ሰዎች ለምን ራሳቸውን ስለማጥፋት ያስባሉ?

የተጨነቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Vladimir Vladimirov

ራስን ማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ትልቅ የሞት መንስኤ የሚታይ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም በሚገኙ ወጣቶች ዘንድም ሶስተኛው ትልቁ የሞት መንስኤ ራስን ማጥፋት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ቢያንስ 700 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከሶስት አራተኛው በላይ የሚሆኑት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች እንደሆነ ከኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ድረ-ገፅ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በምስራቅ አፍሪካ አገራትም ራስን የማጥፋት አኃዝ በዓመት ከ100 ሺህ ህዝብ ከ5.02-15.71 እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታትን ዋቢ አድርጎ ማህበሩ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው ጽሁፍ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው አመታዊ ራስን የማጥፋት መጠን መካከለኛ እንደሆነ የሚጠቅሰው በድረ-ገጹ የወጣው ፅሁፍ በዓመት ከ100,000 ህዝብ 9.63 ሲሆን ይህም ማለት በየቀኑ 30 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ ማለት ነው።

እዚህ ጋር በጉዳዩ ላይ በቂ በሚባል ደረጃ ጥናቶችና ምርምሮች አለመደረጋቸው እንዲሁም ማህበረሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለው እውቀት ዝቅተኛ መሆኑና እንደ ችግር የሚወራ ባለመሆኑ የበርካቶች ሞት መንስኤ ሳይወራ ወይም ተደብቆ ያልፋል።

አንድ የቤተሰብ አባል እራሱን ሲያጠፋ ማህበረሰቡ ሰዎች ምን ይሉኛል? በሚል ፍራቻ የሞቱን መንስኤ ይደብቃል አልያም ሌላ ምክንያት ለመስጠት ይሞክራል። ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። ስለጉዳዩ በግልጽ አለመወራቱ አንድ ሰው እራሱን ሲያጠፋ ሰዎች ለምን ብለው እንዳይጠይቁና ከሌሎች ተሞክሮዎች እንዳይማሩ ያደርጋቸዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ አእምሮ መምህር የሆኑት ዶክተር ኤሊያስ ገብሩ እንደሚሉት ምንም እንኳን በቂ በሚባል ደረጃ ጥናቶች ባይሰሩም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሐይማኖቶች ጠንካራ አማኞች ባሏቸው አገራት እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በእስልምናም ሆነ በክርስትና ሐይማኖቶች እራስን ማጥፋት እንደ ሀጢያት መቆጠራቸው ነው።

በሌላ በኩል ራስን ማጥፋት በሁሉም ሐይማኖቶች መከልከሉ ሰዎች እራሳቸውን ሲያጠፉ የተጎጂ ቤተሰቦች ጉዳዩን ለሰዎች እንዳያጋሩና እንዲደብቁት ያደርጋቸዋል።

በአጠቃላይ የኮቪድ-19 ወረርሽን ተከትሎ እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ ጨምሮ እንደነበር የሚገልጹት ዶክተር ኤልያስ ፣ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ይፋዊ የሆነ ጥናት ባይካሄድበትም እንደ ባለሙያ ሲታይ ግን ቀላል የማይባሉ ሰዎች ወረርሽኙን ተከትሎ እራሳቸውን ስለማጥፋት አስበዋል፣ ሞክረዋል አልያም ራሳቸውን አጥፍተዋል ይላሉ።

''እኔ ባለሁበት አካባቢ እንኳን 7 የሚሆኑ ወጣቶች በሁለት ወር ውስጥ እራሳቸውን አጥፍተው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች የማያወሯቸውና ሌሎች ሰዎች ሊሰሟቸው የማይችሉ በርካታ ሞቶች ሊመዘገቡ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው''

መጠጥ የሚጠጣ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, KatarzynaBialasiewicz

ሰዎች እራሳቸውን ወደማጥፋት የሚገፋቸው ምንድነው?

ባለሙያው እንደነገሩን እራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጊዜያዊም ሆነ ቀጣይነት ባለው የስነ አእምሮ ጤና መቃወስ ተጠቂ ናቸው። ስለዚህ እራስን ማጥፋት አልያም ስለማጥፋት ማሰብ አብዛኛውን ጊዜ ከስነ አእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ነው ማለት እንችላለን።

ለመሆኑ የትኞቹ የአእምሮ ጤና መቃወሶች ናቸው ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ አልያም እራሳቸውን ስለማጥፋት እንዲያስቡ የሚያደርጋቸውን ስንል ለዶክተር ኤልያስ ጥያቄ ሰነዘርን።

''በተለይ ከፍተኛ ድብርትና ጭንቀት ሰዎችን ወደዚህ መስመር የሚገፉ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው። እነዚህን የአእምሮ ጤና እክሎች በአግባቡ መረዳትና ማከም ስንችል እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ እንችላለን።" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከፍተኛ ድብርት ምክንያት የሌለው ጭንቀት፣ የባዶነት ስሜት፣ ደጋግሞ እራስን መውቀስ፣ ምንም የማልጠቅም ሰው ነኝ እያሉ ማሰብ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የሚረዳኝ ሰው የለም ብሎ ማሰብ፣ ከባድ ድካምና አቅም ማጣት፣ የእንቅልፍ መዛባት (ብዙ መተኛት አልያም እንቅልፍ ማጣት)፣ ስራና የግል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማጣት እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው።

