በጎንደር በተከሰተው ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል- የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

ጎንደር ካርታ

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጎንደር ከተማ ትላንት ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሼህ ኤሊያስ መካነ መቃብር የቀብር ስነ ስርዓት ወቅት በተነሳ ግጭት ሳቢያ እስካሁን ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ150 በላይ ሰዎችም ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ ገለጸ።

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመስጅድ እና የእውቀት ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዑስማን ዑመር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

በትናንትናው እለት የአማራ ክልል መንግሥት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በግጭቱ ሳቢያ ሰዎች እንደሞቱ ቢገልጽም ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ በአሃዝ አልገለጸም።

በተጨማሪም በርካታ መስጂዶች መቃጠላቸውንና የሙስሊሙ ህብረተሰብ በተለይም የነጋዴው ሃብት ንብረት መዘረፉንም ሐጂ ዑስማን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማው የሚገኘው የሙስሊሙ ማህበረሰብ በተለያዩ መስጊዶች ተጠልለው እንደሚገና ጥበቃም እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገልጸው የሚመለከታቸው የመጅሊስ አመራሮች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የደረሰውን ጉዳት ማረጋገጥ አልቻሉም ብለዋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በጎንደር ሙስሊም መካነ መቃብር ቦታ ላይ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በቡድን እና በነፍስ ወከፍ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ብሏል።

ጥቃቱ የተፈጸመው "አስቀድመው በተዘጋጁ መሣሪያዎች" ነው ሲል የከሰሰው መግለጫው፣ በጥቃቱ ከሰው ሕይወት በተጨማሪ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሱቆች መዘረፋቸውን፣ መስጂዶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ሙስሊሞች እየተለዩ መደብደባቸውን ገልጿል።

ሐጂ ዑስማንም "ይሄ በግልፅ ታስቦበት ታቅዶበት የተደረገ ሴራ ነው።" ያሉ ሲሆን በቦምብ ሰዎች መቁሰላቸውንና እንዲሁም ጥቃቱ ወደ ከተማው ተስፋፍቶ መጠነ ሰፊ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል።

ለዚህ ግጭት መነሻ ሊሆን የሚችል ጉዳይ የለም ያሉት ሐጂ ዑስማን "አንድ ሃገር፣ አንድ ሃይማኖት የሚሉ ፅንፈኛ አክራሪዎች የፈጸሙት ድርጊት ነው" ይላሉ።

"ይህች ሃገር የኛ ብቻ ናት የሚል አስተሳሰብ ካልሆነ" የሚሰጠው ምከንያት ስህተት ነው ሲሉም ያስረዳሉ።

በትናንትናው ዕለት የቀብር ስነ ስርዓታቸው ግጭት ያስነሳው ሼኽ ከማል በከተማው ትልቅ አባትና በሃገር በቀል የህክምና ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆናቸውን ሐጂ ዑስማን ገልጸው "እኒህን አባት በክብር ለማሳረፍ በተደረገው ሂደት ላይ ነው አጸያፊ ድርጊት የተፈጸመው።" ብለዋል።

"እኒህ አባት ለጎንደር ከተማ ሙስሊም እንዲሁም ክርስቲያንም ትልቅ አርዓያ የሆኑ አባት ናቸው። የኋላ እሴቶቻችንና የኋላ ታሪኮቻችን ስናስታውስ የመከባበበሩ፣ የመቻቻሉና የአብሮነት እሴቶች እየተሸረሸሩ መሆኑን በግልፅ የሚያመላክት ድርጊት መሆኑን ነው በኛ በኩል የተረዳነው። ይሄ አስተሳሳብ በጊዜ መታረቅ ካልቻለ ወደፊትም የከፋ ችግር ይከሰታል" ሲሉም ኃላፊው ምክራቸውን ለግሰዋል።

የክልሉ፣ የፌደራሉ መንግሥትና የሃይማኖት አባቶች በተለይ የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ይህንን ጉዳይ ሊያወግዙትና አጥፊዎችን ወደ ህግ እንዲያቀርቡ፣ ተቀራርቦና ተከባብሮ የኖረውን ህብረተሰብ ወደነበረው ማንነቱ እንዲመለስ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱም በበኩሉ በመግለጫው በጎንደር ከተማ በሙስሊሞች ላይ የተቃጣውን ጥቃት አውግዞ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞችም ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጠይቋል።

