነት አለ የሚለው አመለካከት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደርጅቶ ነበር።

በኋላ ላይ በተለይ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ተያይዞ በውጪ አገራት ሰልጥነው የመጡ ወጣቶቸ መካከል የሚታይ አመለካከት ነው በማለት ሰዎች ማንሳት መጀመራቸውን ተካልኝ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

በኋላም ላይ በ2001 (እኤአ) በአሜሪካ መሪነት ዓለም አቀፉ የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ መቀስቀስን ተከትሎ ኢትዮጵያም ውስጥ ይህ ጽንፈኝነት የሚለው ሃሳብ ተመልሶ መነሳት ጀመረ።

በ2006 ጅማ አካባቢ በርካታ ሰዎች በሃይማኖታቸው የተነሳ ከመገደላቸው ጋር ተያይዞ ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ውስጥም ቦታ አግኝቷል የሚለው አመለካከት ስፍራ እየያዘ መጣ ይላሉ ተካልኝ (ዶ/ር)።

በኋላም ከ2011 መጨረሻ ጀምሮ ከድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ እንደገና ይህ ሃሳብ አንሰራራ።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴንም በተወሰነ ደረጃ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ አለው ብሎ ማቅረብ ጀምሮ እንደነበር አክለው ይጠቅሳሉ።

ከዚህ በኋላም ቢሆን በተለያየ ጊዜ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚደርሱ ጥቃቶች ጋር ይህ ቃል በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሲውል ታይቷል።

ፕሮፌሰር ቴሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖትን የማጥበቅ እርምጃዎች ይስተዋላሉ ይላሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ እነዚህ ሃይማኖተኞች ስፍራ ለማግኘት እና ሃይማኖታቸውን ይበልጥ ለማጥበቅ በጣሩ ቁጥር ሌሎች ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም።

ይህ ደግሞ አንዳንዴም ቢሆን ወደ ግጭት ያመራል።

ሃይማኖትን ለማስፋፋት ከመሞኮር፣ የራሳቸውን ለመከላከል፣ አልያም ደግሞ የእኛ ነበር የሚለውን ዳግም ለማስመለስ በሚደረግ ትግል ውስጥ ፍርሃት፣ ብስጭት እና ግጭት ይከሰታል።

በዶ/ር ተካልኝ አመለካከት በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌሎች አገራት ጽንፈኝነት የሚታይባቸው ግለሰቦች አሉ።

“ነገር ግን ጽንፈኝነት በጣም ጠንካራ እና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ደርጅቶ እንዲሁም ትስስር ያለው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ በየትኛውም የሃይማኖት ዘርፍ ውስጥ ስር በሰደደ እና መሰረት በያዘ መልኩ አለ ብዬ አላምንም” ይላሉ።

“ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ማኅበራዊ መሰረት ኖሮት፣ በርካታ ሰው ሀሳቡን ገዝቶት፣ የተሰራጨ ሃሳብ ሆኗል ብዬ አላምንም።”

ሰውን በቀላሉ ማነሳሳት ስለሚቻል ሃይማኖትን፣ ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ሰዎች ጭምር ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት መሳርያ ነው ይላሉ ዶ/ር ተካልኝ።

በተለያየ ጊዜም በተነሱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሃይማኖት ማገዶ በመሆን አብሮ መቅረቡን ያስታውሳሉ።

በግለሰቦች ደረጃ ሃይማኖተኛም ቢሆኑም፣ ባይሆኑም ጽንፈኝነት አለ ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ጽንፈኝነት በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ እንደሚታይ የሚያስረዱት ዶ/ር ተካልኝ “ጽንፈኝነት የአእምሮ ቅኝት እና አካሄድ ስለሆነ በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ይገኛል” ይላሉ።

መስጂድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጽንፈኝነት ከእምነት ውጪ ባሉ ተቋማት

ፕሮፌሰር ቴሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የብሔር ጽንፈኝነት እንደሚታይ ይናገራሉ።

ይህም የእኔ ብሔር ከሌላው ይበልጣል በሚል እንደሚገለጥ ጨምረው ያስረዳሉ።

ዶ/ር ተካልኝ በበኩላቸው ፖለቲካ እና ብሔር በርካታ ብዝሃነት ያለበት መሆኑን ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያሉባት አገር መሆኗን የሚጠቅሱት ተካልኝ (ዶ/ር) ፖለቲካውም የፌደራል ሥርዓቱን የሚደግፉ እና የሚነቅፉ ጎራ የለዩባት መሆኗን ያነሳሉ።

ስለዚህ ይላሉ ምሁሩ፣ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው ብሔሮች አንስቶ እስከ ህዳጣን (አነስተኛ ቁጥር) እስካላቸው ድረስ ሌላውን አስመልክቶ ያላቸው ዕይታ ሌላውን ማቀፍ ከሌለበት፣ ሌላውን ማጥፋት የሚል ሃሳብ ካለበት፣ የሚፈልጉትን መብቶች በማስፈጸም ረገድ ደግሞ ኃይልን፣ ማጥቃትን እንደ መንገድ ከተጠቀሙ ጽንፈኝነት ሰፍኗል ልንል እንችላለን ይላሉ።

