ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ሊያቀርቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶን) የመቀላቀል ጥያቄን በሚቀጥለው ወር ይፋ እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የፊንላንድ እና ስዊድን መሪዎች ግንቦት አጋማሽ ላይ ተገናኝተው ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄያቸውን በጋራ ያቀርባሉ ተብሏል።
አፍተንብላዴት የተባለ የስዊድን ጋዜጣ ሁለቱ አገራት ኔቶን ለመቀላቀል በሚያቀርቡት ማመልከቻ ላይ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ድጋፍ ለመስጠት ተስማምተዋል ሲል የስዊድን መንግሥት ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ስቶኮልም እና ሄልሲንኪ በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ላለመግባት ሲሉ እራሳቸውን ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አቅበው ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የሁለቱ አገራት አቋም ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ከከፈተች በኋላ ተቀይሯል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በስዊድን በነበራቸው ጉብኝት ላይ ከሩሲያ ወረራ በኋላ፤ "ሁሉንም ነገር ተቀይሯል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን፤ አገራቸው ለየትኛውን አይነት የሩሲያ እርምጃ እራሷን ዝግጁ ማድረግ አለባት ሲሉም ተደምጠዋል።
ፊንላንድ ከሩሲያ ጋር ረዥም ድንበር የምትጋራ ሲሆን የኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ ከሞስኮ ጋር ውጥረት ውስጥ እንደሚከታት ይጠበቃል።
1340 ኪሎ ሜትር ከሩሲያ ጋር የምትጋራ ሲሆን፤ የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሄልሲንኪ ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ የሚቀርብ ከሆነ ሞስኮ የራሷን እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ ተናግረው ነበር።
ሩሲያ ከፊንላንድ ጋር ወደምትዋሰንበት የድንበር አካባቢዎች ጦር መሳሪያዎችን እያንቀሳቀስች ነው የሚሉ ሪፖርቶች ቢወጡም አሜሪካ ግን ይህን የሚያረጋግጥ የደኅንነት መረጃ የለኝም ብላለች።
ሁለቱ አገራት ኔቶን ለመቀላቀል ማመልከቻ ሲያርቡ ከአሜሪካ እና ዩኬ ከሚቀርቡላቸው የደኅንነት ድጋፎች መካከል፤ በአገራቱ የሚሰፍሩ የጦር አባላትን ቁጥር መጨመር፣ የደኅንነት ትብብርን ማጠናከር፣ የሳይበር ስጋቶችን መከላከል እና በባልቲክ አካባቢ የኔቶ የጦር መርከቦች ቁጥርን መጨመር ይገኙበታል።
ሩሲያ የኔቶን መስፋፋት እንደ ስጋት ትመለከታለች። ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት ኔቶ ከምስራቅ አውሮፓ ጦሩን እንዲያስወጣ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጠይቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎት ያልነበራቸው አገራት የጦር ማሕበሩ አባል የመሆን ፍላጎት እያንጸባረቁ ነው።