አክሎም የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች "የእኛ መጨፍጨፍ፣ መበደል፣ መዘረፍ፣ መሰደድ ሊያንገበግባችሁ እና ሊያሳዝናችሁ ይገባል" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአማራ ክልል አስተዳደር በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እና በሙስሊሞች ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን "ተደጋጋሚ መዋቅራዊ ጥቃት እንዲያስቆም" እንዲሁም ጥፋተኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

ሐጂ ዑስማን በትናንትናው ዕለት የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነና ባለፉት ሰባትና ስምንት አመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ።

"በሆደ ሰፊነት ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በአካልም ከሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ሰፊ ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርገናል።፡" የሚሉት ሐጂ ዑስማን "ነገር ግን የመንግሥት አመራሮች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው የተፈጠረ ችግር ነው።" ይላሉ።

በአሁኑም ወቅት በህግ አግባብ ችግሮች እንዲፈቱ፣ አጥፊዎች እንዲያዙ፣ ወንጀለኞች እንዲቀጡ፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ስራዎችን እየሰሩም መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዛሬውም ዕለት ከትናንትናው መሻሻል የታየ ሲሆን "ህዝበ ሙስሊሙ እንዲረጋጋ፣ በህግና በህግ ብቻ መብቱን እንዲያስከብር የማረጋጋት ስራዎች እየተሰራ ነው። "ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ "በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን" ብሏል።

አክሎም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማሳባሰብ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ለመግለጽ፣ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል እና ለተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሥራዎች መጀመሩን አስታውቋል።

ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቃል ምልልስ ያደረጉት የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ችግሩን የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ እንደሆነና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

"ሃይማኖትን ለማጠልሸት እና ግጭቱን ለማባባስ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ድንጋይ በመወርወር" ግጭቱን ያባባሱ አካሎች እንዳሉ ጠቁመው፣ የጸጥታ መዋቅሩ ከሃይማኖት፣ ከብሔርና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ሰፊ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም አክለዋል።

የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱን በቁጥጥር ስር እንዳዋለና የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጎንደር ከተማ ወጣቶች በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙም አክሏል።

የተፈጠረው ምንድን ነው?

የአማራ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ግጭቱ የተከሰተው በጎንደር ከተማ ታዋቂ የነበሩት ሼኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር ትናንት እየተፈጸመ በነበረበት ወቅት ነው።

በቀብር ስፍራው ለቀብር የሚሆን ድንጋይ በሚነሳበት ወቀት፣ የመቃብር ስፍራው አጠገብ ያለው ቤተ ክርስቲያን "ድንጋዩ የቤተ ክርስቲያኑ ድንበር ውስጥ" እንደሆነ በመግለጽ ውዝግብ መነሳቱ ተገልጿል።

ሐጂ ዑስማን "ይህ የተሳሳተ ነው። ቀብር ሲፈጽሙ ድንጋይ የሚያነሱት እዛው ቦታቸው ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥም አይደለም። በሌሎች አካላት የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ወንጀለኞችንና አጥፊዎችን ላለመያዝና ጥፋተኞችን ወደኛ ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው።" ብለዋል።

የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ በክርስትና እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ግጭት ለማስነሳት በሚል "የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ድንጋይ መወርወር ተጀምሯል" ብለዋል።

የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ፣ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ "እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው" በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል ብሏል።

ክልሉ "በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ኾነ በንጹሃን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም" በሚል አቋሙን ከገለጸ በኋላ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ አካሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ "በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሙስሊም እና ክርስቲያን ወገኖቻችንን ለማፋጀት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ሁሉም የማኅበረሰባችን ክፍል ተባብሮ ሊያስቆመው ይገባል" ብሏል።

የትናንትናውን ክስተት በተመለከተ አብን ባወጣው መግለጫ "ሕዝባችንን ማኅበራዊ እረፍት መንሳት የሚፈልጉ አካላት አጀንዳ" ብሎታል።

የእስልምና ሃይማኖትና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች "አጥፊዎችን በመቆጣጠር ላይ ርብርብ እንዲያደርጉም" ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

ትናንት ምሽት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ምሥሎችና ቪድዮዎች በጎንደር የተከሰተውን ግጭት በመቃወም በተለያዩ ስፍራዎች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ያመላክታሉ።