ስለዚህ ጽንፈኛ ብሔርተኞች እና ፖለቲከኞች የእነርሱን ወገን በሌላው ላይ መቀስቀስ፣ ማነሳሳት፣ የሚጠይቋቸው ነገሮች ደግሞ በፍፁም ተቀባይነት ሊኖራቸው የማይችሉ፣ ከዲሞክራሲያዊ እሴቶች የሚጣረሱ ሆነው ይገኛሉ።

በተደራጀና በመንግሥት መዋቅር እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት በእንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ ወይንም ፊት ለፊት ሲሳተፉ እንደማይስተዋሉ ይገልጻሉ።

ከዚያ ይልቅ በግላቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪዝም ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የብሔር እና የፖለቲካ ጽንፈኝነት እንደሚታይ ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ፖሊስ በእሬቻ በዓል ላይ ቢሾፍቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጽንፈኝነት መሰረት እንዲይዝ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

እንደ ዶ/ር ተካልኝ ገለጻ የሚጠየቀው የመብት ዓይነት የተለያየ ይሁን እንጂ፣ ጽንፈኝነት ምንጊዜም ከመብት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነው።

ፖለቲካ ውስጥ የምንፈልገውን ያህል ተሳትፎ አላገኘንም፣ ከብሔር አንጻር መጠቀም ያለብንን ያህል አልተጠቀምንም የሚል ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰር ቴሪ ያብራራሉ።

በማኅበራዊ መዋቅሮቻችን ውስጥ ከሌላው ጋር እንደ አቻ አልተቆጠርንም የሚል የመገፋት ስሜት ሊሆን እንደሚችለም ዶ/ር ተካልኝ ያክላሉ።

“ተጠቅቻለሁ፣ መብቴ ተገፏል፣ የሚገባኝን አላገኘሁም። ይህንን በማጣት ውስጥ ደግሞ አደናቃፊ የሆኑ አሉ” በሚል ትግሉ እንደሚጀምር ምሁራኑ ይጠቅሳሉ።

የፖለቲካ ምኅዳሩ ክፍት ሳይሆን፣ ኢኮኖሚው ሁሉንም ሚዛናዊነት እንዲጠቀም የሚያስችል ሥርዓት እና መዋቅር ከሌለ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስሮች ውስጥ የሁሉንም እኩልነት ከመቀበል ይልቅ አበላላጭ ሥርዓት ሲኖር ጽንፈኝነት የሚያቆጠቁጥበት እና የሚያብብት እድል ይኖራል ይላሉ ተካልኝ (ዶ/ር)።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ግጭቶች መኖራቸው መቼም እንደማይቀር የሚያነሱት ተካልኝ (ዶ/ር)፣ መፍትሔው ግጭቶችን የምናስተናግድባቸው መንገዶችን ማስተካከል ነው ይላሉ።

አክለውም ግጭቶችን ስናስተናግድ አንደኛውን ወገን መጫን መፈለግ እንደሚታይ በመግለጽ፣ “በዚህ ውስጥ የሌላውን ሰው ጉዳይ፣ ሃሳብ፣ ፍላጎት፤ አያገባኝም እኔ ባለጉልበት ስለሆንኩ የምፍልገውን በጉልበቴ አስፈጽማለሁ” የሚል በጊዜ ሂደት የሚፈነዳ ጽንፈኝነትን እያዋለደ መሆኑን ያብራራሉ።

የምንፈልገውን ነገር በማስፈጸም ሂደት ውስጥ “የሚያዋጣው መንገድ ሌሎችን ማጥቃት ነው ብሎ ማሰብ” ጽንፈኝነት እንዲያቆጠቁጥ መንገድ ከፋች ነው።

“ግጭትን ባስከተሉ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ወገን እኩል አድርጎ በማየት፣ እኛና እነርሱ ከመባባል በመውጣት ጥፋት ሲታይ አብሮ አልቅሶ፤ ኢፍትሃዊነት ሲሰፍን ወደ ፍትህ በጋራ ለማምጣት የሚያስችል ሥርዓት ሲፈጠር” ያኔ ጽንፈኝነት መብቀያ ቦታ ያጣል ይላሉ ዶ/ር ተካልኝ።

“አንዳችን ሌላኛችንን እንደ ጠላት፣ አንዳችን ከሌላኛችን እንደምናንስ ከማየት ወጥተን እንደ ባልንጀራ መተያየት” ጽንፈኝነትን በእንጭጩ ለመቅጨት ጥሩ መፍትሔ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በመንግሥት ደረጃ ደግሞ የሰዎች ጥያቄ በአግባቡ የሚመለሱበትን ዲሞክራሲያዊ መንገድ መገንባት፣ ሕግ የሚከበርበትን መንገድ ማስፈን፣ አድልዎ የሚያሰፍን ሥርዓት ማስወገድ፣ የጽንፈኝነት ሃሳብ ቢነሳ እንኳ የሚያብብበት ዕድል እንደማይኖረው ገልጸዋል።