የዩክሬኑ ጦርነት ባለፉት 50 ዓመታት ያልታየ የዋጋ ንረት እንደሚያስከትል ተገለጸ

ሱፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬን ጦርነት ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ወዲህ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ የሸቀጦች እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ባንክ አሳስቧል።

የዓለም ባንክ ባወጣው ትንበያ መሠረት የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በበርካታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እያስከተለ ሲሆን ከነዚህ መካከል በዋነኛነት የተፈጥሮ ጋዝ፣ ስንዴ እንዲሁም ጥጥ ይገኙበታል።

"የዋጋ ጭማሪው ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ጫናዎችን እያስከተለ ነው" ብለዋል ሪፖርቱን ካዘጋጁት መካከል አንደኛው የሆኑት ፒተር ኔግል።

አክለውም "በመላው ዓለም የሚገኙ ቤተሰቦች ጫናውን በደንብ እያስተዋሉት ነው። እኛን በጣም የሚያሳስበን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ናቸው ምግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጉልበትና ገንዘብ የሚያወጡት። የዋጋ ንረት ተከሰተ ማለት እነዚህን ቤተሰቦች ነው በቀጥታ የሚመለከተው" ብለዋል።

የኃይል አቅራቢ ድርጅቶች ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህ ደግሞ ለድሃ ቤተሰቦችና አነስተኛ የንግድ ተቋማት መጥፎ ዜና ነው ይላል የዓለም ባንክ።

ከፍተኛው የዋጋ ጭማሪ የሚኖረው አውሮፓ ውስጥ ሲሆን በዚህም ምናልባት ዋጋዎች ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምረው ልንመለከት እንችላለን።

የዋጋ ንረቱ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት እንዲሁም በ2024 ቅናሽ እንደሚያሳይ ተገምቷል።

ነገር ግን ምንም እንኳን ቅናሽ ቢስተዋል ከዚህ በፊት ከነበሩት ዋጋዎች አንጻር እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ይኖረዋል ብሏል የዓለም ባንክ።

የነዳጅ ዋጋም ቢሆን ጭማሪ እያሳየ እስከ 2024 ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ያልተጣራ ድፍድፍ በርሜል ነዳጅ በዚህ ዓመት እስከ 100 ዶላር ሊያወጣ ይችላል። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ንረትን ያባብሰዋል።

ሩሲያ ዓለማችን ከምትጠቀመው ነዳጅ 11 በመቶ የሚሆነውን ታቀርባለች።

ነገር ግን ጦርነቱ ቢቆም እንኳን ጦርነቱን ተከትሎ በርካታ ያደጉ አገራት ሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውና ትልልቅ የአውሮፓና አሜሪካ ድርጅቶች ሩሲያን ጥለው መውጣታቸው ለወደፊቱ በርካታ መዘዞችን ይዘው ይመጣሉ።

በሌላ በኩል አውሮፓውያን ከሚጠቀሙት ጋዝ 40 በመቶ የሚሆነው ከሩሲያ ሲሆን፣ የሚመጣው 27 በመቶ የነዳጅ ፍላጎታቸውም ቢሆን የሚሟላው በሩሲያ ነው።

ይህ ደግሞ በተለይ በአውሮፓ የዋጋ ንረቱ ከዕለት ወደ ዕለት እንዲጨምርና እጥረት እንዲከሰትም እያደረገ ነው።

የዓለም ባንክ እንደሚለው ከነዳጅና ጋዝ በተጨማሪ የምግቦች ዋጋም ቢሆን በእጅጉ ይጨምራል። የተባበሩት መንግሥታትም ቢሆን በ60 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የምግቦች ዋጋ ንረት መከሰቱን አስታውቋል።

የስንዴ ዋጋ የ42 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ገብስም ቢሆን የ33 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል።

የዶሮ ምርቶች የ41̇.8 በመቶ ጭማሪ እንዲሁም ሌሎች ጥራጥሬዎች የ29.8 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሎባቸዋል።

እነዚህ ሁሉ ቁጥሮች የሚያሳዩት ደግሞ ሩሲያና ዩክሬን ምን ያህል ለዓለማችን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አገራት እንደሆኑ ነው።

ከጦርነቱ በፊት ሁለቱ አገራት የዓለም ሕዝብ ከሚመገበው ስንዴ 28.9 በመቶ የሚሆነውን ያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ ዓለም ለማብሰል ይጠቀመው የነበረው የሱፍ ዘይትም ቢሆን 60 በመቶው የሚመጣው ከነዚሁ አገራት ነበር።