መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

ካርታ

የፌደራሉ መንግሥት በስፋት በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የታገዘ ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ የአካባቢው ባለሥልጣን እና የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናገሩ።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው እና የፌደራሉ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀውን 'ሸኔ' ቡድን ለማጥፋት ለአንድ ወር የሚዘልቅ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስታውቆ ነበር።

ይህን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በተለይ በምዕራብ ሸዋ ዞን በሁለቱ አካላት መካከል ጥንካራ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡና ግንደበረት ወረዳ ነዋሪ በአካባቢው በታጣቂ ቡድኑ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን ይናገራሉ።

ነዋሪው፣ ባለፈው አርብ ሚያዚያ 14/2014 ዓ.ም. ብአቡና ግንደበረት ወረዳ ብደጎማ ኮቢ ቀበሌ መንግሥት በፈጸመው የአየር ጥቃት በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

"ባለፈው ዓርብ ደጎማ ኮቢ ቀበሌን ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአየር ከደበደቡ በኋላ ሰዎች ተገድለዋል። በዛ አካባቢ ወደ 400 ሰዎች ይኖራሉ አሁን ጥቃቱን በመሸሽ አንድም ሰው መንደር ውስጥ የሉም። ሸሽተው ጫካ ገብተዋል።" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ሚሬሳ በበኩላቸው በአካባቢው መንግሥት በድሮን የታዘገ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸው በአየር ጥቃቱ ንጹሃን ሰዎች ስለመጎዳታቸው መረጃው የለኝም ብለዋል።

"መንግሥት ሙሉ አቅም ተጠቅሞ እርምጃ እየወሰደ ነው። ሲቪል ሳይጎዳ ድሮን ጥቅም ላይ ውሏል። በዚህ አካባቢ ያለን መረጃ ጉዳት እየደረሰበት ያለው ኦነግ ሸኔ እንደሆነ ነው እንጂ ሲቪል ሰዎች ላይ አይደለም። ከአባቢው የወጡ ሲቪሎች እንዳሉ ግን መረጃው አለን" ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በተመሳሳይ መንግሥት በሠራዊታቸው ላይ የድሮን ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸው፤ "በአየር ድብደባው ወታደራዊ ስኬት አላገኙም። ይልቁንም ሲቪሎች ናቸው እየተጎዱ ያሉት። ደጎማ የሚባል ቦታ ሦስት ቤቶች አቃጥሏል። እኛ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። የሚያሳስበን በሲቪሉ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከቀናት በፊት "ሸኔን የማጽዳት" ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ይህ ወታደራዊ ዘመቻ የተፈለገለትን ዒላማ እያሳካ እንደሆነ በመግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፤ "ወታደሮቻችን እየተዋጉ ነው። ድል እንጂ ሽንፈት አልገጠመንም። . . . ከ400 በላይ ወታደር ማርከናል። የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችን ማርከናል" ይላሉ።

ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡነ ግንደበረት ወረዳ የመንግሥት ጥቃትን ተከትሎ የታጣቂ ቡድኑ አባላት አካባቢውን ጥለው ወጥተዋል ቢሉም ኦዳ ተርቢ ግን፤ "ለወታደራዊ ስትራቴጂ ቦታ ይቀያይራሉ እንጂ አልወጡም" ይላሉ።

"ድል እያደረግን ነው። መንግሥት ወታደር ልኮ የያዘው ቦታ የለም" በማለት ቃል አቀባዩ ይናገራሉ።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ሚሬሳ ባለፉት ቀናት በዞኑ በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች 'ኦነግ ሸኔን' የሚያወግዙ ሰልፎች ሕዝቡ አከናውኗል ይላሉ።

"ሸኔ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰው ስቃይ እጅግ እየተባባሰ በመምጣቱ በዞኑ ባሉ በርካታ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። ታጣቂዎቹን የሚቃወመው ሰልፍ እየተካሄደ ያለው ታጣቂዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው ወረዳዎች ውስጥ ነው" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዚያ 12/2014 ባወጣው መግለጫ "አሸባሪውን ሸኔ የማጽዳት ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብሎ ነበር።

ክልሉ በመግለጫው "በቡድኑ ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች የኦሮሞ ሕዝብ በቅርቡ ከቡድኑ እረፍት እንደሚያገኝ ማሳያዎች ናቸው" ብሏል።