በሌላ በኩል ከባድ ጭንቀት በዋነኛነት የወደፊቱን ነገር ካለማወቃችን ጋር ተያይዞ ምን ይፈጠር ይሆን እያልን የምንጨነቀው ነው። በአንድ ጊዜ ስለብዙ ነገሮች አብዝቶ መጨነቅ፤ ነገን እንዴት ነው የምሆነው ብሎ ሌሎች ስራዎችን ትቶ ቁጭ ብሎ ማሰብና ሕይወታችንን እስከ ማወክ ሊደርስ ይችላል።

እነዚህ የአእምሮ ጤና እክሎች ደግሞ በሰዎች የስራ ሕይወት፣ ትምህርት፣ የፍቅር ግንኙነት እንዲሁም ከቤተሰብና ጓደኞች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በእጅጉ ያበላሸዋል። ከባድ ጭንቀትና ከባድ ድብርት አብዛኛውን ጊዜ ተያይዘው የሚመጡ ነገሮች ሲሆኑ በአግባቡና በጊዜ ካልታከሙ ደግሞ ሰዎችን እራስን ማጥፋት ወደሚለው ጎዳና ሊመሩ ይችላሉ።

የትኞቹ የማህበረሰብ አባላት ተጋላጭ ናቸው?

ዶክተር ኤልያስ እንደሚሉት ከእድሜ አንጻር አፍላ እድሜያቸው ላይ የሚገኙ ወጣቶችና በአርባዎቹና ሀምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ጎልማሶች አካባቢ እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል።

በተለይ በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ማንነታቸውን ማወቅ የሚጀምሩበትና በርካታ የሕይወት ጥያቄዎችን መመለስ የሚጀምሩበት ወቅት መሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

''ታዳጊዎች ላይ የምናያቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ታዳጊዎች 20 ዓመት እስከሚሞላቸው ድረስ እራሳቸውን የሚያገኙበት፣ ማንነታቸውን የሚቀርጹበት ጊዜ እንደመሆኑ ብዙ ጊዜ ግራ መጋባት ውስጥ ሊከታቸው ይችላል። ከትምህርት፣ ከቤተሰብ ግንኙነት፣ ከጓደኞች እንዲሁም ከተቃራኒ ጾታ ግንኙነት አንጻር ብዙ አይነት መቀያየሮችና ግራ መጋባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ''

እነዚህን መቀያየሮችና እራስን የማግኘት ሂደት ውስጥ ደግሞ ታዳጊዎች ስሜታዊ መሆን፣ ራሳቸውን መቆጣጠር አለመቻል፣ ቶሎ ተስፋ መቁረጥ እንዲሁም ማንም ሰው አይረዳኝም ብሎ ማሰብ ውስጥ ይገባሉ። ታዳጊዎች በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ ብዙ ነገሮችን ይሞክራሉ፤ ይጠይቃሉ።

እነሱ በሚገባቸውና በሚረዱት ልክ መልስ የማያገኙ ከሆነ ደግሞ የህይወት ትርጉሙ ሊጠፋባቸውና ከዚህ ሁሉ ጭንቀት ብገላገልስ የሚል አስተሳሰብ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።

''ይህ የእድሜ ክልል ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ክትትልና ተጽዕኖ የሚደረግበት ነው። በተጨማሪ ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው መስተጋብር ከራሳቸው በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ነው። በአጭሩ በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች በቀላሉ ተፅእኖ ውስጥ ይገባሉ። በራሳቸው ብዙ ነገሮችን መወሰን አይችሉም''ይላሉ።

ይህንን ተከትሎ አንድ አስጨናቂና ከእነሱ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር ሲያጋጥማቸው በቶሎ ተስፋ የመቁረጥና ራስን ወደ ማጥፋት ሊያመሩ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የእድሜ ክልል ጥቂት የማይባሉ የአእምሮ ህመሞች እራሳቸውን የሚገልጡበት ወቅት ነው። በዘር የሚመጡት ህመሞችም ሆነ ሌሎች የአእምሮ ህመሞች በትክክል ህመም ሆነው መታየት የሚጀምሩት በዚህ እድሜ ውስጥ ነው።

ሌላ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ብለው ዶክተር ኤልያስ ያነሱት ጉዳይ ደግሞ ወጣቶች በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ በራሳቸውም ሆነ በጓደኞቻቸው ገፋፊነት ወደተለያዩ ሱሶች ውስጥ መግባታቸው አስተዋጽኦ እንዳለው ነው።

ከታዳጊዎች ጋር በተገናኘ በተለይ ወላጆችና ማህበረሰቡ በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን በአግባቡ መረዳትና በተቻለ መጠን ድጋፍ ማድረግ ያለበት ወቅት እንደሆነ ዶክተር ኤልያስ ያሳስባሉ።

''እነዚህ ታዳጊዎች የራሳቸው ፈቃድ እንዳላቸውና በራሳቸው ነገሮችን ማመዛዘን እንደሚችሉ ማህበረሰቡ መረዳት አለበት። ያለአግባብ አዳዲስ ነገሮችን እንዳይሞክሩ መከልከልና ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ እንዲያውም ወዳልሆነ ውሳኔ እንዲሁም ባህሪ ነው የሚገፋቸው'' ይላሉ።

አክለውም '' በህይወታቸው የራሳቸውን መንገድ እንዲያገኙ መደገፍና ትክክለኛውን አካሄድ ማሳየት ነው እንጂ በጭፍን መከልከልና እኛ የምንለውን ነገር ብቻ አድርጉ ማለት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ታዳጊዎች ነጻነትና እምነት ወሳኝ ናቸው'' በማለት ያስረዳሉ።

ታዳጊዎች አእምሯቸው እያደገና ጥያቄዎችን መጠየቅ ሲጀምሩ በተለይ ከሃይማኖት፣ ትምህርት፣ የፍቅር ግንኙነትና የወደፊት እቅዶች ጋር በተያያዘ ብዙ ግራ መጋባት ውስጥ ይወድቃሉ። ቤተሰብና ማህበረሰቡ ይህንን ተረድቶ ተገቢውን ድጋፍ ባላደረገላቸው ቁጥር ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆኑ ሲቀሩ በቶሎ ተስፋ መቁረጥና እጅ መስጠት ውስጥ ይገባሉ።

ሌላኛው ራስን በማጥፋት ትልቅ ቁጥር የሚመዘገብበት የእድሜ ክልል የጎልማሶች ነው። በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በህይወታቸው ባደረጓቸው ነገሮች ደስተኛ አለመሆንና ቁጭት ይስተዋልባቸዋል።

''ወደ ኋላ መለስ ብለው ህይወታቸውን የመቃኘትና ሀዘን ውስጥ መግባት ይስተዋላል። በውሳኔዎቻቸው መጸጸትና ከፍተኛ ጭንቀትና ድብርት ውስጥ መግባትም ይታይባቸዋል''

የማህበረሰብ ኃላፊነት

ዶክተር ኤልያስ እንደሚሉት ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ የሚችሉት አልያም ራሳቸውን ስለማጥፋት የሚያስቡት በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ከላይ በተጠቀሱት ሌሎች የአእምሮ ጤና መታወክ ምክንያት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድንገተኛ የሆነ አሳዛኝ ወይም አስደንጋጭ ክስተት ሲያጋጥም ነው።

''በሆነ አጋጣሚ ከሰዎች ጋር ሲጣላ ወይም የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥማቸው በቃ እኔ ብሞት ይሻለኛል። ምንም የማልጠቅም ሰው ነኝ የሚሉ ሰዎች ስናገኝ በቀላሉ ማለፍ የለብንም። ጓደኞችም ሆነ ቤተሰቦች ቀርበው ለምን መሞት እንደሚፈልግ ወይም ብዙ ጊዜ ስለመሞት ያስብ እንደሆነ መጠየቅና መረዳት አለባቸው። መርዳት በሚችሉት ሁሉ መንገድ ለመርዳት መጣር ኃላፊነታቸው ነው''

''በማህበረሰባችን ውስጥ እንደ ቀልድ የሚባሉ ለምሳሌ ፈጣሪዬ ውሰደኝ በቃ፤ የኔ ሕይወት ትርጉም የለውም አይነት ንግግሮችን ሰዎች ሲያዘወትሩ በጊዜያዊ ንዴት ውስጥ ሆነው ነው ወይስ የምር መሞት ይፈልጋሉ ብለን ማጣራት አለብን'' ሲሉ ያሳስባሉ።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት እራሱን ለማጥፋት ሞክሮ የሚያውቅ ሰው ከሆነ ቤተሰብም ሆነ ሌሎች የቅርብ ሰዎች ሁሌም ቢሆን በንቃት መጠበቅ አለባቸው። ግለሰቡ ከሌላ ጊዜው በተለየ መልኩ የጸባይ መለዋወጥ፣ ዝምታ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ጭንቀት የሚያበዛ ከሆነ ቀረብ ብሎ መጠየቅና በግልጽ ማውራት እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የሚወዱትን ሰው ያጡ ሰዎች፣ ሀብት ንብረታቸው የጠፋባቸው ሰዎች ወይም ከፈተና የወደቁ ተማሪዎች እራስን ስለማጥፋት የማሰብ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሊከታተሏቸው ይገባል።

ለምሳሌ አንድ ፈተና የወደ ተማሪ ወደ ሱቅ ሄዶ ገመድ አልያም በረኪና ለመግዛት ቢሞክር ባለሱቆች እንኳን የተማሪውን የፊት ሁኔታ ማጤንና ለምን እየገዛው እንደሆነ መጠየቅ አለባቸው።